የጭንቀት ቀን ሳይመጣ በጕብዝናህ ወራት ፈጣሪህን ዐስብ፤ ደስ አያሰኙም የምትላቸው ዓመታት ሳይደርሱ፥ ፀሓይና ብርሃን፥ ጨረቃና ከዋክብትም ሳይጨልሙ፥ ደመናትም ከዝናብ በኋላ ሳይመለሱ፥ ቤት ጠባቆች በሚንቀጠቀጡበት፥ ኀያላን ሰዎችም በሚጐብጡበት፥ ጥቂቶች ሆነዋልና ፈጭታዎች ሥራ በሚፈቱበት፥ በመስኮትም ሆነው የሚመለከቱ በሚጨልሙበት፥ በአደባባይም ደጆቹ በሚዘጉበት ቀን፥ የወፍጮ ድምፅ ሲላሽ፥ ከዎፍ ድምፅ የተነሣ ሰው ሲነሣ፥ ዜማም የሚጮኹ ሴቶች ልጆች ሁሉ ዝግ ሲሉ፤ ከፍ ያለውን ተመልክተው ደግሞ ሲፈሩ፥ ድንጋጤም በመንገድ ላይ ሲሆን፤ ለውዝም ሲያብብ፥ አንበጣም እንደ ሸክም ሲከብድ፥ ፍሬም ሳይበተን፤ ሰው ወደ ዘለዓለም ቤቱ ሲሄድ፥ አልቃሾችም በአደባባይ ሲዞሩ፤ የብር ድሪ ሳይበጠስ፥ የወርቅም ኵስኵስት ሳይሰበር፥ ማድጋውም በምንጭ አጠገብ ሳይከሰከስ፥ ወደ መስኮት የሚያዩ ዐይኖች ሳይጠፉ፥ የአደባባይ ደጆች ሳይዘጉ፥ ስለ ቃላት ድንጋጤ ከጠላት ቃል የተነሣ የሚጮኹ ሳይነሡ፥ በአዳም ልጆች ሁሉ ወዮታ ሳይሆን፥ ወደ ላይም ሳይመለከቱ፥ በመንገድም ፍርሀት ሳይመጣ፥ እሳትም ወደ ላይ ከፍ ማለትን በወደደ ጊዜ ሳይታይ፥ በአደባባይ ልቅሶ ሳይሰማ፥ የብር መልኩ ሳይለወጥ፥ የወርቅም መልኩ ሳይጠፋ፥ መንኰራኵሩም በጕድጓድ ላይ ሳይሰበር፥ አፈርም ወደ ነበረበት ምድር ሳይመለስ፥ ነፍስም ወደ ሰጠው ወደ እግዚአብሔር ሳይመለስ በሥጋም በነበረበት ጊዜ መልካም ወይም ክፉ ቢሆን ስለ ሠራው ሁሉ መልስ ሳይሰጥ ፈጣሪህን አስብ። ሰባኪው አለ፥ “ሁሉ ከንቱ፥ የከንቱ ከንቱ ነው።” ሰባኪውም ጠቢብ ስለ ሆነ ለሕዝቡ ዕውቀትን አስተማረ፥ ጆሮውም እንቆቅልሽን መረመረ። ሰባኪውም ያማረውን በቅንም የተጻፈውን እውነተኛውንም ቃል መርምሮ ለማግኘት ፈለገ። የጠቢባን ቃል እንደ በሬ መውጊያ ነው፥ የተሰበሰቡትም ከአንድ እረኛ የተሰጡት ቃላት እንደ ተቸነከሩ ችንካሮች ናቸው። ከዚህም ሁሉ በላይ፥ ልጄ ሆይ፥ ተግሣጽን ስማ፥ ፍጻሜ የሌላቸው ብዙ መጻሕፍትን አታድርግ። እጅግም ምርምር ሰውነትን ያደክማል። የነገሩን ሁሉ ፍጻሜ ስማ፤ ይህ የሰው ሁለንተናው ነውና፥ እግዚአብሔርን ፍራ፥ ትእዛዙንም ጠብቅ። እግዚአብሔር ሥራን ሁሉ የተሰወረውንም ነገር ሁሉ፥ መልካምም ቢሆን ክፉም ቢሆን፥ ወደ ፍርድ ያመጣዋልና።
መጽሐፈ መክብብ 12 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ መክብብ 12:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች