መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 14
14
የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስ
(2ዜ.መ. 25፥1-24)
1በእስራኤል ንጉሥ በኢዮአካዝ ልጅ በዮአስ በሁለተኛው ዓመት የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ ነገሠ። 2መንገሥም በጀመረ ጊዜ ዕድሜው ሃያ አምስት ዓመት ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ሃያ ዘጠኝ ዓመት ነገሠ። እናቱም ዮአድም የተባለች የኢየሩሳሌም ሴት ነበረች። 3በእግዚአብሔርም ፊት ቅን ነገር አደረገ፤ ነገር ግን አባቱ ኢዮአስ እንዳደረገ ሁሉ እንጂ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት አላደረገም። 4ነገር ግን በኮረብቶቹ ላይ ያሉትን መስገጃዎች አላስወገደም፤ ሕዝቡም ገና በኮረብቶቹ ላይ ባሉት መስገጃዎች ይሠዋና ያጥን ነበር። 5መንግሥቱም በእጁ በጸናለት ጊዜ አባቱን የገደሉትን አገልጋዮች ገደለ። 6በሙሴ ሕግ መጽሐፍም እንደ ተጻፈ፥ እግዚአብሔርም፥ “ሁሉ በኀጢአቱ ይሙት እንጂ አባቶች ስለ ልጆች አይሙቱ፤ ልጆችም ስለ አባቶች አይሙቱ” ብሎ እንዳዘዘ የነፍሰ ገዳዮቹን ልጆች አልገደላቸውም። 7እርሱም በጨው ሸለቆ ከኤዶምያስ ዐሥር ሺህ ሰው ገደለ፤ ሴላንም በጦርነት ወስዶ ስምዋን እስከ ዛሬ ድረስ “ዮቅትኤል” ብሎ ጠራት።
8በዚያን ጊዜም አሜስያስ፥ “ና እርስ በርሳችን ፊት ለፊት እንተያይ” ብሎ ወደ እስራኤል ንጉሥ ወደ ኢዩ ልጅ ወደ ኢዮአካዝ ልጅ ወደ ዮአስ መልእክተኞችን ላከ። 9የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ፥ “የሊባኖስ ኵርንችት፦ ልጅህን ለልጄ ሚስት አድርገህ ስጠው ብሎ ወደ ሊባኖስ ዝግባ ላከ፤ የሊባኖስም አውሬ አልፎ ኵርንችቱን ረገጠ። 10ኤዶምያስን በእውነት መታህ፤ ልብህንም ከፍ ከፍ አደረግህ፤ በዚያ ተመካ፤ በቤትህም ተቀመጥ፤ አንተ፥ ይሁዳም ከአንተ ጋር ትወድቁ ዘንድ ስለ ምን መከራን ትሻለህ?” ብሎ ወደ ይሁዳ ንጉሥ ወደ አሜስያስ ላከ።
11አሜስያስ ግን አልሰማም፤ የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ ዘመተ፤ እርሱና የይሁዳ ንጉሥ አሜስያስም በይሁዳ ባለች በቤትሳሚስ ፊት ለፊት ተያዩ። 12ይሁዳም በእስራኤል ፊት ተመታ፤ እያንዳንዱም ወደ ድንኳኑ ሸሸ። 13የእስራኤልም ንጉሥ ዮአስ የይሁዳን ንጉሥ የአካዝያስን ልጅ የኢዮአስን ልጅ አሜስያስን በቤትሳሚስ ይዞ ወደ ኢየሩሳሌም መጣ፤ የኢየሩሳሌምንም ቅጥር ከኤፍሬም በር ጀምሮ እስከ ማዕዘኑ በር ድረስ አራት መቶ ክንድ አፈረሰ። 14ወርቁንና ብሩን ሁሉ፥ በእግዚአብሔርም ቤትና በንጉሥ ቤተ መዛግብት የነበሩትን ዕቃዎች ሁሉ፤ በመያዣም የተያዙትን ልጆች ወስዶ ወደ ሰማርያ ተመለሰ።
15የቀረውም ያደረገው የዮአስ ነገር፥ ኀይሉም፥ ከይሁዳም ንጉሥ ከአሜስያስ ጋር እንደ ተዋጋ፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 16ዮአስም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በሰማርያም ከእስራኤል ነገሥታት ጋር ተቀበረ፤ ልጁም ኢዮርብዓም በፋንታው ነገሠ።
17የይሁዳ ንጉሥ የኢዮአስ ልጅ አሜስያስ ከእስራኤል ንጉሥ ከኢዮአካዝ ልጅ ከዮአስ ሞት በኋላ ዐሥራ አምስት ዓመት ኖረ። 18የቀረውም የአሜስያስ ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ እነሆ፥ በይሁዳ ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 19በኢየሩሳሌምም የዐመፅ መሐላ አደረጉበት፤ እርሱም ወደ ለኪሶ ኮበለለ፤ ወደ ለኪሶም ተከተሉት፤ በዚያም ገደሉት። 20በድኑንም በፈረስ ጭነው አመጡት፤ በኢየሩሳሌምም በዳዊት ከተማ ከአባቶቹ ጋር ቀበሩት። 21የይሁዳም ሕዝብ ሁሉ የዐሥራ ስድስት ዓመት ልጅ የነበረውን ዓዛርያስን ወስደው በአባቱ በአሜስያስ ፋንታ አነገሡት። 22ንጉሡም ከአባቶቹ ጋር ከአንቀላፋ በኋላ፥ ኤላትን ሠርቶ ወደ ይሁዳ መለሳት።
የእስራኤል ንጉሥ ዳግማዊ ኢዮርብአም
23በይሁዳ ንጉሥ በኢዮአስ ልጅ በአሜስያስ በዐሥራ አምስተኛው ዓመተ መንግሥት የእስራኤል ንጉሥ የዮአስ ልጅ ኢዮርብዓም በሰማርያ መንገሥ ጀመረ፤ አርባ አንድ ዓመትም ነገሠ። 24በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ ነገር አደረገ እስራኤልንም ካሳታቸው ከናባጥ ልጅ ከኢዮርብዓም ኀጢአት ሁሉ አልራቀም። 25በጋትሔፌር በነበረው በአማቴ ልጅ በባሪያው በነቢዩ በዮናስ አፍ እንደ ተናገረው እንደ እስራኤል አምላክ እንደ እግዚአብሔር ቃል የእስራኤልን ድንበር ከሔማት መግቢያ ጀምሮ እስከ ዓረባ ባሕር ድረስ መለሰ። 26በቍጥር እንዳነሱ፥ የታሰረውና የተለቀቀውም እንደ ጠፋ፥ እስራኤልንም የሚረዳ እንዳልነበረ እግዚአብሔር እጅግ የመረረውን የእስራኤልን ጭንቀት አየ። 27እግዚአብሔርም የእስራኤልን ዘር ከሰማይ በታች ይደመስስ ዘንድ አልተናገረም፤ ነገር ግን በዮአስ ልጅ በኢዮርብዓም እጅ አዳናቸው።
28የቀረውም የኢዮርብዓም ነገር፥ ያደረገውም ሁሉ፥ ኀይሉም፥ የይሁዳ የነበረውን ደማስቆንና ሔማትን ለእስራኤል እንደ መለሰ፥ እነሆ፥ በእስራኤል ነገሥታት የታሪክ መጽሐፍ የተጻፈ አይደለምን? 29ኢዮርብዓምም እንደ አባቶቹ እንደ እስራኤል ነገሥታት አንቀላፋ፤ ልጁም ዘካርያስ በፋንታው ነገሠ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነገሥት ካልእ 14: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ