በማግስቱም ጳውሎስና ሌሎቻችንም ያዕቆብን ለማየት ሄድን፤ ሽማግሌዎችም ሁሉ በዚያ ነበሩ። ጳውሎስም ሰላምታ ካቀረበላቸው በኋላ፣ እግዚአብሔር በርሱ አገልግሎት አማካይነት በአሕዛብ መካከል ያደረገውን ሁሉ በዝርዝር አስረዳቸው። እነርሱም ይህን ሲሰሙ፣ እግዚአብሔርን አመሰገኑ፤ ጳውሎስንም እንዲህ አሉት፤ “ወንድም ሆይ፤ በብዙ ሺሕ የሚቈጠሩ አይሁድ እንዳመኑ ተመልከት፤ ሁሉም ደግሞ ለሙሴ ሕግ የሚቀኑ ናቸው። በአሕዛብ መካከል የሚኖሩ አይሁድ ሁሉ ሙሴን እንዲተዉና ልጆቻቸውን እንዳይገርዙ፣ በቈየው ልማዳችን መሠረት እንዳይኖሩ እንደምታስተምር ስለ አንተ ተነግሯቸዋል። መምጣትህን መስማታቸው የማይቀር ነውና እንግዲህ ምን እናድርግ? ስለዚህ የምንልህን አድርግ። ስእለት ያለባቸው አራት ሰዎች በእኛ ዘንድ አሉ፤ እነዚህን ሰዎች ይዘህ ከእነርሱ ጋራ የመንጻቱን ሥርዐት ፈጽም፤ ራሳቸውንም እንዲላጩ የሚጠየቀውን ገንዘቡን ክፈልላቸው፤ በዚህም ስለ አንተ የተነገራቸው ሰዎች ሁሉ የሰሙት እውነት እንዳልሆነና አንተ ራስህ ሕጉን ጠብቀህ የምትኖር መሆንህን ያውቃሉ። ከአሕዛብ ወገን ያመኑትን በተመለከተ ግን ለጣዖት የተሠዋ ምግብ፣ ደምና ታንቆ የሞተ እንስሳ ሥጋ እንዳይበሉ፣ ደግሞም ከዝሙት ርኩሰት ራሳቸውን እንዲጠብቁ ወስነን ጽፈንላቸዋል።” ጳውሎስም በማግስቱም ሰዎቹን ይዞ ሄደ፤ ዐብሯቸውም የመንጻቱን ሥርዐት ፈጸመ። ከዚያም የመንጻቱ ሥርዐት መቼ እንደሚያበቃና የእያንዳንዳቸውም መሥዋዕት መቼ እንደሚቀርብ ለማስታወቅ ወደ ቤተ መቅደስ ገባ። ሰባቱ ቀንም ሊፈጸም ሲቃረብ፣ ከእስያ አውራጃ የመጡት አይሁድ ጳውሎስን በቤተ መቅደስ ባዩት ጊዜ፣ ሕዝቡን ሁሉ አነሣሥተው ያዙት፤ እንዲህም እያሉ ጮኹ፤ “የእስራኤል ሰዎች ሆይ፤ ርዱን! ሕዝባችንንና ሕጋችንን እንዲሁም ይህን ስፍራ በማጥላላት በደረሰበት ስፍራ የሚገኙትን ሰዎች ሁሉ የሚያስተምረው ሰው ይህ ነው፤ ከዚህም በላይ ግሪኮችን ወደ ቤተ መቅደስ እያስገባ ይህን የተቀደሰ ስፍራ የሚያረክሰው እርሱ ነው።” ይህንም ያሉት ቀደም ሲል፣ የኤፌሶኑን ሰው ጥሮፊሞስን ከጳውሎስ ጋራ በከተማው ውስጥ ስላዩት፣ ጳውሎስ እርሱንም ወደ ቤተ መቅደስ ይዞ የገባ ስለ መሰላቸው ነበር። ከተማው በሙሉ ታወከ፤ ሕዝቡም ከየአቅጣጫው እየተሯሯጡ መጡ፤ ጳውሎስንም ይዘው እየጐተቱት ከቤተ መቅደሱ ግቢ አወጡት፤ በሮቹም ወዲያውኑ ተዘጉ። ሊገድሉት ሲፈልጉም የኢየሩሳሌም ከተማ ፍጹም ታወከች፤ ወሬውም ለሮማ ጦር አዛዥ ደረሰው። እርሱም ወዲያው አንዳንድ የጦር መኰንኖችንና ወታደሮችን ይዞ እየሮጠ ወደ እነርሱ ወረደ፤ እነርሱም መኰንኖቹንና ወታደሮቹን ባዩ ጊዜ ጳውሎስን መደብደብ ተዉ። የጦር አዛዡም ቀርቦ ያዘው፤ በሁለት ሰንሰለትም እንዲታሰር ትእዛዝ ሰጠ፤ ከዚያም ማን መሆኑንና ምን እንዳደረገ ጠየቀ። ሕዝቡም ከፊሉ አንድ ነገር ሲናገር፣ ከፊሉ ደግሞ ሌላ ይናገር ነበር፤ ከጫጫታው የተነሣም አዛዡ ምንም ነገር ሊሰማ አልቻለም፤ ስለዚህ ጳውሎስ ወደ ጦር ሰፈር እንዲወሰድ አዘዘ። ከሕዝቡ ሁካታ የተነሣ፣ ጳውሎስ ወደ መውጫው ደረጃ ሲደርስ ወታደሮቹ ይሸከሙት ዘንድ ግድ ሆነባቸው። ከኋላ የተከተለውም ሕዝብ፣ “አስወግደው!” እያለ ይጮኽ ነበር።
ሐዋርያት ሥራ 21 ያንብቡ
ያዳምጡ ሐዋርያት ሥራ 21
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ሐዋርያት ሥራ 21:18-36
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች