የሐዋርያት ሥራ 16:25-40

የሐዋርያት ሥራ 16:25-40 አማ05

ወደ እኩለ ሌሊት ገደማ ጳውሎስና ሲላስ በጸሎትና በመዝሙር እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር፤ ሌሎችም እስረኞች ያዳምጡአቸው ነበር። በድንገት የወህኒ ቤቱ መሠረት እስኪናጋ ድረስ ታላቅ የምድር መናወጥ ሆነ፤ በሮቹም ሁሉ በአንድ ጊዜ ተከፈቱ፤ የእያንዳንዱም እስረኛ ሰንሰለት ተፈታ። ጠባቂው ከእንቅልፉ ነቅቶ የወህኒ ቤቱ በሮች ተከፍተው ባየ ጊዜ እስረኞቹ ያመለጡ መስሎት ራሱን ሊገድል ሰይፉን መዘዘ። ነገር ግን ጳውሎስ፥ “ሁላችንም እዚህ ነን! ስለዚህ በራስህ ላይ ጒዳት አታድርስ!” ሲል በታላቅ ድምፅ ጮኸ። በዚህ ጊዜ ጠባቂው መብራት አስመጥቶ እየሮጠ ወደ ውስጥ ገባ፤ እየተንቀጠቀጠም በጳውሎስና በሲላስ እግር ሥር በግንባሩ ተደፋ። ወደ ውጪም አወጣቸውና “ጌቶቼ ሆይ! ለመዳን ምን ማድረግ ይገባኛል?” አላቸው። እነርሱም “በጌታ በኢየሱስ እመን፤ ትድናለህ፤ ቤተሰቦችህም ይድናሉ” አሉት። የጌታንም ቃል ለእርሱና በእርሱ ቤት ላሉትም ሁሉ ተናገሩ። በዚያኑ ሰዓት በሌሊት የወህኒ ቤቱ ጠባቂ ወሰዳቸውና ቊስላቸውን አጠበላቸው፤ ወዲያውኑ እርሱና ቤተሰቡ በሙሉ ተጠመቁ። ከዚህ በኋላ ጳውሎስንና ሲላስን ወደ ቤቱ ወስዶ ምግብ አቀረበላቸው፤ በእግዚአብሔር ስላመነም ከቤተ ሰቡ ሁሉ ጋር ደስ አለው። በነጋም ጊዜ ባለሥልጣኖቹ “እነዚያ ሰዎች ይለቀቁ” ብለው ፖሊሶችን ላኩ። የወህኒ ቤት ጠባቂውም “እናንተ እንድትለቀቁ ባለሥልጣኖቹ ሰው ልከዋልና እንግዲህ ወጥታችሁ በሰላም ሂዱ” ሲል ለጳውሎስ ነገረው። ጳውሎስ ግን “እኛ የሮም ዜጋዎች ስንሆን ያለ ፍርድ በአደባባይ ገርፈው ወደ ወህኒ አስገብተውናል። አሁን ደግሞ ከወህኒ ቤት በስውር እንድንወጣ ያደርጋሉን? አይሆንም! እነርሱ ራሳቸው መጥተው ያስወጡን!” ሲል መለሰ። ፖሊሶቹ ይህን ነገር ለባለሥልጣኖቹ ነገሩ፤ ባለሥልጣኖቹም ጳውሎስና ሲላስ የሮም ዜጋዎች መሆናቸውን ባወቁ ጊዜ ፈሩ። ስለዚህ መጥተው ይቅርታ ጠየቁአቸውና ከወህኒ ቤት አስወጡአቸው፤ ከከተማውም እንዲሄዱ ለመኑአቸው። ጳውሎስና ሲላስም ከወህኒ ቤት ወጥተው ወደ ልድያ ቤት ገቡ፤ እዚያም ወንድሞችን አግኝተው፥ አጽናኑአቸውና ከተማውን ለቀው ሄዱ።