መጽሐፈ ዕዝራ ካልእ 6
6
የቤተ መቅደሱ ሥራ እንደገና እንደ ተጀመረ
1በዳርዮስ በሁለተኛው ዓመተ መንግሥቱ፦ ነቢያቱ ሐጌና የሐዶ ልጅ ዘካርያስ በይሁዳና በኢየሩሳሌም ባሉ አይሁድ ላይ በእስራኤል አምላክ በእግዚአብሔር ስም ትንቢት ተናገሩ። 2ከዚህም በኋላ የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤልና የኤዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ ተነሡ፤ የእግዚአብሔርም ነቢያት እየረዱአቸው ከእነርሱ ጋር ሳሉ በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት ይሠሩ ጀመሩ።
3በእነዚያም ወራት የሶርያና የፊንቂስ ገዥ ሲሳኒስና ሳትራቡዛኒስ ከባልንጀሮቻቸው ጋር ወደ እነርሱ መጡ። 4እንዲህም አሏቸው፥ “ይህን ቤትና ጣራውን፥ ሌላውንም ሥራ ሁሉ ትሠሩ ዘንድ ማን አዘዛችሁ? የሚሠሩትስ ግንበኞች እነማን ናቸው?” 5ያንጊዜም እግዚአብሔር ይቅር ብሏቸዋልና#ግሪክ ሰባ. ሊ. “እግዚአብሔር ምርኮኞቹን ጐብኝትዋልና” ይላል። ለአይሁድ ሽማግሌዎች ባለሟልነትን ሰጣቸው። 6ወደ ዳርዮስ እስኪልኩ፥ ደብዳቤንም እስኪያመጡላቸው ድረስ ሥራውን አልከለከሏቸውም።
7የሶርያና የፊንቂስ ገዥ ሲሳኒስና ሳትራቡዛኒስ፥ በሶርያና በፊንቂስም ከእነርሱ ጋር ያሉ ሹሞች፥ ባልንጀሮቻቸውም “ለንጉሡ ለዳርዮስ ትድረስ” ብለው ወደ ዳርዮስ ጽፈው ላኩ። 8“ጌታችን ንጉሥ ሆይ ሰላም ለአንተ ይሁን! ሁሉን እንድታውቅ ወደ ይሁዳ ወደ ኢየሩሳሌም በመጣን ጊዜ የአይሁድ ምርኮኞች አለቆችን በኢየሩሳሌም ከተማ አገኘናቸው። 9በተጠረበና ዋጋው ብዙ በሆነ ድንጋይ፥ በየወገናቸው ማዕዘን ባላቸው እንጨቶችም ታላቅና አዲስ የሆነውን የእግዚአብሔርን ቤት ሲሠሩ አገኘናቸው። 10በችኰላም ይሠሩና ያፋጥኑ ነበር፤ በእጃቸውም እያስተካከሉ በትጋት ይሠሩ ነበር። በክብርና በጥንቃቄም ተሠራ። 11ከዚህም በኋላ ‘ይህን ቤት ትሠሩ ዘንድ፥ ይህንም መሠረት ትጥሉ ዘንድ ማን አዘዛችሁ?’ ብለን አለቆቻቸውን ጠየቅናቸው። 12ሰዎቻቸውንና የሥራ መሪዎቻቸውንም በየስማቸው ጽፈን ወደ አንተ እንልክ ዘንድ መረመርናቸው፤ አለቆቻችውንም ጠየቅናቸው። 13እነርሱም እንዲህ ብለው መለሱልን፦ ‘እኛስ ምድርንና ሰማይን የፈጠረ የእግዚአብሔር ባሮች ነን።’ 14ይህ ቤት ከብዙ ዘመን አስቀድሞ በታላቁና በብርቱው የእስራኤል ንጉሥ ሰሎሞን ተሠርቶ ተፈጽሞ ነበር። 15ነገር ግን አባቶቻችን ኀጢአት ሠርተው ሰማያዊውን የእስራኤል ፈጣሪ አሳዝነውታልና በባቢሎን ንጉሥ በናቡከደነፆርና በፋርስ ንጉሥ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “በከለዳውያን ንጉሥ” ይላል። እጅ ጣላቸው። 16ይህንም ቤት አፈረሰ፤ በእሳትም አቃጠለ፤ ሕዝቡንም ማረከ፤ ወደ ባቢሎንም ወሰዳቸው። 17ቂሮስም በባቢሎን በነገሠ በመጀመሪያው ዓመት ንጉሡ ቂሮስ ይህን ቤት ይሠሩ ዘንድ ጻፈ። 18ናቡከደነፆርም በኢየሩሳሌም ካለው ቤተ መቅደስ ያወጣውን፥ ባዳራሹም ያኖረውን የወርቅና የብር ንዋየ ቅድሳቱን፥ ንጉሥ ቂሮስ በባቢሎን ካለ አዳራሹ አውጥቶ ለዘሩባቤልና ለገዥው ለሰናባሶርስ ሰጣቸው። 19ይህንም ንዋየ ቅድሳት ወስደው በኢየሩሳሌም ባለ ቤተ መቅደስ ያኖሩት ዘንድ፥ የእግዚአብሔርንም ቤተ መቅደስ በቦታው ይሠሩት ዘንድ አዘዛቸው።#በግሪክ ሰባ. ሊ. ምዕ. 6 ቍ. 19 በነጠላ ነው። 20ከዚህም በኋላ ያ ሰናባሳሮስ በደረሰ ጊዜ በኢየሩሳሌም ያለ የእግዚአብሔርን ቤት ይሠራ ጀመረ፤ ከዚያም ቀን ጀምሮ እስከ ዛሬ ድረስ ይሠሩ ነበር፤ ነገር ግን አልጨረሱም። 21አሁንም ጌታችን ንጉሥ ሆይ! በባቢሎን ያለ የንጉሡን የቂሮስን መንግሥት የታሪክ መጻሕፍት ገልጠህ መርምር። 22ንጉሡ ቂሮስ በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት ይሠሩ ዘንድ እንደ ፈቀደ ብታገኝ፥ ጌታችን ንጉሥ ሆይ! አንተም ፈቅደህላቸው እንደ ሆነ ስለዚህ ነገር ላክልን።”
የንጉሥ ቂሮስ ትእዛዝ መገኘት
23ከዚህም በኋላ ንጉሡ ዳርዮስ በባቢሎን የታሪክ መጽሐፍ ውስጥ ይፈልጉ ዘንድ አዘዘ፤ በሜዶን አውራጃ በጣኒስ-ባሪ ከተማ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ኤክባታና” ይላል። ውስጥ የታሪክ መጽሐፉን ባኖሩበት በአንድ ቦታ ተገኘ፤ እንዲህም ይላል፦ 24“በንጉሡ በቂሮስ በመጀመሪያው ዓመተ መንግሥት በየዕለቱ በእሳት መሥዋዕት የሚሠዉበትን፥ በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት ይሠሩ ዘንድ አዘዘ። 25ቁመቱ ስድሳ ክንድ ወርዱም ስድሳ ክንድ ይሁን፤ ሥራውም በሦስት ወገን በጥርብ ድንጋይ፥ ባንዲት ወገንም በሀገሩ አዲስ የዝግባ እንጨት ይሁን፤ ወጭውንም ከንጉሡ ከቂሮስ ዕቃ ቤት ይሰጧቸው ዘንድ አዘዘ። 26ናቡከደነፆርም በኢየሩሳሌም ካለው ከቤተ መቅደስ አውጥቶ ወደ ባቢሎን የወሰደውን የወርቁንና የብሩን የእግዚአብሔርን ቤት ንዋየ ቅድሳት በኢየሩሳሌም ወዳለው ቀድሞ ወደ ነበረበት ወደዚያ ቤት ይመልሱት ዘንድ አዘዘ።”
ንጉሥ ዳርዮስ ሥራው እንዲቀጥል ማዘዙ
27የእግዚአብሔር ባሪያ የይሁዳ አለቃ ዘሩባቤልና በይሁዳ ያሉ ሽማግሌዎች የእግዚአብሔርን ቤት በቦታው ይሠሩት ዘንድ የሶርያና የፊንቂስ ገዥ ሲሳኒስና ሳትራቡዛኒስ፥ ከእነርሱም ጋራ ያሉ ጓደኞቻቸው የሶርያና የፊንቂስ ሹሞች ቦታቸውን ይተዉላቸው ዘንድ አዘዘ፤ 28“እኔም የእግዚአብሔርን ቤት ሠርተው እስኪፈጽሙ ድረስ ከተማረኩበት የተመለሱ የአይሁድ ወገኖች ሁሉ አንድ ሁነው ተሰማርተው የእግዚአብሔርን ቤት ይሠሩ ዘንድ አዘዝኋቸው። 29ከቄሊ-ሶርያና ፊኒቂ ከሚገባው ግብር ለእግዚአብሔር መሥዋዕት ፍየሎችንና ላሞችን፥ በጎችንም እንደ ሥርዐቱ ለእነዚህ ሰዎችና ለአለቃው ለዘሩባቤልም ሰጥታችሁ ደስ አሰኙአቸው። 30እንደዚሁም የሚያነዱትን እንጨት፥ ስንዴውን፥ ጨዉንና ወይኑን፥ ዘይቱንም፥ የዘወትሩንም ወጭ ገንዘብ ሁሉ፥ በየዓመቱም የሚያደርሳቸውን፥ በኢየሩሳሌም ያሉ ካህናቱ ያሏችሁን ያህል ስጧቸው፤ ግብሩንም ሳትከራከሩ እነርሱ የሚሏችሁን የሚበቃቸውን ስጧቸው። 31ስለ ንጉሡና ስለ ልጆቹ ለልዑል እግዚአብሔር ቍርባኑን ያቀርቡ ዘንድ፥ ስለ ሕይወታቸውም ይጸልዩላቸው ዘንድ።
32“በዚች ደብዳቤ እንደ ተጻፈ አልሠራም የሚል፥ የሚከራከራቸውም ቢኖር ከራሱ ቤት እንጨት አምጥተው በዚያ ይስቀሉት፤ ገንዘቡንም ይዝረፉት፤ ለንጉሡ ቤትም ይሁን። 33ስለዚህም ስሙ በዚያ የተጠራ እግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ያለውን የእግዚአብሔርን ቤት ሥራ ይከለክሏቸው ዘንድ፥ ክፉ ሥራም ይሠሩ ዘንድ እጃቸውን የሚያነሡ ነገሥታትንና አሕዛብን ሁሉ ያጥፋቸው። 34እኔ ዳርዮስ እንዲህ አድርገው ተግተው ይሠሩ ዘንድ አዘዝሁ።”
Currently Selected:
መጽሐፈ ዕዝራ ካልእ 6: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ