የጭንቀት ጊዜ ሳይመጣ፣ “ደስ አያሰኙኝም” የምትላቸው ዓመታት ሳይደርሱ፣ በወጣትነትህ ጊዜ፣ ፈጣሪህን ዐስብ። ፀሓይና ብርሃን፣ ጨረቃና ከዋክብት ሳይጨልሙ፣ ደመናትም ከዝናብ በኋላ ሳይመለሱ፣ ቤት ጠባቂዎች ሲርዱ፣ ብርቱዎች ሲጐብጡ፣ ጥቂት በመሆናቸው ፈጪታዎች ሲያቆሙ፣ በመስኮት የሚያዩትም ሲፈዝዙ፣ ወደ አደባባይ የሚያወጡ በሮች ሲዘጉ፣ ወፍጮ ሟልጦ ድምፁ ሲላሽ፣ ሰው በወፍ ድምፅ ሲነሣ፣ ዝማሬው ሁሉ ሲዳከም፤ ዳገት መውጣት ሲያርድ፣ መንገድም ሲያስፈራ፣ የአልሙን ዛፍ ሲያብብ፣ አንበጣም ራሱን ሲጐትት፣ ፍላጎት ሲጠፋ፤ በዚያም ጊዜ ሰው ወደ ዘላለማዊ ቤቱ ይሄዳል፤ አልቃሾችም በአደባባዮች ይዞራሉ። የብር ሰንሰለት ሳይበጠስ፣ የወርቅ ሳሕንም ሳይሰበር፣ የውሃ መቅጃው በምንጩ አጠገብ ሳይከሰከስ፣ ወይም መንኰራኵሩ በውሃ ጕድጓድ ላይ ሳይሰበር፣ ዐፈር ወደ መጣበት መሬት ሳይመለስ፣ መንፈስም ወደ ሰጠው ወደ አምላክ ሳይመለስ፣ ፈጣሪህን ዐስብ። ሰባኪው “ከንቱ ከንቱ ሁሉም ነገር ከንቱ ነው!” ይላል። ሰባኪው ጥበበኛ ብቻ አልነበረም፤ ነገር ግን ለሕዝቡ ዕውቀትንም ያስተምር ነበር። እርሱም በጥልቅ ዐሰበ፤ ተመራመረም፤ ብዙ ምሳሌዎችንም በሥርዐት አዘጋጀ። ሰባኪው ትክክለኛውን ቃል ለማግኘት ተመራመረ፤ የጻፈውም ቅንና እውነት ነበረ። የጠቢባን ቃላት እንደ ሹል የከብት መንጃ ናቸው፤ የተሰበሰቡ አባባሎቹም እጅግ ተቀብቅበው እንደ ገቡ ችንካሮች ሲሆኑ፣ ከአንድ እረኛ የተሰጡ ናቸው። ልጄ ሆይ፤ ከዚህ ሁሉ በላይ በማንኛውም ነገር ተጠንቀቅ፤ አንዳችም አትጨምር። ብዙ መጻሕፍትን መጻፍ ማብቂያ የለውም፤ ብዙ ማጥናትም ሰውነትን ያደክማል። እነሆ፤ ሁሉ ነገር ከተሰማ ዘንድ፣ የነገሩ ሁሉ ድምዳሜ ይህ ነው፤ አምላክን ፍራ፤ ትእዛዞቹንም ጠብቅ፤ ይህ የሰው ሁለንተናዊ ተግባሩ ነውና። መልካምም ይሁን ክፉ፣ ስውር የሆነውን ነገር ሁሉ አንድ ሳይቀር፣ ማንኛውንም ሥራ አምላክ ወደ ፍርድ ያመጣዋልና።
መክብብ 12 ያንብቡ
ያዳምጡ መክብብ 12
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መክብብ 12:1-14
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች