በማግሥቱም ጳውሎስ ከእኛ ጋር ወደ ያዕቆብ ገባ፤ ቀሳውስትም ሁሉ በዚያ ነበሩ። ጳውሎስም ሰላምታ ካቀረበላቸው በኋላ በእርሱ ሐዋርያነት እግዚአብሔር በአሕዛብ ያደረገውን ሁሉ ነገራቸው። እነርሱም ሰምተው እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ እንዲህም አሉ፥ “ወንድማችን ሆይ፥ ከአይሁድ መካከል ያመኑት ስንት አእላፋት እንደ ሆኑ ታያለህን? ሁሉም ለኦሪት የሚቀኑ ናቸው። ነገር ግን የማይሆነውን እንደምታስተምር፥ የሙሴንም ሕግ እንደምታስተዋቸው፥ በአሕዛብ መካከል ያሉ ያመኑ አይሁድንም ልጆቻቸውን እንዳይገርዙ፥ የኦሪትንም ሕግ እንዳይፈጽሙ እንደምትከለክላቸው ስለ አንተ ነግረዋቸዋል። አሁንሳ ምን ይሁን? ሕዝቡ ወደዚህ እንደ መጣህ ይሰሙና ይሰበሰቡ ይሆናል። ስለዚህም ይህን የምልህን አድርግ፦ ብፅዐት ያላቸው አራት ሰዎች በእኛ ዘንድ አሉ። ይዘሃቸው ሂድ፤ ከእነርሱም ጋር ራስህን አንጻ፤ ራሳቸውንም እንዲላጩ ስለ እነርሱ ገንዘብ ክፈልላቸው፤ የሚያሙህም በሐሰት እንደ ሆነ፥ አንተም የኦሪትን ሕግ እንደምትጠብቅ ሁሉም ያውቃሉ። ስለሚአምኑት አሕዛብ ግን እርም ከሆነውና ለጣዖታት ከሚሠዉት፥ ከዝሙት፥ ሞቶ የተገኘውንና ደምን ከመብላት እንዲከለከሉ እኛ አዝዘናል።” ያንጊዜም ጳውሎስ ሰዎችን ይዞ በማግሥቱ ከእነርሱ ጋር ነጻ። የመንጻታቸውንም ወራት መድረሱን ከነገራቸው በኋላ ሁሉም እየአንዳንዳቸው መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ ወደ ቤተ መቅደስ ይዞአቸው ገባ። በሰባተኛውም ቀን ከእስያ የመጡ አይሁድ ጳውሎስን በመቅደስ አዩት፤ ሕዝቡንም ሁሉ በእርሱ ላይ አነሳሥተው ያዙት። እየጮሁም እንዲህ አሉ፥ “እናንተ የእስራኤል ወገኖች ሆይ፥ ርዱን፤ በየስፍራው ሕዝባችንን፥ ኦሪትንም፥ ይህንም ስፍራ የሚቃወም ትምህርት ለሰው ሁሉ የሚያስተምር እነሆ፥ ይህ ሰው ነው፤ አሁንም አረማውያንን ወደ መቅደስ አስገባ፤ ቤተ መቅደስንም አረከሰ። የኤፌሶን ሀገር ሰው የሆነ ጥሮፊሞስን ከጳውሎስ ጋር በከተማ አይተውት ነበርና፤ ጳውሎስም ወደ ቤተ መቅደስ ያስገባው መስሎአቸው ነበርና። ከተማውም ሁሉ ታወከ፤ ሕዝቡም ሁሉ እየሮጡ ሄደው ጳውሎስን ጐትተው ከቤተ መቅደስ አወጡት፤ በሩንም ሁሉ ዘጉ። ሊገድሉትም ፈልገው ብዙ ደበደቡት፤ ወዲያውም ኢየሩሳሌም በመላዋ እንደ ታወከች የሚገልጥ መልእክት ወደ ሻለቃው ደረሰለት። በዚያ ጊዜም ጭፍሮቹን ከአለቆቻቸው ጋር ይዞ ወደ እነርሱ ሄደ፤ እነርሱም የሻለቃውን ጭፍሮች ባዩ ጊዜ ጳውሎስን መምታታቸውን ተዉ። የሻለቃውም ቀረብ ብሎ ያዘው፤ በሁለት ሰንሰለትም እንዲታሰር አዘዘ፤ “ምንድነው? ምንስ አደረገ?” ብሎም ጠየቀ። ሕዝቡም እኩሌቶቹ እንዲህ ነው፤ እኩሌቶቹም እንዲህ አይደለም እያሉ ይጮሁ ነበር፤ ሻለቃውም ሕዝቡ የሚታወክበትን ርግጡን ማወቅ ተሣነው፤ ወደ ወታደሮቹም ሰፈር እንዲወስዱት አዘዘ። ደረጃውንም በሚወጣበት ጊዜ ወታደሮች ተሸክመው አወጡት፤ ሰው ይጋፋ ነበርና። ብዙዎችም ይከተሉት ነበር፤ ሕዝቡም፥ “አስወግዱት” እያሉ ይጮሁ ነበር።
የሐዋርያት ሥራ 21 ያንብቡ
ያዳምጡ የሐዋርያት ሥራ 21
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 21:18-36
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች