የሐዋርያት ሥራ 21:18-36

የሐዋርያት ሥራ 21:18-36 አማ05

በማግስቱ ጳውሎስ ከእኛ ጋር ወደ ያዕቆብ ሄደ፤ የቤተ ክርስቲያን ሽማግሌዎች ሁሉ እዚያ ነበሩ። ጳውሎስ ለሁሉም ሰላምታ ከሰጠ በኋላ በእርሱ አማካይነት እግዚአብሔር በአሕዛብ መካከል ያደረገውን ሁሉ አንድ በአንድ ተረከላቸው። ይህን በሰሙ ጊዜ ሁሉም ጌታን አመሰገኑ፤ ጳውሎስንም እንዲህ አሉት፦ “ወንድም ሆይ! በብዙ ሺህ የሚቈጠሩ ምእመናን በአይሁድ መካከል እንዳሉና ሁሉም ለሕግ ቀናተኞች እንደ ሆኑ ታውቃለህ፤ አንተ በአሕዛብ መካከል የሚኖሩትን አይሁድ ሁሉ ‘ልጆቻችሁን አትግረዙ ወይም ሥርዓቶችን አትፈጽሙ’ እያልክ በማስተማር የሙሴን ሕግ እንዲሽሩ ታደርጋለህ እየተባለ የሚወራውን ሰምተዋል። እንግዲህ ምን ማድረግ ይሻላል? መምጣትህን በእርግጥ ይሰማሉ፤ ስለዚህ እኛ የምንልህን አድርግ፤ በእኛ መካከል ስለት ያለባቸው አራት ሰዎች አሉ። እነርሱን ውሰድና ከእነርሱ ጋር ሆነህ ራስህን አንጻ፤ ጠጒራቸውንም እንዲላጩ ለቤተ መቅደስ የሚሰጠውን የመባ ገንዘብ ክፈልላቸው፤ ይህን ብታደርግ በአንተ ላይ የተወራው ሁሉ ከንቱ መሆኑንና አንተም ራስህ ለሕግ ታዛዥ መሆንክህን ሁሉም ያውቃሉ። ከአሕዛብ ወገን ያመኑት ግን ‘ለጣዖት በመሠዋቱ ምክንያት የረከሰ ምግብ አትብሉ፤ ደምም አትብሉ፤ ታንቆ የሞተ እንስሳ ሥጋ አትብሉ፤ ከዝሙት ራቁ’ የሚለውን ውሳኔ የያዘ ደብዳቤ ጽፈን ልከንላቸዋል።” ከዚህ በኋላ ጳውሎስ ሰዎቹን ወሰደና በማግስቱ ከእነርሱ ጋር ራሱን አነጻ፤ የሚነጹባቸው ቀኖች መቼ እንደሚሆንና ስለ እያንዳንዱም የሚሰጠው የመባ ገንዘብ የሚከፈልበት ጊዜ መቼ እንደሚሆን ለማስታወቅ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ። ሰባቱ ቀን ሊፈጸም ሲቃረብ ከእስያ የመጡ አይሁድ ጳውሎስን በቤተ መቅደስ በማየታቸው ሕዝቡን ሁሉ አሳድመው ያዙት፤ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ! እርዱን! ሕዝባችንንና ሕጋችንን፥ ይህንንም ስፍራ እየተሳደበ በየአገሩ ያለውን ሕዝብ ሁሉ የሚያስተምር ይህ ሰው ነው፤ ይህም አልበቃ ብሎት አሕዛብን ወደ ቤተ መቅደስ በማስገባት ይህን የተቀደሰ ስፍራ አርክሶአል!” እያሉ ጮኹ። ይህንንም ያሉበት ምክንያት ከዚህ ቀደም የኤፌሶኑን ተወላጅ ጥሮፊሞስን ከእርሱ ጋር በከተማ አይተውት ስለ ነበር እርሱን ጳውሎስ ወደ ቤተ መቅደስ ይዞት የገባ መስሎአቸው ነበር። ከተማዋ በሙሉ ታወከች፤ ሕዝቡም ሁሉ እየሮጡ በአንድነት መጡና ጳውሎስን ይዘው እየጐተቱ ከቤተ መቅደስ አወጡት፤ የቤተ መቅደሱ በሮችም ወዲያውኑ ተዘጉ። ሰዎቹ ጳውሎስን ሊገድሉት በፈለጉ ጊዜ “የኢየሩሳሌም ከተማ በሙሉ ታውካለች” የሚል መልእክት ለሮማውያኑ ጦር አዛዥ ደረሰ። ስለዚህ እርሱ ወታደሮችንና የመቶ አለቆችን አስከትሎ በፍጥነት እየሮጠ ወደ ሰዎቹ ሄደ። ሰዎቹም አዛዡንና ወታደሮቹን ባዩ ጊዜ ጳውሎስን መደብደብ ተዉ። አዛዡም ቀርቦ ጳውሎስን ያዘውና በሁለት ሰንሰለት እንዲታሰር አዘዘ፤ ከዚህ በኋላ ማን መሆኑንና ምን እንዳደረገ ለማወቅ ፈልጎ ጠየቀ። ሕዝቡም አንዳንዶቹ አንድ ነገር ሲሉ፥ ሌሎች ሌላ ነገር ይሉ ነበር፤ አዛዡ ከሕዝቡ ጩኸት የተነሣ እርግጠኛውን ነገር ለማወቅ ስላልቻለ ጳውሎስን ወደ ወታደሮቹ ሰፈር እንዲወስዱት አዘዘ። ጳውሎስ ወደ ደረጃው በደረሰ ጊዜ ሕዝብ ሁሉ በብርቱ ቊጣ ተነሣሥቶ አደጋ ሊያደርስበት በመፈለጉ ወታደሮቹ ተሸክመውት ሄዱ። ሕዝቡም “ይገደል!” እያሉ በመጮኽ ይከተሉት ነበር።