መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 6
6
ኤልሳዕ ያደረገው ተአምር
1የነቢያትም ልጆች ኤልሳዕን፥ “እነሆ፥ በፊትህ የምናድርበት ቤት ጠብቦናል። 2ወደ ዮርዳኖስም እንሂድ፤ ከእኛም እያንዳንዱ ከዚያ ምሰሶ ያምጣ፥ የምናድርበትም ቤት እንሥራ፥” አሉት፤ እርሱም፥ “ሂዱ” አለ። 3ከእነርሱም አንዱ፥ “አንተ ደግሞ ከእኛ ከአገልጋዮችህ ጋር ለመሄድ ና” አለ። ኤልሳዕም፥ “እሽ እኔም እመጣለሁ” አለ። 4ከእነርሱም ጋር ሄደ፤ ወደ ዮርዳኖስም በደረሱ ጊዜ እንጨት ቈረጡ። 5ከእነርሱም አንዱ ዛፉን ሲቈርጥ የምሳሩ ብረት ወልቆ ወደ ውኃው ውስጥ ወደቀ፤ እርሱም፥ “ጌታዬ ሆይ፥ ወየው! ወየው! የተዋስሁት ነበር” ብሎ ጮኸ። 6የእግዚአብሔርም ሰው፥ “የወደቀው ወዴት ነው?” አለ፤ ስፍራውንም አሳየው፤ ከእንጨትም ቅርፊት ቀርፎ በዚያ ጣለው፤ ብረቱም ተንሳፈፈ። 7እርሱም፥ “እነሆ፥ ምሳርህ ውሰደው” አለ፤ እጁንም ዘርግቶ ወሰደው።
8የሶርያም ንጉሥ ከእስራኤል ጋር ይዋጋ ነበር፤ ከአገልጋዮቹም ጋር ተማክሮ፥ “በዚህ ስውር ቦታ ተደብቀን እናድራለን።” አላቸው። 9ኤልሳዕም፥ “ሶርያውያን በዚያ ተደብቀዋልና በዚያ ስፍራ እንዳታልፍ ተጠንቀቅ” ብሎ ወደ እስራኤል ንጉሥ ላከ። 10የእስራኤልም ንጉሥ ኤልሳዕ ወደ ነገረው ስፍራ ላከ፤ አንድ ጊዜም ሳይሆን፥ ሁለት ጊዜም ሳይሆን በዚያ ራሱን አዳነ። 11የሶርያም ንጉሥ መንፈስ ስለዚህ እጅግ ተበሳጨች፤ አገልጋዮቹንም ጠርቶ፥ “ለእስራኤል ንጉሥ ማን እንደሚነግረው አትነግሩኝምን?” አላቸው። 12ከአገልጋዮቹም አንዱ፥ “ጌታዬ ሆይ፥ በእስራኤል ሀገር ነቢዩ ኤልሳዕ ያለ አይደለምን? በእልፍኝህ ውስጥ ሆነህ የምትናገረውንና ቃልህን ሁሉ ለእስራኤል ንጉሥ እርሱ ይነግረዋል፤” አለ። 13እርሱም፥ “ልኬ አስይዘው ዘንድ ሄዳችሁ ወዴት እንደ ሆነ ዕወቁ፤” አለ። እነርሱም፥ “እነሆ፥ በዶታይን አለ” ብለው ነገሩት።
14ወደዚያም ፈረሶችንና ሰረገሎችን ብዙም ጭፍራ ላከ፤ በሌሊትም መጥተው ከተማዪቱን ከበቡአት። 15የኤልሳዕም ሎሌ ማለዳ ነቃ፤ ተነሥቶም በወጣ ጊዜ፥ እነሆ፥ በከተማዪቱ ዙሪያ ጭፍሮች ከተማዋን ከብበዋት አየ። ፈረሶችና ሰረገሎችም ነበሩ። ሎሌውም፥ “ጌታዬ ሆይ፥ ወዮ! ምን እናድርግ?” አለው። 16እርሱም፥ “ከእኛ ጋር ያሉት ከእነርሱ ጋር ካሉት ይበልጣሉና አትፍራ” አለው። 17ኤልሳዕም፥ “አቤቱ፥ ያይ ዘንድ ዐይኖቹን፥ እባክህ፥ ግለጥ” ብሎ ጸለየ። እግዚአብሔርም የብላቴናውን ዐይኖች ገለጠ፤ እነሆም፥ የእሳት ፈረሶችና ሰረገሎች በኤልሳዕ ዙሪያ ተራራውን ሞልተውት አየ። 18ወደ እርሱም በወረዱ ጊዜ ኤልሳዕ፥ “አቤቱ፥ እነዚህን ሰዎች አሳውራቸው” ብሎ ወደ እግዚአብሔር ጸለየ። ኤልሳዕም እንደ ተናገረው ቃል አሳወራቸው። 19ኤልሳዕም፥ “መንገዱ በዚህ አይደለም፥ ከተማዪቱም ይህች አይደለችም፤ የምትሹትን ሰው አሳያችሁ ዘንድ ተከተሉኝ” አላቸው፤ ወደ ሰማርያም ወሰዳቸው።
20ወደ ሰማርያም በገቡ ጊዜ ኤልሳዕ፥ “አቤቱ፥ ያዩ ዘንድ የእነዚህን ሰዎች ዐይኖች ግለጥ” አለ፤ እግዚአብሔርም ዐይኖቻቸውን ገለጠ፤ እነርሱም አዩ። እነሆም፥ በሰማርያ መካከል እንዳሉ ዐወቁ። 21የእስራኤልም ንጉሥ ባያቸው ጊዜ ኤልሳዕን፥ “አባቴ ሆይ፥ ልግደላቸውን?” አለው። 22እርሱም፥ “በሰይፍህና በቀስትህ የማረክሃቸውን ግደል እንጂ በሰይፍህና በቀስትህ የማረክሃቸው አይደሉምና አትግደላቸው። ይልቁንስ እንጀራና ውኃ በፊታቸው አቅርብላቸው፤ በልተውና ጠጥተውም ወደ ጌታቸው ይመለሱ” አለው። 23ብዙም መብል አዘጋጀላቸው፤ በበሉና በጠጡ ጊዜም አሰናበታቸው፤ እነርሱም ወደ ጌታቸው ሄዱ። ከዚያም በኋላ የሶርያውያን አደጋ ጣዮች ዳግመኛ ወደ እስራኤል ሀገር አልመጡም።
የሶርያ ንጉሥ ወልደ አዴር ሰማርያን እንደ ከበበ
24ከዚያም በኋላ የሶርያ ንጉሥ ወልደ አዴር ሠራዊቱን ሁሉ ሰበሰበ፤ ወጥቶም ሰማርያን ከበባት፤ በዚያም ተቀመጠ። 25በሰማርያም ታላቅ ራብ ሆኖ ነበር፤ እነሆም፥ የአህያ ራስ በኀምሳ ብር፥ የድርጎ አንድ አራተኛ የሚሆን ኵስሐ ርግብም በአምስት ብር እስኪሽጥ ድረስ ከበቡአት። 26የእስራኤልም ንጉሥ በቅጥር ላይ ሲመላለስ አንዲት ሴት፥ “ጌታዬ ንጉሥ ሆይ፥ ርዳኝ” ብላ ወደ እርሱ ጮኸች። 27እርሱም፥ “እግዚአብሔር ካልረዳሽ እኔ እንዴት እረዳሻለሁ? ከአውድማው ወይስ ከመጭመቂያው ነውን?” አለ። 28ንጉሡም፥ “ምን ሆነሻል?” አላት፤ እርስዋም፥ “ይህች ሴት፦ ዛሬ እንድንበላው ልጅሽን አምጪ፤ ነገም ልጄን እንበላለን አለችኝ። 29ልጄንም ቀቅለን በላነው፤ በማግሥቱም፦ እንድንበላው ልጅሽን አምጪ አልኋት፤ ልጅዋንም ሸሸገችው” ብላ መለሰችለት። 30የእስራኤልም ንጉሥ የሴቲቱን ቃል ሰምቶ ልብሱን ቀደደ፤ በቅጥርም ይመላለስ ነበር፤ ሕዝቡም በስተውስጥ በሥጋው ላይ ለብሶት የነበረውን ማቅ አዩ። 31ንጉሡም፥ “የሣፋጥ ልጅ የኤልሳዕ ራስ ዛሬ በላዩ ያደረ እንደ ሆነ እግዚአብሔር እንዲህ ያድርገኝ እንዲህም ይግደለኝ” አለ።
32ኤልሳዕ ግን በቤቱ ተቀምጦ ነበር፤ ሽማግሌዎችም ከእርሱ ጋር ተቀምጠው ነበር፤ ንጉሡም በፊቱ ከሚቆሙት አንድ ሰው ላከ፤ መልእክተኛውም ገና ሳይደርስ ለሽማግሌዎች፥ “ይህ የነፍሰ ገዳይ ልጅ ራሴን ይቈርጥ ዘንድ እንደ ላከ እዩ፤ መልእክተኛውም በመጣ ጊዜ ደጁን ዘግታችሁ ከልክሉት፤ በደጅም ይቆም ዘንድ ተዉት፤ የጌታው የእግሩ ኮቴ በኋላው ነው” አላቸው። 33ከእነርሱም ጋር ሲነጋገር እነሆ፥ መልእክተኛው ወደ እርሱ ደረሰ፤ እርሱም፥ “እነሆ፥ ይህ ክፉ ነገር ከእግዚአብሔር ዘንድ ነው፥ እግዚአብሔርን ገና እጠብቅ ዘንድ ምንድን ነኝ?” አለ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 6: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ