ትንቢተ አሞጽ 3
3
የእስራኤል በደልና ቅጣት
1የእስራኤል ቤት ሆይ! እኔ እግዚአብሔር በእናንተና ከግብፅ ምድር በአወጣሁት ወገን ሁሉ ላይ የተናገርሁትን ይህን ቃል ስሙ፤ እንዲህም አልሁ፦ 2“እኔ ከምድር አሕዛብ ሁሉ እናንተን ብቻችሁን አውቄአችኋለሁ፤ ስለዚህ ስለ ኀጢአታችሁ ሁሉ እበቀላችኋለሁ።” 3በውኑ ሁለት ሰዎች ሳይተያዩ በአንድነት ይሄዳሉን? 4ወይስ አንበሳ የሚነጥቀው ነገር ሳያገኝ በጫካው ውስጥ በከንቱ ያገሣልን? ወይስ የአንበሳ ደቦል አንዳች ሳይዝ በመደቡ ሆኖ በከንቱ ይጮኻልን? 5ወይስ ወፍ፥ አጥማጅ ከሌለው፥ በምድር ላይ በወጥመድ ይያዛልን? ወይስ ወስፈንጠር አንዳች ሳይዝ ከምድር በከንቱ ይፈናጠራልን? 6ወይስ በከተማ ውስጥ መለከት ሲነፋ ሕዝቡ አይደነግጡምን? ወይስ እግዚአብሔር ያላዘዘው ክፉ ነገር በከተማ ላይ ይመጣልን? 7ጌታ እግዚአብሔር ለባሪያዎቹ ለነቢያት ያልገለጠውንና ያልነገረውን ምንም አያደርግምና። 8አንበሳው አገሣ፤ የማይፈራ ማን ነው? ጌታ እግዚአብሔር ተናገረ፤ ትንቢት የማይናገር ማን ነው?
የሰማርያ ውድቀት
9በፋርስ ሀገሮችና በግብፅ ሀገሮች ዐውጁና፥ “በሰማርያ ተራሮች ላይ ተሰብሰቡ፤ በውስጥዋም የሆነውን ታላቁን ተአምር፥ በመካካልዋም ያለውን ግፍ ተመልከቱ” በሉ። 10“በፊቷ የሚመጣባትን አላወቀችም፤ ይላል እግዚአብሔር፤ በሀገራቸው ቅሚያንና ግፍን የሚያከማቹ ናቸው።” 11ስለዚህ ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እስከ ጢሮስ በአለው ዙሪያሽ ድረስ ምድርሽ ይጠፋል፥#ዕብ. “በምድሪቱ ዙሪያ ጠላት ይመጣል” ይላል። ብርታትሽንም ከአንቺ ያወርዳል፤ ሀገሮችሽም ይበዘበዛሉ።” 12ስለዚህ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “እረኛ ከአንበሳ አፍ ሁለት እግርን ወይም የጆሮን ጫፍ እንደሚያድን፥ እንዲሁ በሰማርያ በአሕዛብ ፊትና በደማስቆ የተቀመጡት የእስራኤል ልጆች ይድናሉ።
13“ካህናት ሆይ!#“ካህናት” የሚለው በዕብ. የለም። ስሙ፤ በያዕቆብም ቤት ላይ መስክሩ፥ ይላል ሁሉን የሚችል ጌታ እግዚአብሔር። 14እስራኤልን ስለ ኀጢአቱ በምበቀልበት ቀን የቤቴልን መሠዊያዎች ደግሞ እበቀላለሁ፤ የመሠዊያው ቀንዶች ይሰበራሉ፤ ወደ ምድርም ይወድቃሉ። 15የክረምቱንና የበጋዉን ቤት እመታለሁ፤ በዝሆንም ጥርስ የተለበጡት ቤቶች ይጠፋሉ፤ ሌሎችም ታላላቆች ቤቶች ይፈርሳሉ” ይላል ጌታ እግዚአብሔር።
Currently Selected:
ትንቢተ አሞጽ 3: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ