መጽሐፈ መክብብ 12:1-14

መጽሐፈ መክብብ 12:1-14 አማ05

በወጣትነትህ ዘመን ፈጣሪህን አስብ፤ ይህን ባታደርግ ግን ክፉ ቀን ይመጣብሃል፤ “ደስ አያሰኙኝም” የምትላቸው ዓመቶች ይደርሳሉ። የፀሐይ፥ የጨረቃና የከዋክብት ብርሃን ለአንተ የሚጨልምበት ጊዜ ይመጣል፤ ያን ጊዜ ከዝናብ በኋላ ደመናዎች ከስፍራቸው ፈቀቅ አይሉም፤ የምትተማመንባቸው ክንዶችህ ይንቀጠቀጣሉ፤ አሁን ብርቱ የሆኑ እግሮችህ ይዝላሉ፤ ጥርሶችህ ቊጥራቸው ከማነሳቸው የተነሣ ምግብ ማኘክ አይችሉም፤ ዐይኖችህ ከመፍዘዛቸው የተነሣ አጥርተው ማየት ይሳናቸዋል። ጆሮችህ የአደባባይ ጫጫታ አይሰሙም የወፍጮ ወይም የሙዚቃ ድምፅ መስማት ይሳንሃል፤ ሆኖም የወፍ ድምፅ እንኳ ከእንቅልፍህ ይቀሰቅስሃል። ወደ ከፍተኛ ስፍራዎች መውጣት ያስፈራሃል፤ በእግር መጓዝም አደገኛ ይሆንብሃል፤ ጠጒርህ እንደ ለውዝ አበባ ነጭ ይሆናል፤ ራስህን ችለህ መራመድ አቅቶህ እንደ አሮጌ ኩብኩባ ትጐተታለህ፤ ፍላጎትህ መቀስቀሱ ይቀራል። ድምፅ እንኳ ከእንቅልፍህ ይቀሰቅስሃል። ሰውም ወደ ዘለዓለማዊ መኖሪያው ይሄዳል፤ አልቃሾችም በየመንገዱ እያለቀሱ ይሸኙታል። የብር ሐብል ይበጠሳል፤ ከወርቅ የተሠራ መቅረዝ ወድቆ ይሰበራል፤ የውሃ መቅጃውን የያዘ ገመድ በውሃ ጒድጓድ ላይ ይበጠሳል፤ የውሃ መቅጃውም እንስራ ይከሰከሳል፤ ሥጋ ዐፈር ስለ ሆነ ወደ ዐፈር ይመለሳል፤ ነፍስም ወደ ፈጠራት ወደ እግዚአብሔር ትሄዳለች። ጥበበኛው፥ “ከንቱ! ከንቱ! ሁሉ ነገር ከንቱ ነው!” አለ። ጥበበኛው ጠቢብ ብቻ ሳይሆን ዕውቀትን ለሕዝቡ ማስተማር ቀጠለ፤ ብዙ ምሳሌዎችን መርምሮ ካጠና በኋላ በቅደም ተከተል አዘጋጀ፤ ጥበበኛው ተስማሚ የሆኑ ቃላትንም መረመረ፤ ስለዚህ እርሱ የጻፈው ሁሉ እውነትና ትክክል ነው። የጠቢባን ንግግር፥ እረኛ የከብቶቹን መንጋ እንደሚነዳበት ጫፉ እንደ ሾለ በትር ነው፤ በአንድነት የተከማቹ ምሳሌዎች ጠልቀው እንደሚገቡ ምስማሮች ናቸው፤ እነርሱም ከሁላችን ጠባቂ ከእግዚአብሔር የተሰጡ ናቸው። ልጄ ሆይ! ልትጠነቀቅባቸው የሚገባ ሌሎች ነገሮች አሉ፤ መጻሕፍትን ጽፎ ለመጨረስ ከቶ አይቻልም፤ የምርምርም ብዛት ሰውነትን ያደክማል። እነሆ፥ ሁሉ ነገር ተነግሮአል፤ የሁሉ ነገር መደምደሚያ ይህ ነው፤ እግዚአብሔርን ፍራ፤ ትእዛዞቹንም ጠብቅ፤ ይህ የሰው ዋና ተግባሩ ነው። እግዚአብሔር ስውር የሆነውን ነገር ሳይቀር የሰውን ሥራ ሁሉ ክፉውንም ደጉንም ወደ ፍርድ ያመጣዋል።