በመንፈቀ ሌሊትም ጳውሎስና ሲላስ ጸለዩ፤ እግዚአብሔርንም በዜማ አመሰገኑት፤ እስረኞቹም ይሰሙአቸው ነበር። ድንገትም ታላቅ ንውጽውጽታ ሆነ፤ የወህኒ ቤቱ መሠረትም ተናወጠ፤ በሮችም ሁሉ ያንጊዜ ተከፈቱ፤ የሁሉም እግር ብረቶቻቸው እየወለቁ ወደቁ። የወህኒ ቤቱ ጠባቂም ከእንቅልፉ በነቃ ጊዜ በሮች ሁሉ ተከፍተው አየ፤ ሰይፉንም መዝዞ ራሱን ሊገድል ወደደ፤ እስረኞቹ ያመለጡት መስሎት ነበርና። ጳውሎስም፥ “በራስህ ክፉ ነገር አታድርግ፤ ሁላችንም ከዚህ አለን” ብሎ በታላቅ ቃል ጮኸ። መብራት አምጥቶም እየተንቀጠቀጠ ወደ ውስጥ ሄደና ለጳውሎስና ለሲላስ ወድቆ ሰገደ። ወደ ውጭም አውጥቶ “ጌቶች፥ እድን ዘንድ ምን ላድርግ?” አላቸው። እነርሱም፥ “በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ እመን፤ አንተና ቤተ ሰብህም ሁሉ ትድናላችሁ” አሉት። የእግዚአብሔርንም ቃል ለእርሱና በቤቱ ላሉት ሁሉ ነገሩአቸው። ወዲያውኑም በሌሊት ወስዶ ቍስላቸውን አጠበላቸው፤ እርሱም በዚያው ጊዜ ከቤተ ሰቡ ሁሉ ጋር ተጠመቀ። ወደ ቤቱም አግብቶ ማዕድ አቀረበላቸው፤ በጌታችን ስለ አመነም እርሱ ከቤተ ሰቡ ጋር ደስ አለው። በነጋ ጊዜም፥ ገዢዎቹ፥ “እነዚያን ሰዎች ፈትታችሁ ልቀቋቸው” ብለው ብላቴኖቻቸውን ላኩ። የወህኒ ቤቱ ጠባቂም በሰማ ጊዜ ሄዶ ገዢዎቹ “ይፈቱ” ብለው እንደ ላኩ ይህን ነገር ለጳውሎስና ለሲላስ ነገራቸው፤ “አሁንም ውጡና በሰላም ሂዱ” አላቸው። ጳውሎስ ግን፥ “እኛ የሮም ሰዎች ስንሆን፥ ያለ ፍርድ በአደባባይ ገረፉን፤ አሰሩንም፤ አሁንም በስውር ሊያወጡን ይሻሉ፤ አይሆንም፥ ራሳቸው መጥተው ያውጡን” አላቸው። ብላቴኖቻቸውም ሄደው ይህንን ነገር ለገዢዎቹ ነገሩአቸው፤ የሮም ሰዎች መሆናቸውንም ሰምተው ደነገጡ። መጥተውም ከከተማቸው እንዲወጡ ማለዱአቸው። ከወኅኒ ቤቱም ከወጡ በኋላ ወደ ልድያ ቤት ገብተው ወንድሞችን አገኙ፤ አጽናንተዋቸውም ሔዱ።
የሐዋርያት ሥራ 16 ያንብቡ
ያዳምጡ የሐዋርያት ሥራ 16
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የሐዋርያት ሥራ 16:25-40
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች