ከዚህም በኋላ እግዚአብሔር ኤልያስን በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ በሚያወጣው ጊዜ ኤልያስና ኤልሳዕ ከጌልጌላ ተነሥተው ሄዱ። ኤልያስም ኤልሳዕን፥ “እግዚአብሔር ወደ ቤቴል ልኮኛልና በዚሁ ቈይ” አለው። ኤልሳዕም፥ “ሕያው እግዚአብሔርን! ሕያው ነፍስህንም አልለይህም” አለው። ወደ ቤቴልም ደረሱ። በቤቴልም የነበሩ የነቢያት ልጆች ወደ ኤልሳዕ መጥተው፥ “እግዚአብሔር ጌታህን ከአንተ ለይቶ ዛሬ እንደሚወስደው ዐውቀሃልን?” አሉት። እርሱም፥ “አዎን፥ ዐውቄአለሁ፤ ዝም በሉ” አላቸው። ኤልያስም ኤልሳዕን፥ “እግዚአብሔር ወደ ኢያሪኮ ልኮኛልና፥ በዚህ ቈይ” አለው። ኤልሳዕም፥ “ሕያው እግዚአብሔርን! ሕያው ነፍስህንም አልለይህም” አለው። ወደ ኢያሪኮም ደረሱ፤ በኢያሪኮም የነበሩ የነቢያት ልጆች ወደ ኤልሳዕ ቀርበው፥ “እግዚአብሔር ጌታህን ከራስህ ላይ ዛሬ እንዲወስደው ዐውቀሃልን?” አሉት። እርሱም፥ “አዎን፥ ዐውቄአለሁ፤ ዝም በሉ” አላቸው። ኤልያስም ኤልሳዕን፥ “እግዚአብሔር ወደ ዮርዳኖስ ልኮኛልና እባክህ፥ በዚህ ቈይ” አለው። ኤልሳዕም፥ “ሕያው እግዚአብሔርን! ሕያው ነፍስህንም አልለይህም” አለው፤ ሁለቱም ሄዱ። ከነቢያትም ልጆች አምሳ ሰዎች ሄዱ፤ በፊታቸውም ርቀው ቆሙ፤ እነዚህም ሁለቱ በዮርዳኖስ ዳር ቆመው ነበር። ኤልያስም መጠምጠሚያውን ወስዶ ጠቀለለው፤ የዮርዳኖስንም ውኃ መታበት፤ ውኃውም ወዲህና ወዲያ ተከፈለ፤ ሁለቱም በደረቅ ተሻገሩ። ወጥተውም በምድረ በዳው ቆሙ። ከተሻገሩም በኋላ ኤልያስ ኤልሳዕን፥ “ከአንተ ሳልወሰድ አደርግልህ ዘንድ የምትሻውን ለምን” አለው፤ ኤልሳዕም፥ “መንፈስህ በእኔ ላይ ሁለት እጥፍ ይሆን ዘንድ እለምንሃለሁ” አለ። ኤልያስም፥ “አስቸጋሪ ነገር ለምነሃል፤ ነገር ግን ከአንተ ዘንድ በተወሰድሁ ጊዜ ብታየኝ ይሆንልሃል፤ አለዚያ ግን አይሆንልህም” አለው። ሁለቱም እየተነጋገሩ ሲሄዱ፥ እነሆ፥ የእሳት ሰረገላና የእሳት ፈረሶች በሁለቱ መካከል ገብተው ከፈሉአቸው፤ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ንውጽውጽታ ወደ ሰማይ ወጣ። ኤልሳዕም አይቶ፥ “አባቴ! አባቴ ሆይ! የእስራኤል ኀይላቸውና ጽንዓቸው፥” ብሎ ጮኸ። ከዚያም ወዲያ ዳግመኛ አላየውም፤ ልብሱንም ይዞ ከሁለት ቀደደው። ኤልያስም መጠምጠሚያውን ለኤልሳዕ ጣለለት፤ በኤልሳዕም ራስ ላይ ዐረፈ። ኤልሳዕም ተመልሶ በዮርዳኖስ ዳር ቆመ። በራሱ ላይ ያረፈችውን የኤልያስን መጠምጠሚያ ወስዶ ውኃውን መታባት፦ ውኃው ግን አልተከፈለም፤ እርሱም፥ “የኤልያስ አምላክ እግዚአብሔር ወዴት ነው? እንዴትስ ነው?” አለ። ከዚህም በኋላ ውኃውን በመታ ጊዜ ወዲህና ወዲያ ተከፈለ፤ ኤልሳዕም ተሻገረ። በኢያሪኮም የነበሩት የነቢያት ልጆች ኤልሳዕ ወደ እነርሱ ሲመጣ ባዩት ጊዜ፥ “የኤልያስ መንፈስ በኤልሳዕ ላይ ዐርፎአል” አሉ። ሊገናኙትም መጥተው በፊቱ በምድር ላይ ሰገዱለት። እነርሱም፥ “እነሆ፥ ከአገልጋዮችህ ጋር አምሳ ኀ`ያላን ሰዎች አሉ፤ የእግዚአብሔር መንፈስ ወደ ዮርዳኖስ ወይም ወደ አንድ ተራራ ወይም ወደ አንድ ኮረብታ ጥሎት እንደ ሆነ፥ ሄደው ጌታህን ይፈልጉት” አሉት። ኤልሳዕም፥ “አትላኩ፤” አላቸው። እስኪያፍራቸውም ድረስ ግድ ባሉት ጊዜ፥ “ላኩ” አለ፤ አምሳም ሰዎች ላኩ፤ ሦስት ቀንም ፈልገው አላገኙትም። በኢያሪኮም ተቀምጦ ሳለ ወደ እርሱ ተመለሱ፤ እርሱም፥ “አትላኩ፥ አትሂዱም አላልኋችሁምን?” አላቸው።
መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 2 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 2:1-18
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች