መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 17
17
የእስራኤል ንጉሥ ሆሴዕ
1የይሁዳ ንጉሥ አካዝ በነገሠ በዐሥራ ሁለተኛው ዓመት የኤላ ልጅ ሆሴዕ በእስራኤል ላይ በሰማርያ ዘጠኝ ዓመት ነገሠ። 2በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ፤ ነገር ግን ከእርሱ አስቀድሞ እንደ ነበሩት እንደ እስራኤል ነገሥታት አልሆነም። 3የአሦርም ንጉሥ ስልምናሶር በእርሱ ላይ ዘመተ፤ ሆሴዕም ተገዛለት፤ ግብርም አመጣለት። 4የአሦርም ንጉሥ በሆሴዕ ላይ ዐመፅ አገኘ፤ መልእክተኞችን ወደ ግብፅ ንጉሥ ወደ ሴጎር ልኮ ነበርና፤ እንደ ልማዱም በየዓመቱ ለአሦር ንጉሥ ግብር አልሰጠምና፤ ስለዚህ የአሦር ንጉሥ ተዋጋው፤ ይዞም በወህኒ ቤት አሰረው።
የዐሥሩ ነገድ መንግሥት መውደቅ
5የአሦርም ንጉሥ በምድር ሁሉ ላይ ወጣ፤ ወደ ሰማርያም ወጥቶ ሦስት ዓመት ከበባት። 6በሆሴዕም በዘጠነኛው ዓመት የአሦር ንጉሥ ሰማርያን ያዘ፤ እስራኤልንም ወደ አሶር አፈለሰ፤ በአላሔና በአቦር፤ በጎዛንም ወንዝ፤ በሜዶንም ከተሞች አኖራቸው።
7የእስራኤልም ልጆች ከግብፅ ንጉሥ ከፈርዖን እጅ፥ ከግብፅ ምድር ያወጣቸውን አምላካቸውን እግዚአብሔርን በድለው ነበርና፥ ሌሎችንም አማልክት አምልከው ነበርና፤ 8እግዚአብሔርም ከእስራኤል ልጆች ፊት በአሳደዳቸው በአሕዛብ ሥርዐት፥ የእስራኤልም ነገሥታት ባደረጓት ሥርዐት ሄደው ነበርና እንደዚህ ሆነ። 9የእስራኤልም ልጆች በአምላካቸው በእግዚአብሔር ላይ ቅን ያልሆነን ነገር በስውር አደረጉ፤ በከተሞቻቸውም ሁሉ ከዘበኞች ግንብ ጀምሮ እስከ ተመሸገች ከተማ ድረስ በከፍታዎች ላይ መስገጃዎችን ሠሩ። 10በረጃጅሙ ኮረብታ ሁሉ ላይ፥ በለመለመውም ዛፍ ሁሉ በታች ሐውልቶችንና የማምለኪያ ዐምዶችን ተከሉ፤ 11እግዚአብሔርም ከፊታቸው ያወጣቸው አሕዛብ እንዳደረጉት፥ በኮረብቶቹ መስገጃዎች ሁሉ ላይ ያጥኑ ነበር፤ እግዚአብሔርንም ያስቈጡ ዘንድ የማምለኪያ ዐፀዶችንና ሐውልቶችን አደረጉ፤ 12እግዚአብሔርም፥ “በእግዚአብሔር ላይ ይህን አታድርጉ” ብሎ የከለከላቸውን ጣዖቶች አመለኩ። 13እግዚአብሔርም፥ “ከክፉ መንገዳችሁ ተመለሱ፤ ለአባቶቻችሁም እንዳዘዝሁት፥ በባሪያዎቼ በነቢያት የላክሁላችሁን ትእዛዜንና ሥርዐቴን፥ ሕጌንም ሁሉ ጠብቁ” ብሎ በነቢዩ ሁሉና በባለ ራእዩ አፍ ሁሉ በእስራኤልና በይሁዳ መሰከረ። 14ነገር ግን አምላካቸውን እግዚአብሔርን እንዳላመኑ ከአባቶቻቸው አንገት ይልቅ አንገታቸውን አደነደኑ እንጂ አልሰሙም። 15የገባላቸውንም ቃል ኪዳን ሁሉ አልጠበቁም። ከንቱ ነገርንም ተከተሉ፤ ከንቱም ሆኑ፤ እንደ እነርሱም እንዳይሠሩ ያዘዛቸውን በዙሪያቸው ያሉትን አሕዛብ ተከተሉ። 16የአምላካቸውንም የእግዚአብሔርን ትእዛዝ ሁሉ ተዉ፤ ቀልጠው የተሠሩትንም የሁለቱን እንቦሶች ምስሎች አደረጉ፤ የማምለኪያ ዐፀድንም ተከሉ፤ ለሰማይም ሠራዊት ሁሉ ሰገዱ፤ በዓልንም አመለኩ። 17ወንዶችና ሴቶች ልጆቻቸውንም በእሳት ሥዉአቸው፤ ምዋርተኞችና አስማተኞችም ሆኑ፤ ያስቈጡትም ዘንድ በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገር ለማድረግ ራሳቸውን ሸጡ። 18ስለዚህም እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ እጅግ ተቈጣ፤ ከፊቱም ጣላቸው፤ ከይሁዳም ነገድ ብቻ በቀር ማንም አልቀረም።
19ይሁዳም ደግሞ እስራኤል ባደረጋት ሥርዐት ሄደ እንጂ የአምላኩን የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አልጠበቀም፤ እግዚአብሔርንም ተዉት። 20እግዚአብሔርም በእስራኤል ዘር ሁሉ ተቈጣ፤ አስጨነቃቸውም፤ ከፊቱም እስኪጥላቸው ድረስ በበዝባዦች እጅ አሳልፎ ሰጣቸው። 21እስራኤልም ከዳዊት ቤት ተለዩ፤ የናባጥንም ልጅ ኢዮርብዓምን አነገሡ፤ ኢዮርብዓምም እግዚአብሔርን ከመከተል እስራኤልን መለሰ፤ ታላቅም ኀጢአት አሠራቸው። 22የእስራኤልም ልጆች ኢዮርብዓም ባደረገው ኀጢአት ሁሉ ሄዱ፤ 23እግዚአብሔርም በባሪያዎቹ በነቢያት ሁሉ አፍ እንደ ተናገረው እስራኤልን ከፊቱ እስኪያወጣ ድረስ ከእርስዋ አልራቁም። እስራኤልም እስከ ዛሬ ድረስ ከምድሩ ወደ አሦር ፈለሰ።
24የአሦርም ንጉሥ ከባቢሎንና ከኩታ፥ ከአዋና ከሐማት፥ ከሴፌርዋይም ሰዎችን አመጣ፤ በእስራኤልም ልጆች ፋንታ በሰማርያ ከተሞች አኖራቸው፤ ሰማርያንም ወረሱአት፤ በከተሞችዋም ተቀመጡ። 25በዚያም መቀመጥ በጀመሩ ጊዜ እግዚአብሔርን አይፈሩትም ነበር፤ እግዚአብሔርም አንበሶችን ሰደደባቸው፤ ይገድሉአቸውም ነበር። 26ስለዚህም ለአሦር ንጉሥ፥ “ያፈለስኻቸው፥ በሰማርያም ከተሞች ያኖርኻቸው ሕዝቦች የሀገሩን አምላክ ሕግ አላወቁም፤ የሀገሩን አምላክ ሕግ አላወቁምና አንበሶችን ሰድዶባቸዋል፤ እነሆም፥ እየገደሉአቸው ነው” ብለው ተናገሩት።
27የአሦርም ንጉሥ፥ “ከዚያ ካመጣኋቸው ካህናት አንዱን ውሰዱ፤ ሄዶም በዚያ ይቀመጥ፤ የሀገሩንም አምላክ ሕግ ያስተምራቸው” ብሎ አዘዘ። 28ከሰማርያም ካፈለሱአቸው ካህናት አንዱን ወስደው በቤቴል አኖሩት፤ ያም ካህን እግዚአብሔርን እንዴት እንደሚፈሩት ያስተምራቸው ነበር። 29በየሕዝባቸውም አምላኮቻቸውን አደረጉ፤ ሳምራውያንም በሠሯቸው በኮረብታው መስገጃዎች ሕዝቡ ሁሉ በሚኖሩባቸው ከተሞቻቸው አኖሩአቸው። 30የባቢሎንም ሰዎች ሴኬቤቴናሆምን ሠሩ፤ የኩታም ሰዎች ኤርጌትን ሠሩ፤ 31የሐማትም ሰዎች አሲማትን ሠሩ፤ አዋውያንም ኤልባዝርንና ተርታቅን ሠሩ፤ የሴፌርዋይም ሰዎች ለሴፌርዋይም አማልክት ለአድራሜሌክና ለአኔሜሌክ ልጆቻቸውን በእሳት ይሠዉ ነበር። 32እግዚአብሔርንም ይፈሩ ነበር፤ ሕዝቡም ሁሉ በሚኖሩበት ከተማ በሰማርያ በሠሩት በከፍታው ቦታ ጣዖቶቻቸውን አኖሩ። እግዚአብሔርንም ይፈሩ ነበር፤ ከመካከላቸውም ለኮረብታው መስገጃዎች ካህናትን አደረጉ፤ በኮረብታውም መስገጃዎች ይሠዉ ነበር። 33እግዚአብሔርንም ሲፈሩ ከመካከላቸው እንደ ፈለሱት እንደ አሕዛብ ልማድ አምላካቸውን ያመልኩ ነበር።
34እስከ ዛሬም ድረስ እንደ ልማዳቸው ያደርጋሉ፤ እግዚአብሔርንም ይፈራሉ፤ እግዚአብሔርም እስራኤል ብሎ የጠራውን የያዕቆብን ልጆች እንዳዘዛቸው ሥርዐትና ፍርድ፥ ሕግና ትእዛዝም ያደርጋሉ።#ዕብ. “አይፈሩም ፤ አያደርጉም” ይላል። 35እግዚአብሔርም ከእነርሱ ጋር ቃል ኪዳን አደረገ፤ እንዲህም ብሎ አዘዛቸው፥ “ሌሎችን አማልክት አትፍሩአቸው፤ አትስገዱላቸውም፤ አታምልኩአቸውም፤ አትሠዉላቸውም። 36ነገር ግን በታላቅ ኀይል በተዘረጋችም ክንድ ከግብፅ ምድር ያወጣችሁን እግዚአብሔርን እርሱን ፍሩ፤ ለእርሱም ስገዱ፤ ለእርሱም ሠዉ። 37የጻፈላችሁንም ሥርዐትና ፍርድ፥ ሕግና ትእዛዝም ለዘለዓለም ታደርጉ ዘንድ ጠብቁ፤ ሌሎችንም አማልክት አትፍሩ። 38ከእናንተም ጋር ያደረገውን ቃል ኪዳን አትርሱ፤ ሌሎችንም አማልክት አትፍሩ። 39ነገር ግን አምላካችሁን እግዚአብሔርን ፍሩ፤ እርሱም ከጠላቶቻቸሁ ሁሉ እጅ ያድናችኋል። 40ነገር ግን እነርሱ እንደሚያደርጉት ልማዳቸውን አትስሙ። 41እነዚህም አሕዛብ እግዚአብሔርን ይፈሩ ነበር፤ ደግሞም የተቀረጹ ምስሎቻቸውን ያመልኩ ነበር፤ ልጆቻቸውም፥ የልጅ ልጆቻቸውም አባቶቻቸው እንዳደረጉ እስከ ዛሬ ድረስ እንዲሁ ያደርጋሉ።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 17: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ