መጽሐፈ መክብብ 3
3
ለሁሉ ጊዜ አለው
1ለሁሉ ዘመን አለው፥ ከፀሐይ#ዕብ. እና ግሪክ ሰባ. ሊ. “ከሰማይ” ይላል። በታችም ለሆነ ነገር ሁሉ ጊዜ አለው። 2ለመፅነስ ጊዜ አለው፥#“ለመፅነስ ጊዜ አለው” የሚለው በግእዝ ብቻ። ለመውለድም ጊዜ አለው፤ ለመኖር ጊዜ አለው፥ ለመሞትም ጊዜ አለው፤ ለመትከል ጊዜ አለው፥ የተተከለውንም ለመንቀል ጊዜ አለው። 3ለመግደል ጊዜ አለው፥ ለመፈወስም ጊዜ አለው፤ ለማፍረስ ጊዜ አለው፥ ለመሥራትም ጊዜ አለው፤ 4ለማልቀስ ጊዜ አለው፥ ለመሣቅም ጊዜ አለው፤ ዋይ ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመዝፈንም ጊዜ አለው። 5ድንጋይን ለመወርወር ጊዜ አለው፥ ድንጋይንም ለመሰብሰብ ጊዜ አለው፤ ለመተቃቀፍ ጊዜ አለው፥ ከመተቃቀፍም ለመራቅ ጊዜ አለው፤ 6ለመፈለግ ጊዜ አለው፥ ለማጥፋትም ጊዜ አለው፤ ለመጠበቅ ጊዜ አለው፥ ለመጣልም ጊዜ አለው፤ 7ለመቅደድ ጊዜ አለው፥ ለመስፋትም ጊዜ አለው፤ ዝም ለማለት ጊዜ አለው፥ ለመናገርም ጊዜ አለው፤ 8ለመውደድ ጊዜ አለው፥ ለመጥላትም ጊዜ አለው፤ ለጦርነት ጊዜ አለው፥ ለሰላምም ጊዜ አለው። 9ለሠራተኛ የድካሙ ትርፍ ምንድን ነው?
10እግዚአብሔር ለሰው ልጆች ይደክሙበት ዘንድ የሰጣቸውን ድካም ሁሉ አይቻለሁ። 11የሠራው ሥራ ሁሉ በጊዜው መልካም ነው፤ እግዚአብሔርም ከጥንት ጀምሮ እስከ ፍጻሜ ድረስ የሠራውን ሥራ ሰው መርምሮ እንዳያገኝ ዘለዓለምነትን በልቡ ሰጠው። 12ሰው ደስ ከሚለውና በሕይወቱ ሳለ መልካምን ነገር ከሚያደርግ በቀር በውስጣቸው መልካም ነገር እንደሌለ ዐወቅሁ። 13ደግሞም ሰው ሁሉ ይበላና ይጠጣ ዘንድ በድካሙም ሁሉ መልካምን ያይ ዘንድ የእግዚአብሔር ስጦታ ነው። 14እግዚአብሔር ያደረገው ሁሉ ለዘለዓለም እንዲኖር ዐወቅሁ፤ በእነርሱም ላይ መጨመር ከእነርሱም ማጕደል አይቻልም፤ እግዚአብሔርም በፊቱ ይፈሩ ዘንድ አደረገ። 15በፊት የተደረገው አሁን አለ። ይደረግ ዘንድ ያለውም እነሆ ተደርጓል፤ እግዚአብሔርም ያለፈውን መልሶ ይሻዋል።
16ደግሞም ከፀሐይ በታች በጻድቅ ስፍራ ኃጥእ፥ በኃጥእም ስፍራ ጻድቅ እንዳለ አየሁ። 17እኔም በልቤ፥ “በዚያ ለነገር ሁሉና ለሥራ ሁሉ ጊዜ አለውና በጻድቁና በኀጢአተኛው ላይ እግዚአብሔር ይፈርዳል” አልሁ። 18እኔ በልቤ ስለ ሰው ልጆች ነገር፥ “እንደ እንስሳ መሆናቸውን ያሳይ ዘንድ እግዚአብሔር ይፈርድባቸዋል” አልሁ። 19ለሰው ልጆች ሞት አለባቸው፥ ለእንስሳም ሞት አለባቸው፤ አንድ ሞት አለባቸው፤ አንዱ እንደሚሞት ሌላውም እንዲሁ ይሞታል፤ ለሁሉም አንድ እስትንፋስ አላቸው፥ ሰው ከእንስሳ ብልጫው ምንድን ነው? ሁሉም ከንቱ ነውና ምንም የለውም። 20ሁሉም ወደ አንድ ቦታ ይሄዳል፤ ሁሉ ከአፈር ተገኘ፥ ሁሉም ወደ አፈር ይመለሳል። 21የሰው ልጆች ነፍስ ወደ ላይ እንደምትወጣ፥ የእንስሳም ነፍስ ወደ ታች ወደ ምድር እንደምትወርድ የሚያውቅ ማን ነው? 22ያም ዕድል ፋንታው ነውና ሰው በሥራው ደስ ከሚለው በቀር ሌላ መልካም ነገር እንደሌለው አየሁ፤ ከእርሱ በኋላስ የሚሆነውን ያይ ዘንድ የሚያመጣው ማን ነው?
Currently Selected:
መጽሐፈ መክብብ 3: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ