መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 7
7
1ኤልሳዕም፥ “የእግዚአብሔርን ቃል ስማ፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ ነገ በዚህ ጊዜ በሰማርያ በር፥ ሁለት መስፈሪያ ገብስ በአንድ ሰቅል አንድ መስፈሪያ መልካም ዱቄትም በአንድ ሰቅል ይሸመታል” አለው። 2ንጉሡም በእጁ ተደግፎት የሚቆም የነበረ ያ ብላቴና ለኤልሳዕ መልሶ፥ “እነሆ፥ እግዚአብሔር በሰማይ የእህል ሿሿቴ ቢያደርግ ይህ ነገር ይሆናልን?” አለው። ኤልሳዕም፥ “እነሆ፥ በዐይኖችህ ታየዋለህ፤ ከዚያ ግን አትቀምስም” አለ።
3በከተማዋም በር አራት ለምጻሞች ሰዎች ነበሩ፤ እርስ በርሳቸውም፥ “እስክንሞት ድረስ በዚህ ለምን እንቀመጣለን? 4ወደ ከተማ ብንገባ ራብ በከተማ አለና፥ በዚያ እንሞታለን፤ በዚህም ብንቀመጥ እንሞታለን። እንግዲህ ኑ፥ ወደ ሶርያውያን ሰፈር እንሂድ፤ በሕይወት ቢያኖሩን እንኖራለን፤ ቢገድሉንም እንሞታለን” ተባባሉ። 5በጨለማም ወደ ሶርያውያን ሰፈር ይሄዱ ዘንድ ተነሡ፤ ወደ ሶርያውያንም ሰፈር መጀመሪያ ዳርቻ በመጡ ጊዜ፥ እነሆ፥ በዚያ ማንም ሰው አልነበረም። 6እግዚአብሔርም ለሶርያውያን የሰረገላ ድምፅ፥ የፈረስ ድምፅና የብዙ ጭፍራ ድምፅ አሰምቶአቸዋልና፥ እርስ በርሳቸው “እነሆ፥ የእስራኤል ንጉሥ ይከቡን ዘንድ የኬጤዎናውያንንና የግብፃውያንን ነገሥት ቀጥሮ አምጥቶብናል” ይባባሉ ነበር። 7ስለዚህም ተነሥተው በጨለማ ሸሹ፤ ድንኳኖቻቸውንና ፈረሶቻቸውን፥ አህዮቻቸውንና ሰፈሩን እንዳለ ትተው ነፍሳቸውን ያድኑ ዘንድ ሸሹ። 8እነዚያም ለምጻሞች ወደ ሰፈሩ መጀመሪያ ዳርቻ በመጡ ጊዜ ወደ አንድ ድንኳን ገብተው በሉ፤ ጠጡም፤ ከዚያም ወርቅና ብር ልብስም ወሰዱ፤ ሄደውም ሸሸጉት፤ ተመልሰውም ወደ ሌላ ድንኳን ገቡ፤ ከዚያም ደግሞ ወስደው ሸሸጉ።
9ከዚያም ወዲያ እርስ በርሳቸው፥ “መልካም አላደረግንም፤ ዛሬ የመልካም ምሥራች ቀን ነው፤ እኛ ዝም ብለናል፤ እስኪነጋም ድረስ ብንቆይ በደለኞች እንሆናለን፤ ኑ፥ እንሂድ፤ ለንጉሥ ቤተሰብም እንናገር” ተባባሉ። 10ገብተውም በከተማው በር ጮኹ፤ እንዲህም ብለው ተናገሩ፥ “ወደ ሶርያውያን ሰፈር ገባን፤ እነሆም፥ ፈረሶችና አህዮች ታስረው፥ ድንኳኖችም ተተክለው ነበር እንጂ ያገኘነው አልነበረም፤ የሰውም ድምፅ አልነበረም።” 11የደጁም ጠባቂዎች ለንጉሡ ይነግሩ ዘንድ ወደ ውስጥ ገቡ፤ ለንጉሡም ቤት አወሩ። 12ንጉሡም በሌሊት ተነሥቶ ብላቴኖቹን፥ “ሶርያውያን ያደረጉብንን እነግራችኋለሁ፤ እንደ ተራብን ያውቃሉ፤ ስለዚህ፦ ከከተማይቱ በወጡ ጊዜ በሕይወታቸው እንይዛቸዋለን፤ ወደ ከተማም እንገባለን ብለው በሜዳ ይሸሸጉ ዘንድ ከሰፈሩ ወጥተዋል” አላቸው። 13ከብላቴኖቹም አንዱ መልሶ፥ “እዚህ ከቀሩት ፈረሶች አምስት ይውሰዱ፤ እነሆ፥ እነርሱ በቀሩት በእስራኤል ቍጥር ናቸው፥ እንስደድና ይዩ” አለ። 14ሁለት ፈረሰኞችንም ወሰዱ፤ የእስራኤል ንጉሥም፥ “ሄዳችሁ እዩ” ብሎ የሶርያውያንን ንጉሥ ይከተሉት ዘንድ ላከ። 15በኋላቸውም እስከ ዮርዳኖስ ድረስ ተከትለዋቸው ሄዱ፤ እነሆም፥ ሶርያውያን ሲሸሹ የጣሉት ልብስና ዕቃ መንገዱን ሁሉ ሞልቶ አገኙ። እነዚያ መልእክተኞችም ተመልሰው ለእስራኤል ንጉሥ ነገሩት።
16ሕዝቡም ወጥቶ የሶርያውያንን ሰፈር በዘበዘ፤ እንደ እግዚአብሔርም ቃል አንድ መስፈሪያ መልካም ዱቄት በአንድ ሰቅል፥ ሁለት መስፈሪያ ገብስም በአንድ ሰቅል ተሸመተ። 17ንጉሡም ያን እጁን ይደግፈው የነበረውን ብላቴና በሩን ይጠብቅ ዘንድ አቆመው። ሕዝቡም በበሩ ረገጠው፥ መልእክተኛው ወደ እርሱ በወረደ ጊዜ የእግዚአብሔር ሰው እንደ ተናገረውም ሞተ። 18ኤልሳዕም ለንጉሡ፥ “ነገ በዚህ ጊዜ በሰማርያ በር ሁለት መስፈሪያ ገብስ በአንድ ሰቅል፥ አንድ መስፈሪያ መልካም ዱቄትም በአንድ ሰቅል፥ ይሸመታል” ብሎ እንደ ተናገረው ነገር እንዲሁ ሆነ። 19ያም ሎሌ ለኤልሳዕ መልሶ፥ “እነሆ፥ እግዚአብሔር በሰማይ የእህል ሿሿቴ ቢያወርድ ይህ ነገር ይሆናልን?” ብሎ ነበር፤ ኤልሳዕም፥ “እነሆ፥ በዐይኖችህ ታየዋለህ፥ ከዚያም አትቀምስም” ብሎት ነበር። 20እንዲሁም ሆነ፤ ሕዝቡም በበሩ ረገጠውና ሞተ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 7: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ