መጽሐፈ መቃብያን ሣልስ 8
8
1ኢዮብ በእግዚአብሔር አመነ፤ ፈጣሪው እግዚአብሔርን ማመስገንን ቸል አላለምና የአዳም ልጆች ጠላት ዲያብሎስ ካመጣበት መከራውም ሁሉ አዳነው፤ በደረሰበትም መከራ ልቡን አላሳዘነም፤ ነገር ግን “እግዚአብሔር ሰጠ፤ እግዚአብሔርም ነሳ፤ እግዚአብሔርም እንደ ወደደ ሆነ፤ በሁሉም በሰማይና በምድር የእግዚአብሔር ስሙ የተመሰገነ ይሁን” አለ። 2እግዚአብሔርም የኢዮብ ልቡ ንጽሕት እንደ ሆነች ባየው ጊዜ፥ እግዚአብሔር በብዙ ክብር ተቀበለው። 3ከቀደመ ገንዘቡ ይልቅ የሚበዛ ገንዘብንም ሰጠው፤ እጅግ ትዕግሥተኛ ሆኗልና፥ የደረሰበትን መከራ ሁሉ ስለ መታገሡ ከቍስሉ ፈወሰው። 4እንዲሁም እናንተ ወደ እናንተ ከሚላኩ ጠላቶች ብትታገሡ ብፁዓን ትሆናላችሁ። 5ታገሡ፤ እግዚአብሔር ከሚጠሏችሁ ሰዎች ለእናንተና ከእናንተም በኋላ ለልጆቻችሁና ለልጅ ልጆቻችሁ መጠጊያ ይሆናችሁ ዘንድ ከመጣባችሁ መከራ የተነሣ ልቡናችሁን አታሳዝኑ፤ 6እመኑት፥ እርሱም መጠጊያ ይሆናችኋል፤ ጥሩት፥ ይሰማችኋልም፤ ተስፋ አድርጉት፥ እርሱም ይቅር ይላችኋል፤ ለምኑት፥ እርሱም አባት ይሆናችኋል። 7አስቴርንና መርዶክዮስን፥ ዮዲትንና ጌዴዎንንም፥ ባርቅንና ዲቦራንም፥ ሶምሶምንና ዮፍታሔንም፥ 8በእግዚአብሔር ለማመን የጨከኑ ጠላቶቻቸውም ድል ያልነሷቸው እንደነርሱ ያሉ ሌሎችንም አስቡ። 9እግዚአብሔር እውነተኛ ነውና፥ ፊት አይቶም አያዳላምና በእነርሱ ላይ ክፉ ያደርጉ ዘንድ የወደዱ ክፉውን ተቀበሉ፤ የሚፈሩትንና ጽድቅን የሚያደርጉትን ሁሉ ግን ነፍሶቻቸውን ይጠብቃል፤ ክብርንና ባለሟልነትንም ይሰጣቸዋል። 10በመግባታቸውና በመውጣታቸው፥ በሞታቸውና በሕይወታቸው፤ በመቀመጣቸውና በመነሣታቸውም ደስ ያሰኛቸዋል፤ እርሱ ያድናልና፥ ይገድላልምና። 11እርሱ ይገርፋል፤ ይቅርም ይላል። 12እርሱ ያደኸያል፤ ባለ ጸጋም ያደርጋል፤ እርሱ ያዋርዳል፥ ያከብራልም።
Currently Selected:
መጽሐፈ መቃብያን ሣልስ 8: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ