ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 7:1-20

ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 7:1-20 አማ05

ኤልሳዕም “እግዚአብሔር የሚለውን ስማ! ነገ ይህን ጊዜ በሰማርያ ሦስት ኪሎ ምርጥ ስንዴ ወይም ስድስት ኪሎ ገብስ በአንድ ጥሬ ብር ይሸመታል” ሲል መለሰለት። በዚህ ጊዜ የንጉሡ የቅርብ ባለሟል የሆነ አገልጋዩ ኤልሳዕን፥ “እግዚአብሔር ራሱ የሰማይ መስኮቶችን ከፍቶ እህልን እንደ ዝናብ ቢያዘንብ እንኳ ይህ ሊሆን ከቶ አይችልም!” ሲል በመጠራጠር ተናገረ። ኤልሳዕም “ያን እህል በዐይንህ ታያለህ፤ ነገር ግን ከእርሱ ምንም ነገር አትቀምስም!” አለው። ሰውነታቸው የቆዳ በሽታ የያዛቸው አራት ሰዎች ከሰማርያ ቅጽር በር ውጪ ነበሩ፤ እነርሱም እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፤ “እስክንሞት ድረስ ስለምን በዚህ እንቈያለን? ወደ ከተማይቱ መግባት ምንም ጥቅም የለውም፤ እዚያ ከገባን በራብ እንሞታለን፤ እዚህም ብንቀር ከመሞት አንድንም፤ ስለዚህ ተነሥተን ወደ ሶርያውያን ሰፈር እንሂድ፤ እነርሱም ቢሆኑ ከመግደል የከፋ ሌላ ምንም ነገር ሊያደርጉብን አይችሉም፤ ምናልባትም ሕይወታችንን ያተርፉ ይሆናል።” ከዚህም በኋላ ቀኑ ሊመሽ ሲል ወደ ሶርያውያን ሰፈር ሄዱ፤ ነገር ግን እዚያ ሲደርሱ ማንም ሰው አልነበረም፤ ይህም የሆነበት ምክንያት እግዚአብሔር ሶርያውያንን በፈረሶችና በሠረገሎች የታጀበ የብዙ ሠራዊት ግሥጋሤ የሚመስል ድምፅ አሰምቶአቸው ስለ ነበር ነው፤ ይኸውም ሶርያውያን እንዳሰቡት የእስራኤል ንጉሥ የሒታውያንና የግብጽ ነገሥታትን ከነሠራዊቶቻቸው ቀጥሮ አደጋ ሊጥልባቸው የመጣ መስሎአቸው ነበር። ስለዚህም በዚያን ቀን ምሽት ሶርያውያን ድንኳኖቻቸውን፥ ፈረሶቻቸውንና አህዮቻቸውን በጠቅላላም ሰፈራቸውን ሁሉ እንዳለ ትተው ሕይወታቸውን ለማትረፍ ሸሽተው ሄደዋል። አራቱ ሰዎች ወደ ሶርያውያን ሰፈር ዳርቻ በደረሱ ጊዜ ወደ አንድ ድንኳን ውስጥ ገቡ፤ በዚያም ያገኙትን ነገር ሁሉ በልተውና ጠጥተው ያገኙትን ብር፥ ወርቅና ልብስ ይዘው ሄደው ደበቁ፤ እንደገናም ተመልሰው ወደ ሌላ ድንኳን በመግባት እንደዚያው አደረጉ፤ ከዚህም በኋላ እርስ በርሳቸው እንዲህ ተባባሉ፥ “መልካም አላደረግንም! እነሆ፥ ዛሬ ታላቅ የምሥራች አግኝተናል፤ ይህንንም መልካም ዜና ደብቀን ልናስቀር አይገባንም! ይህን የምሥራች ሳንነግር እስኪነጋ ብንቈይ በእርግጥ ቅጣት ይደርስብናል፤ ስለዚህም አሁኑኑ ሄደን ለንጉሡ የጦር መኰንኖች እንንገር!” ከዚያም በኋላ ከሶርያውያን ሰፈር በመነሣት ወደ ሰማርያ ተመልሰው ሄዱ፤ እዚያም እንደ ደረሱ የከተማይቱን ቅጽር በር ዘበኞች ጠርተው “ወደ ሶርያውያን ሰፈር ሄደን ነበር፤ ነገር ግን ምንም ያየነው ሰው ወይም የሰማነው ድምፅ እንኳ የለም፤ ፈረሶችና አህዮች እንደ ታሰሩ ናቸው፤ ድንኳኖቹም ሶርያውያን ትተዋቸው ስለ ሄዱ ባዶአቸውን ናቸው” ሲሉ ነገሩአቸው። ዘብ ጠባቂዎቹም ወሬውን ስለ ነዙት እስከ ቤተ መንግሥት ድረስ ተሰማ። ጊዜውም ገና ሌሊት ነበር፤ ንጉሡ ግን ከመኝታው ተነሥቶ ባለሟሎቹ የሆኑትን ባለሥልጣኖች እንዲህ አላቸው፤ “የሶርያውያንን ዕቅድ ልንገራችሁ! እነርሱ በዚህ ስላለው ራብ ያውቃሉ፤ ስለዚህ ሰፈራቸውን ለቀው በገጠር ለመሸሸግ ሄደዋል፤ እኛም ምግብ ፍለጋ ብንወጣ ከነሕይወታችን ማርከው ከተማችንን ይወስዳሉ።” ከባለሟሎቹም አንዱ “በዚህች ከተማ ውስጥ የተረፈው ሕዝብ ከዚህ በፊት እንደ ሞቱት ሰዎች ሁሉ ከሞት የሚያመልጥ አይደለም፤ ስለዚህ የሆነውን ነገር ማወቅ እንድንችል ጥቂት ሰዎችን መርጠን ከሞት ከተረፉት አምስት ፈረሶች ጋር እንላክ” ሲል ሐሳብ አቀረበ። እነርሱም ጥቂት ሰዎችን መረጡ፤ ንጉሡም እነዚያን ሰዎች በሁለት ሠረገሎች እንዲቀመጡ አድርጎ በሶርያውያን ሠራዊት ላይ የደረሰውን ሁኔታ መርምረው እንዲመለሱ መመሪያ በመስጠት ላካቸው። ሰዎቹም ከዚያ ተነሥተው እስከ ዮርዳኖስ ወንዝ ድረስ ዘልቀው ሄዱ፤ በየመንገዱም ሶርያውያን ሲሸሹ ጥለውት የሄዱትን ልብስና መሣሪያ ሁሉ አዩ፤ ከዚያም በኋላ ተመልሰው መጥተው ይህን ሁሉ ለንጉሡ ነገሩ። ሕዝቡም በፍጥነት እየተራወጠ ወጥቶ የሶርያን ሰፈር ዘረፈ፤ እግዚአብሔር አስቀድሞ በተናገረውም መሠረት ሦስት ኪሎ ምርጥ ስንዴ ወይም ስድስት ኪሎ ገብስ በአንድ ጥሬ ብር ተሸመተ። በዚህም ጊዜ የእስራኤል ንጉሥ የከተማይቱ ቅጽር በር የቅርብ ባለሟሉ በሆነው አገልጋዩ ኀላፊነት ሥር እንዲጠበቅ አድርጎ ነበር፤ ነገር ግን ያንን አገልጋይ ሕዝቡ ስለ ረጋገጠው በዚያ ሞተ፤ ይህም የሆነው ንጉሡ ኤልሳዕን ለማነጋገር በሄደ ጊዜ ኤልሳዕ በዚያ አገልጋይ ላይ የተናገረበት የትንቢት ቃል ስለ ተፈጸመ ነው። በዚያን ጊዜ ኤልሳዕ ለንጉሡ “በነገው ዕለት በሰማርያ ከተማ ሦስት ኪሎ ምርጥ ስንዴ ወይም ስድስት ኪሎ ገብስ በአንድ ጥሬ ብር ይሸመታል” ብሎ ነግሮት ነበር፤ ለዚህም ቃል ያ አገልጋዩ የሰጠው መልስ “እግዚአብሔር ራሱ የሰማይ መስኮቶችን ከፍቶ እህልን እንደ ዝናብ ቢያዘንብ እንኳ ይህ ሊሆን ከቶ አይችልም!” የሚል ነበር። ኤልሳዕም “ያን እህል በዐይንህ ታያለህ፤ ነገር ግን ከእርሱ ምንም ነገር አትቀምስም” ብሎት ነበር። እንግዲህ ያ አገልጋይ በሰማርያ ከተማ ቅጽር በር ላይ ሕዝብ ረጋግጦት ለመሞት የበቃው ይህ ትንቢት ስለ ተፈጸመበት ነበር።