ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 2:1-18

ሁለተኛ መጽሐፈ ነገሥት 2:1-18 አማ05

እግዚአብሔር ኤልያስን በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ የሚወስድበት ጊዜ ደረሰ፤ ኤልያስና ኤልሳዕ ከጌልጌላ ተነሥተው ጒዞ ጀመሩ፤ በመንገድም ሳሉ ኤልያስ ኤልሳዕን “እነሆ፥ አንተ በዚህ ቈይ፤ እኔ ወደ ቤትኤል እንድሄድ እግዚአብሔር አዞኛል” አለው። ኤልሳዕ ግን “እኔ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ፤ ከቶ ከአንተ አልለይም” ሲል መለሰለት፤ ስለዚህም አብረው ወደ ቤትኤል ሄዱ። በዚያም የሚኖሩ የነቢያት ጉባኤ ወደ ኤልሳዕ ሄደው፥ “እግዚአብሔር ዛሬ ጌታህን ከአንተ ለይቶ እንደሚወስደው ታውቃለህን?” ሲሉ ጠየቁት። ኤልሳዕም “አዎ ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን ዝም በሉ!” ሲል መለሰላቸው። ከዚህም በኋላ ኤልያስ ኤልሳዕን፥ “እነሆ! አንተ በዚህ ቈይ፤ እኔ ወደ ኢያሪኮ እንድሄድ እግዚአብሔር አዞኛል” አለው። ኤልሳዕ ግን “እኔ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምላለሁ! ከቶ ከአንተ አልለይም!” ሲል መለሰለት፤ ስለዚህም አብረው ወደ ኢያሪኮ ሄዱ። በዚያም የሚኖሩ የነቢያት ጉባኤ ወደ ኤልሳዕ ሄደው፥ “እግዚአብሔር ዛሬ ጌታህን ከአንተ ለይቶ እንደሚወስደው ታውቃለህን?” ሲሉ ጠየቁት። ኤልሳዕም “አዎ ዐውቃለሁ፤ ነገር ግን ዝም በሉ” ሲል መለሰላቸው። ከዚህም በኋላ ኤልያስ ኤልሳዕን፥ “እነሆ! አንተ በዚህ ቈይ፤ እኔ ወደ ዮርዳኖስ ወንዝ እንድሄድ እግዚአብሔር አዞኛል” አለው። ኤልሳዕ ግን “እኔ በሕያው እግዚአብሔር ስም እምልልሃለሁ! ከቶ ከአንተ አልለይም!” ሲል መለሰለት፤ ስለዚህም አብረው ጒዞአቸውን ቀጠሉ። ከነቢያቱም ኀምሳው ተከትለዋቸው ወደ ዮርዳኖስ ሄዱ፤ ኤልያስና ኤልሳዕም በዮርዳኖስ ወንዝ አጠገብ ቆሙ፤ ኀምሳውም ነቢያት ደግሞ ጥቂት ራቅ ብለው ቆመው ነበር፤ ከዚህ በኋላ ኤልያስ ካባውን አውልቆ በመጠቅለል ውሃውን መታው፤ ውሃውም ወደ ቀኝና ወደ ግራ ተከፍሎላቸው ኤልያስና ኤልሳዕ በደረቅ ምድር ተሻገሩ፤ በዚያም ኤልያስ ኤልሳዕን “እኔ ከአንተ ከመወሰዴ በፊት ምን እንዳደርግልህ እንደምትፈልግ ንገረኝ” አለው። ኤልሳዕም “የአንተ ተተኪ እንድሆን የሚያስችል መንፈስ በእጥፍ ስጠኝ” ሲል መለሰለት። ኤልያስም “ያቀረብከው ጥያቄ ከባድ ነው፤ ነገር ግን እኔ ከአንተ ተለይቼ ወደ ሰማይ ስወሰድ ብታየኝ ይህን የጠየቅኸውን ስጦታ መቀበል ትችላለህ፤ ባታየኝ ግን ልታገኘው አትችልም” ሲል መለሰለት። እየተነጋገሩ እርምጃቸውን ቀጠሉ፤ ከዚያም በኋላ የእሳት ፈረሶች የሚስቡአቸው የእሳት ሠረገሎች ድንገት በመካከላቸው ገብተው ሁለቱን ለዩአቸው፤ ኤልያስም በዐውሎ ነፋስ ወደ ሰማይ ተወሰደ። ኤልሳዕም ይህን ሁሉ እያየ “የእስራኤል ሠረገሎችና ፈረሰኞች የሆንክ አባቴ ሆይ! አባቴ ሆይ!” እያለ ወደ ኤልያስ ጮኸ፤ ከዚያም በኋላ ኤልያስን ዳግመኛ አላየውም። ኤልሳዕም ከሐዘን ብዛት የተነሣ ልብሱን ከሁለት ቀደደ፤ ከኤልያስም የወደቀውን ካባ ከመሬት አነሣ፤ ከዚያም ሄዶ በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ቆመ። ውሃውንም በኤልያስ ካባ መትቶ፥ “የኤልያስ አምላክ እግዚአብሔር ወዴት ነው?” አለ፤ ከዚያም በኋላ እንደገና በመታው ጊዜ ውሃው ወደ ቀኝና ወደ ግራ ተከፍሎለት ወደ ማዶ ተሻገረ፤ ከኢያሪኮ የመጡት ነቢያት እርሱን ባዩት ጊዜ “በኤልያስ ላይ ዐድሮ የነበረው የመንፈስ ኀይል በኤልሳዕ ላይ አርፏል!” አሉ፤ ወደ እርሱም በመቅረብ ጐንበስ ብለው እጅ ነሡት “እነሆ! በዚህ ጠንካሮች የሆንን ኀምሳ ሰዎች አለን፤ እንሂድና ጌታህን እንፈልገው፤ ምናልባት የእግዚአብሔር መንፈስ አንሥቶ ወስዶ በአንድ ተራራ ላይ ወይም ሸለቆ ውስጥ አሳርፎት ይሆናል።” ኤልሳዕም “አትላኩአቸው” ሲል መለሰ። እነርሱ ግን እምቢ ለማለት እስኪያሳፍረው ድረስ አጥብቀው ስለ ለምኑት በጉዳዩ ተስማማና ኀምሳ ሰዎች ሄደው ሦስት ቀን ሙሉ ኤልያስን ፈለጉት፤ ነገር ግን ሊያገኙት አልቻሉም፤ ከዚያም በኋላ በኢያሪኮ ሆኖ ወደሚጠብቃቸው ወደ ኤልሳዕ ተመለሱ፤ ኤልሳዕም “እኔ ቀድሞውንስ አትሂዱ ብያችሁ አልነበረምን?” አላቸው።