ኤልሳዕም፥ “የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ነገ በዚህ ጊዜ በሰማርያ በር፥ ሁለት መስፈሪያ ገብስ በአንድ ሰቅል አንድ መስፈሪያ መልካም ዱቄትም በአንድ ሰቅል ይሸመታል” አለው። ንጉሡም በእጁ ተደግፎት የሚቆም የነበረ ያ ብላቴና ለኤልሳዕ መልሶ፥ “እነሆ፥ እግዚአብሔር በሰማይ የእህል ሿሿቴ ቢያደርግ ይህ ነገር ይሆናልን?” አለው። ኤልሳዕም፥ “እነሆ፥ በዐይኖችህ ታየዋለህ፤ ከዚያ ግን አትቀምስም” አለ። በከተማዋም በር አራት ለምጻሞች ሰዎች ነበሩ፤ እርስ በርሳቸውም፥ “እስክንሞት ድረስ በዚህ ለምን እንቀመጣለን? ወደ ከተማ ብንገባ ራብ በከተማ አለና፥ በዚያ እንሞታለን፤ በዚህም ብንቀመጥ እንሞታለን። እንግዲህ ኑ፥ ወደ ሶርያውያን ሰፈር እንሂድ፤ በሕይወት ቢያኖሩን እንኖራለን፤ ቢገድሉንም እንሞታለን” ተባባሉ። በጨለማም ወደ ሶርያውያን ሰፈር ይሄዱ ዘንድ ተነሡ፤ ወደ ሶርያውያንም ሰፈር መጀመሪያ ዳርቻ በመጡ ጊዜ፥ እነሆ፥ በዚያ ማንም ሰው አልነበረም። እግዚአብሔርም ለሶርያውያን የሰረገላ ድምፅ፥ የፈረስ ድምፅና የብዙ ጭፍራ ድምፅ አሰምቶአቸዋልና፥ እርስ በርሳቸው “እነሆ፥ የእስራኤል ንጉሥ ይከቡን ዘንድ የኬጤዎናውያንንና የግብፃውያንን ነገሥት ቀጥሮ አምጥቶብናል” ይባባሉ ነበር። ስለዚህም ተነሥተው በጨለማ ሸሹ፤ ድንኳኖቻቸውንና ፈረሶቻቸውን፥ አህዮቻቸውንና ሰፈሩን እንዳለ ትተው ነፍሳቸውን ያድኑ ዘንድ ሸሹ። እነዚያም ለምጻሞች ወደ ሰፈሩ መጀመሪያ ዳርቻ በመጡ ጊዜ ወደ አንድ ድንኳን ገብተው በሉ፤ ጠጡም፤ ከዚያም ወርቅና ብር ልብስም ወሰዱ፤ ሄደውም ሸሸጉት፤ ተመልሰውም ወደ ሌላ ድንኳን ገቡ፤ ከዚያም ደግሞ ወስደው ሸሸጉ። ከዚያም ወዲያ እርስ በርሳቸው፥ “መልካም አላደረግንም፤ ዛሬ የመልካም ምሥራች ቀን ነው፤ እኛ ዝም ብለናል፤ እስኪነጋም ድረስ ብንቆይ በደለኞች እንሆናለን፤ ኑ፥ እንሂድ፤ ለንጉሥ ቤተሰብም እንናገር” ተባባሉ። ገብተውም በከተማው በር ጮኹ፤ እንዲህም ብለው ተናገሩ፥ “ወደ ሶርያውያን ሰፈር ገባን፤ እነሆም፥ ፈረሶችና አህዮች ታስረው፥ ድንኳኖችም ተተክለው ነበር እንጂ ያገኘነው አልነበረም፤ የሰውም ድምፅ አልነበረም።” የደጁም ጠባቂዎች ለንጉሡ ይነግሩ ዘንድ ወደ ውስጥ ገቡ፤ ለንጉሡም ቤት አወሩ። ንጉሡም በሌሊት ተነሥቶ ብላቴኖቹን፥ “ሶርያውያን ያደረጉብንን እነግራችኋለሁ፤ እንደ ተራብን ያውቃሉ፤ ስለዚህ፦ ከከተማይቱ በወጡ ጊዜ በሕይወታቸው እንይዛቸዋለን፤ ወደ ከተማም እንገባለን ብለው በሜዳ ይሸሸጉ ዘንድ ከሰፈሩ ወጥተዋል” አላቸው። ከብላቴኖቹም አንዱ መልሶ፥ “እዚህ ከቀሩት ፈረሶች አምስት ይውሰዱ፤ እነሆ፥ እነርሱ በቀሩት በእስራኤል ቍጥር ናቸው፥ እንስደድና ይዩ” አለ። ሁለት ፈረሰኞችንም ወሰዱ፤ የእስራኤል ንጉሥም፥ “ሄዳችሁ እዩ” ብሎ የሶርያውያንን ንጉሥ ይከተሉት ዘንድ ላከ። በኋላቸውም እስከ ዮርዳኖስ ድረስ ተከትለዋቸው ሄዱ፤ እነሆም፥ ሶርያውያን ሲሸሹ የጣሉት ልብስና ዕቃ መንገዱን ሁሉ ሞልቶ አገኙ። እነዚያ መልእክተኞችም ተመልሰው ለእስራኤል ንጉሥ ነገሩት። ሕዝቡም ወጥቶ የሶርያውያንን ሰፈር በዘበዘ፤ እንደ እግዚአብሔርም ቃል አንድ መስፈሪያ መልካም ዱቄት በአንድ ሰቅል፥ ሁለት መስፈሪያ ገብስም በአንድ ሰቅል ተሸመተ። ንጉሡም ያን እጁን ይደግፈው የነበረውን ብላቴና በሩን ይጠብቅ ዘንድ አቆመው። ሕዝቡም በበሩ ረገጠው፥ መልእክተኛው ወደ እርሱ በወረደ ጊዜ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ተናገረውም ሞተ። ኤልሳዕም ለንጉሡ፥ “ነገ በዚህ ጊዜ በሰማርያ በር ሁለት መስፈሪያ ገብስ በአንድ ሰቅል፥ አንድ መስፈሪያ መልካም ዱቄትም በአንድ ሰቅል፥ ይሸመታል” ብሎ እንደ ተናገረው ነገር እንዲሁ ሆነ። ያም ሎሌ ለኤልሳዕ መልሶ፥ “እነሆ፥ እግዚአብሔር በሰማይ የእህል ሿሿቴ ቢያወርድ ይህ ነገር ይሆናልን?” ብሎ ነበር፤ ኤልሳዕም፥ “እነሆ፥ በዐይኖችህ ታየዋለህ፥ ከዚያም አትቀምስም” ብሎት ነበር። እንዲሁም ሆነ፤ ሕዝቡም በበሩ ረገጠውና ሞተ።
መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 7 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 7:1-20
5 ቀናት
በእምነት ለመቆም፣ በእምነት የተሞሉ ፀሎቶችን ለመጸለይ እና በሕይወትዎና በሌሎችም ሕይወት ውስጥ ለመንግሥቱ አስገራሚ ነገሮችን ለማከናወን እግዚአብሔር ሊጠቀምብዎት ይችላል። የሚቅጥሉትን 5 ቀናት ይህን እምነቶን በማሳደግ ያሳልፉ።
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች