መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 16
16
የይሁዳ ንጉሥ አካዝ
(2ዜ.መ. 28፥1-27)
1በሮሜልዩ ልጅ በፋቁሔ በዐሥራ ሰባተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአታም ልጅ አካዝ ነገሠ። 2አካዝ መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሃያ ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ዐሥራ ስድስት ዓመት ነገሠ፤ እንደ አባቱም እንደ ዳዊት በአምላኩ በእግዚአብሔር ፊት በታማኝነት ቅን ነገርን አላደረገም። 3ነገር ግን በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፤ ደግሞም እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ፊት እንዳሳደዳቸው እንደ አሕዛብ ርኵሰት ልጁን በእሳት ሠዋው። 4በመስገጃዎቹና በኮረብቶቹ ላይ በለመለመውም ዛፍ ሁሉ በታች ይሠዋና ያጥን ነበር። 5ያን ጊዜም የሶርያ ንጉሥ ረአሶንና የእስራኤል ንጉሥ የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ ሊዋጉ ወደ ኢየሩሳሌም ወጡ፤ አካዝንም ከበቡት፥ ሊያሸንፉት ግን አልቻሉም። 6በዚያም ዘመን የሶርያ ንጉሥ ረአሶን ኤላትን ወደ ሶርያ መለሰላቸው፥ አይሁድንም ከኤላት አሳደደ፤ ኤዶማውያንም ወደ ኤላት መጥተው እስከ ዛሬ ድረስ በዚያ ይኖራሉ።
7አካዝም፥ “እኔ ባሪያህና ልጅህ ነኝ፤ መጥተህ ከተነሡብኝ ከሶርያ ንጉሥና ከእስራኤል ንጉሥ እጅ አድነኝ” ብሎ ወደ አሦር ንጉሥ ወደ ቴልጌልቴልፌልሶር መልእክተኞችን ላከ። 8አካዝም በእግዚአብሔር ቤትና በንጉሡ ቤተ መዛግብት የተገኘውን ብርና ወርቅ ወስዶ ወደ አሦር ንጉሥ ገጸ በረከት አድርጎ ሰደደው። 9የአሦርም ንጉሥ ሰማው፤ የአሦርም ንጉሥ ወደ ደማስቆ ወጣ፤ ያዛትም፤ ሕዝብዋንም ወደ ቂር አፈለሳቸው፤ ረአሶንንም ገደለው።
10የይሁዳ ንጉሥ አካዝም የአሦርን ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶርን ሊገናኘው ወደ ደማስቆ ሄደ፤ በደማስቆ የነበረውንም መሠዊያ አየ፤ ንጉሡም አካዝ የመሠዊያውን ምሳሌና የአሠራሩን መልክ ወደ ካህኑ ወደ ኦርያ ላከው። 11ካህኑም ኦርያ ንጉሡ አካዝ ከደማስቆ እንደ ላከለት መሠዊያውን ሁሉ ሠራ፤ እንዲሁም ካህኑ ኦርያ ንጉሡ አካዝ ከደማስቆ እስኪመጣ ድረስ ሠራው።#“እንዲሁም ካህኑ ኦርያ ንጉሡ አካዝ ከደማስቆ እስኪመጣ ድረስ ሠራው” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። 12ንጉሡም ከደማስቆ በመጣ ጊዜ መሠዊያውን አየ፤ ንጉሡም ወደ መሠዊያው ወጣ። 13የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉንም ቍርባን አሳረገ፤ የመጠጡንም ቍርባን አፈሰሰ፤ የደኅንነቱንም መሥዋዕት ደም በመሠዊያው ላይ ረጨ። 14በእግዚአብሔርም ፊት የነበረውን የናሱን መሠዊያ ከእግዚአብሔር ቤት ፊት ከመሠዊያውና ከእግዚአብሔር ቤት መካከል ፈቀቅ አድርጎ በመሠዊያው አጠገብ በሰሜን በኩል አኖረው። 15ንጉሡም አካዝ፥ “የሚቃጠለውን የጥዋት መሥዋዕት፥ የማታውንም የእህሉን ቍርባን፥ የንጉሡንም መሥዋዕትና የእህሉን ቍርባን፥ የሕዝቡንም ሁሉ የሚቃጠለውን መሥዋዕትና የእህሉን፥ የመጠጡንም ቍርባን በታላቁ መሠዊያ ላይ አቅርብ፤ የሚቃጠለውንም መሥዋዕት ደም ሁሉ፥ የሌላውንም መሥዋዕታቸውን ደም ሁሉ በእርሱ ላይ ርጭበት፤ የናሱ መሠዊያ ግን በየጥዋቱ ለእኔ ይሁን” ብሎ ካህኑን ኦርያን አዘዘው። 16ካህኑ ኦርያም ንጉሡ አካዝ እንዳዘዘው ሁሉ እንዲሁ አደረገ።
17ንጉሡ አካዝም የመቀመጫዎችን ክፈፍ ቈረጠ፤ ከእነርሱም የመታጠቢያውን ሰኖች ወሰደ፤ ኵሬውንም ከበታቹ ከነበሩት ከናሱ በሬዎች አወረደው፤ በጠፍጣፋውም ድንጋይ ላይ አኖረው። 18በእግዚአብሔርም ቤት የዙፋኑን መሠረት ሠራ፤ ስለ አሦርም ንጉሥ በውጭ ያለውን የንጉሡን መግቢያ ወደ እግዚአብሔር ቤት አዞረው። 19የቀረውም አካዝ ያደረገው ነገር እነሆ፥ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 20አካዝም እንደ አባቶቹ አንቀላፋ፥ በዳዊትም ከተማ ተቀበረ፤ ልጁም ሕዝቅያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 16: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ