መጽሐፈ ዕዝራ ካልእ 5
5
ከምርኮ የተመለሱት ሰዎች ስም ዝርዝር
1ከዚህም በኋላ የሚወጡትን ያባቶቻቸውን ቤተ ሰቦች አለቆች በየወገኖቻቸው ለዩ፤ ሚስቶቻቸውን፥ ወንዶች ልጆቻቸውንና ሴቶች ልጆቻቸውን፥ ወንዶች አገልጋዮቻቸውንና ሴቶች አገልጋዮቻቸውን፥ ከብቶቻቸውንም ለዩ። 2ዳርዮስም በመሰንቆ፥ በበገናና በከበሮ በሰላም ወደ ኢየሩሳሌም ያደርሷቸው ዘንድ ከእነርሱ ጋር ሺህ ፈረሰኞችን ላከ። 3ወንድሞቻቸውም ሁሉ እየዘፈኑ ከእነርሱ ጋር በአንድነት እንዲሄዱ አደረገ።
4በየሀገራቸውና በየወገናቸው፥ አለቆቻቸውን ተከትለው የወጡ ሰዎችም ስማቸው ይህ ነው። 5ካህናት የፊንሐስ ልጆች፥ የአሮን ልጆች፥ የሰራህያ ልጅ የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢዮስስ፥#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ኢያሱ” ይላል። ከይሁዳ ወገን ከፋሬስ ወገን ከዳዊት ወገን የሆነ የሰላትያል ልጅ የዘሩባቤል ልጅ ኢዮአቄም፤ 6ዘሩባቤልም በፋርስ ንጉሥ በዳርዮስ ፊት በሁለተኛው ዓመተ መንግሥቱ በመጀመሪያው ወር በሚያዝያ የጥበብን ነገር የተናገረ ነው።
7የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ከማረካቸው ከፋርስ ምርኮ የወጡ ከይሁዳ የሆኑ ሰዎች እኒህ ናቸው። 8እነርሱም ወደ ኢየሩሳሌምና ወደ ሌላዎች የይሁዳ ክፍሎች ተመለሱ። ሁሉንም በየከተሞቻቸው ላካቸው፤ እነዚህም አስቀድመው ከተሾሙላቸው ከመጀመሪያዎቹ ሹሞች፥ ከኢያሱና ከዘሩባቤል፥ ከነህምያ፥ ከዛርያስ፥ ከሬስያስ፥ ከኤኔንዮስ፥ ከመርዶክዮስ፥ ከቦኤልሰሮስ፥ ከአስፈራሶስ፥ ከሬልዮስ፥ ከኢሮምዮስና ከበዓናስ ጋር የመጡ ናቸው። 9የሕዝቡም ቍጥር፥#ግሪክ ሰባ. ሊ. “የሕዝቡና የገዢዎች ቍጥር” ይላል። የፋሬስ ልጆች ሁለት ሺ አንድ መቶ ሰባ ሁለት ናቸው፤ የሳፋንም ልጆች ሦስት መቶ ሰባ ሁለት#ግሪክ ሰባ. ሊ. “አራት መቶ ሰባ ሁለት” ይላል። ናቸው። 10የሐሬስ ልጆችም ሰባት መቶ አምሳ ስድስት ናቸው። 11የፈሓት ሞዓብ ልጆችም ከሮብአምና#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ኢዮአብ” ይላል። ከኢዮስስ ልጆች ጋራ ሁለት ሺ ስምንት መቶ ዐሥራ ሁለት ናቸው። 12የኤላም ልጆች አንድ ሽህ ሁለት መቶ አምሳ አራት ናቸው፤ የዛጦንም ልጆች ዘጠኝ መቶ ስድሳ ናቸው፤ የኮሮባ ልጆች ሰባት መቶ አምሳ ናቸው፤ የባኒን ልጆችም ስድስት መቶ አርባ ስምንት ናቸው። 13የቤባይ ልጆችም ስድስት መቶ ሠላሳ ሦስት ናቸው፤ የዓዝጋድ ልጆችም ሺህ ሦስት መቶ ሃያ ሁለት ናቸው። 14የአዶኒቃም ልጆች ስድስት መቶ ስድሳ ሰባት ናቸው፤ የበጉዋይ ልጆችም ሁለት ሺህ ስድሳ ሰባት ናቸው፤ የአዲኖስም ልጆች አራት መቶ አምሳ አራት ናቸው። 15የአዝራቅዮ፥#ግሪክ ሰባ. ሊ. “የአጤር አዝራቅዩ ልጆች ዘጠና ሁለት” ይላል። የቄላንና የአዛጦን ልጆች ስድሳ ሰባት ናቸው፤ የአዛሩ ልጆችም አራት መቶ ሠላሳ ሁለት ናቸው። 16የሐናንያም ልጆች መቶ አንድ ናቸው፤ የአሮምና የባሕሴ ልጆች ሦስት መቶ ሃያ ሦስት ናቸው፤ 17የአርስፋሪስት ልጆች አንድ መቶ ዐሥራ ሁለት ናቸው። የበጢሩስ ልጆችም ሦስት ሽህ አምስት ናቸው፤ የኤናውም ልጆች መቶ አምሳ ስምንት#ግሪክ ሰባ. ሊ. የኤናውን ልጆች አይጽፍም። ናቸው። የቤትሎሞን ልጆችም መቶ ሃያ ሦስት ናቸው። 18ከኒጤባስም ልጆች አምሳ አምስት፥ ከኤናጦስም ልጆች መቶ አምሳ ስምንት፥ የቤትሳሞስ ልጆች አርባ ሁለት፥ 19የቀታርቲሐርዮስ ልጆችም ሃያ አምስት፥ የጳሬስና የፎሮግ ልጆች ሰባት መቶ አርባ ሦስት ናቸው፤ 20አካዲያስና አሚዳውያንም አራት መቶ ሃያ ሁለት ናቸው፥ የቂራማና የጋቢስ ልጆች ስድስት መቶ ሃያ አንድ ናቸው። 21የመቃሉንም ልጆች መቶ ሃያ ሁለት፥ ከቤጠሊም ልጆች አምሳ ሁለት፥ የኔፋስም መቶ አምሳ ስድስት ናቸው። 22የቀላምሎምና የሁነስ ልጆች ሰባት መቶ ሃያ አምስት፥ የኤሪካ ልጆች ሦስት መቶ አርባ አምስት፤ #ከግሪክ ሰባ. ሊ. የተገኘ ነው። 23የሰናሐሰም ልጆች ሦስት ሺህ ሦስት መቶ አንድ ናቸው።
24የኢዮስስ ልጆች፥ ካህናቱም#ግሪክ ሰባ. ሊ. “የኢዮስስ ልጅ የኤዱ ልጆች ካህናት” ይላል። ከአናሲብ ልጆች ጋራ ስምንት መቶ ሰባ ሁለት ናቸው። የኤምሩት ልጆችም ሁለት መቶ አምሳ ሁለት#“አንድ ሽህ አምሳ ሁለት” የሚልም የግሪክ ሰባ. ሊ. ዘርዕ ይገኛል። ናቸው። 25የፋሰሩ ልጆችም አንድ ሺህ ሁለት መቶ አርባ ሰባት፥ የካርሚ ልጆች#“የካርሚ ልጆች” ከግሪክ ሰባ. ሊ. የተገኘ ነው። ሽህ ዐሥራ ሰባት ናቸው።
26ሌዋውያን ግን፦ የኢዮስስ የቆድሔሉ፥ የባኑና የሱዱይ ልጆች ሰባ አራት፤ 27መዝሙር የሚዘምሩ የካህናት ልጆች፦ የአሳፍ ልጆች መቶ ሃያ ስምንት፥ 28በረኞች የሰሎም ልጆች፦ የአጤር ልጆች፥ የጤልሞን ልጆች፥ የዓቁብ ልጆች፥ የሐጢጣ ልጆች፥ የሰባይ ልጆች ሁሉም መቶ ሠላሳ ዘጠኝ ናቸው።#“በረኞች” አራት መቶ፥ “የዓቁብ ልጆች” አንድ ሺህ ናቸው የሚል የግእዝ ዘርዕ ይገኛል።
29የቤተ መቅደስ አገልጋዮች፦ የኤሳው ልጆች፥ የሓሱፋ ልጆች፥ የጠብይት ልጆች፥ የቀራስ ልጆች፥ የሲዓ ልጆች፥ የፋዶን ልጆች፥ የሌብና ልጆች፤ የአባጋ ልጆች፥ 30የዐቁድ ልጆች፥ የሐጡ ልጆች፥ የኪጣብ ልጆች፥ የአቀባ ልጆች፥ የሳባዊ ልጆች፥ የሐና ልጆች፥ የቃጡዓ ልጆች፥ የጌዱር ልጆች፤ 31የያሳሩ ልጆች፥ የዴሳን ልጆች፥ የነሒሴቦ ልጆች፥ የካሴባ ልጆች፥ የቀዚራ ልጆች፥ የዖዝያ ልጆች፥ የፋኑሕ ልጆች፥ የአዛራ ልጆች፥ የባስቲ ልጆች፥ የአስና ልጆች፥ የማአኒ ልጆች፥ የነፋሲ ልጆች፥ የአቁፋ ልጆች፥ የአኪባ ልጆች፥ የአሱር ልጆች፥ የፋራቂም ልጆች፥ የባስሊም ልጆች፤ 32የሚዳ ልጆች፥ የኩታ ልጆች፥ የሴርያ ልጆች፥ የባርኩስ ልጆች፥ የሴሬር ልጆች፥ የቶምሔ ልጆች፥ የናሲ ልጆች፥ የአጢፍ ልጆች።
33የሰሎሞን አገልጋዮች ልጆች፦ የአሳፍያት ልጆች፥ የፋሬዳ ልጆች፥ የሐሊ ልጆች፥ የሎዝን ልጆች፥ የያሴዳሔል ልጆች፥ የሳፋት ልጆች፤ 34የሐጋያ ልጆች፥ የፈቀሬተሰባይ ልጆች፥ የሳሮትዮ ልጆች፥ የማሲያስ ልጆች፥ የጋስ ልጆች፥ የአዱስ ልጆች፥ የሱባስ ልጆች፥ የአፌራ ልጆች፥ የባሩዲስ ልጆች፥ የሳፋጥ ልጆች፥ የአሎም ልጆች፤
35እነዚህ ቤተ መቅደሱን የሚያገለግሉ ሁሉና የሰሎሞን አገልጋዮች ልጆች ሁሉ ሦስት መቶ ሰባ ሁለት ናቸው።#“አራት ሺህ ሰባ ሁለት” የሚል የግእዝ ዘርዕ ይገኛል።
36ከቴልሜሬትና ከቴሌርሳስ የወጡት ሁሉ፥ አለቆቻቸውም ካራኃታንና ከሀለር ናቸው። 37ሀገራቸውንና ዘመዳቸውን፥ ከእስራኤልም ወገን መሆናቸውን መናገር አልቻሉም። የጡባን ልጆች፥ የዱዳን ልጆች፥ የነቆዲንም ልጆች ስድስት መቶ አምሳ ሁለት ናቸው።#“ዘጠኝ ሺህ አምሳ ሁለት” የሚል አንዳንድ ዘርዕ ይገኛል።
38ከካህናቱ ወገን የሆኑ፥ የክህነትን ሥራ የሚሠሩ፥ ተመዝግበው ያልተገኙ፦ የሐብያ ልጆች፥ የአቅቦስ ልጆች፥ ከቤርዜሊ ልጆች ወገን በስሙ የተጠራች አውግያን ያገባ የይሆድስ ልጆች ናቸው። 39የዘመዶቹ ትውልድ ቍጥር በተጻፈበት መጽሐፍ ትውልዱን ፈልገው አጡ፤ የክህነት አገልግሎቱንም አስተዉት። 40ነህምያና ሐቴርሳታም፥ የክህነትና የጽድቅ ልብስ የሚለብስ ሊቀ ካህናት እስኪሾሙ ድረስ ከተቀደሰው ነገር ሁሉ እንዳይሰጡት አዘዙአቸው።
41ከዐሥራ ሁለት ዓመት በላይ ያሉት እስራኤል ሁሉ ከሴቶች አገልጋዮቻቸውና ከወንዶች አገልጋዮቻቸው በቀር አርባ ሁለት ሺህ ሦስት መቶ ስድሳ ነበሩ። 42ወንዶችና ሴቶች አገልጋዮቻቸውም ሰባት ሺህ ሦስት መቶ ሠላሳ ሰባት ነበሩ፤ ሴቶችና ወንዶች መዘምራንም ሁለት መቶ አርባ አምስት ነበሩ። 43ግመሎቹም አራት መቶ ሠላሳ አምስት፥#“አራት መቶ አርባ ስድስት ግመሎች” የሚል ዘርዕ ይገኛል። ፈረሶቹም ሰባት ሺህ ሠላሳ ስድስት፥#“ሰባት ሺህ ሦስት መቶ አርባ ስድስት” የሚል የግእዝ ዘርዕ ይገኛል። በቅሎዎችም ሁለት መቶ አርባ አምስት፥ አህዮችም አምስት ሺ አምስት መቶ ሃያ አምስት ነበሩ።
44ከሀገሮቻቸው አለቆችም ዐያሌዎች በኢየሩሳሌም ወዳለው ወደ እግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በደረሱ ጊዜ እንደሚቻላቸው መጠን ቤተ መቅደሱን በቦታው ያቆሙት ዘንድ ጸለዩ። 45ለቤተ መቅደሱ የሥራ ጣጣም አንድ ሺህ ወቄት ወርቅ፥ አምስት ሺህ ወቄት ብርና መቶ የካህናት ልብስ ወደ ግምጃ ቤቱ ያገቡ ዘንድ ተሳሉ።
46ካህናቱም፥ ሌዋውያኑም በኢየሩሳሌምና በአካባቢዋ ከሚኖሩ ሕዝቦችም፥ መዘምራኑ፥ በር ጠባቂዎቹም፥ እስራኤልም ሁሉ በየቦታቸው ይቀመጡ ነበር።
ሥርዐተ አምልኮት እንደገና መጀመሩ
47የእስራኤልም ልጆች በያገራቸው ተቀምጠው ሳሉ በሰባተኛው ወር መባቻ በምሥራቁ በር ዳርቻ ባለው አደባባይ በአንድነት ተሰበሰቡ። 48የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱና ወንድሞቹ ካህናት፥ የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤልና ወንድሞቹም፥ ተነሡ፤ 49በእግዚአብሔር ሰው በሙሴ መጽሐፍ እንደ ተጻፈ እንደ ሕጉ መሥዋዕት ይሠዉ ዘንድ ለእስራኤል ፈጣሪ ለእግዚአብሔር መሠዊያውን አዘጋጁ። 50ሌሎችም የምድር አሕዛብ ከእነርሱ ጋር ተሰብስበው በቦታቸው በመሥዊያው አጠገብ ተዘጋጁ፤ ተሰልፈው ነበርና፤ ከዚህም በኋላ የምድር አሕዛብን አሸነፏቸው፤ በየጊዜው የሚደረገውንም የነግሁንና የሠርኩን መሥዋዕት ቍርባኑንም ለእግዚአብሔር አቀረቡ። 51በሕግ እንደ ተጻፈ የዳስ በዓልን አደረጉ፤ በየዕለቱም እንደ ቀድሞው መሥዋዕቱን ሠዉ። 52ዳግመኛም የዘወትሩን ቍርባንና የሰንበቱን መሥዋዕት፥ የመባቻዎችንና የተቀደሱትን በዓላት መሥዋዕት አቀረቡ። 53ለእግዚአብሔርም ስእለት የተሳሉ ሰዎች ሁሉ ከሰባተኛው ወር መባቻ ጀምሮ መሥዋዕቱን ለእግዚአብሔር ያቀርቡ ጀመሩ፤ የእግዚአብሔርም ቤተ መቅደስ ገና አልተሠራም ነበር። 54ደንጊያ ለሚያለዝቡና እንጨት ለሚጠርቡ ሰዎችም ወርቅና ብር ሰጧቸው፤ ለምግባቸውም መብሉንና መጠጡን ሰጧቸው። 55የሲዶናና የጢሮስ ሰዎችንም የዋንዛውን እንጨቶች ከሊባኖስ በኢዮጴ ባሕር በኩል በመርከብ ያገቡላቸው ዘንድ አዘዟቸው፤ ከፋርስ ንጉሥ ከቂሮስ ዘንድም የትእዛዝ ደብዳቤ ጻፉላቸው።
የቤተ መቅደሱ መሠረት እንደ ተጣለ
56ከዚህ በኋላ ወደ ኢየሩሳሌም ወደ እግዚአብሔር ቤት በደረሱ በሁለተኛው ዓመት በሁለተኛው ወር የሰላትያል ልጅ ዘሩባቤል፥ የኢዮሴዴቅ ልጅ ኢያሱ፥ ወንድሞቻቸው ካህናቱና፥ ሌዋውያኑም፥ ከምርኮ ወደ ኢየሩሳሌም የተመለሱትም ሁሉ ቤተ መቅደስን ይሠሩ ዘንድ ጀመሩ። 57ወደ ኢየሩሳሌምና ወደ ይሁዳ በገቡ በሁለተኛው ዓመት በሁለተኛው ወር መባቻ የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስን መሠረት አኖሩ። 58#“ግሪክ ሰባ. ሊ. “ከሃያ ዓመት ጀምሮ ያሉትን ሌዋውያንን ..” ይላል።ሌዋውያንንም በቤተ እግዚአብሔር ሥራ ላይ ሾሟቸው፤ ኢያሱና ልጆቹ፥ ወንድሞቹም፥ ወንድሙ አድያምያልም፥ የኢያሱ ልጅ ሄሜዴቦን፥ የኤልያዳን ልጅ የይሁዳ ልጆች፥ ከልጆቹና ከወንድሞቹ ጋር ሌዋውያንም ሁሉ የእግዚአብሔርን ቤት ይሠሩ ዘንድ የሥራ አለቆች ሆነው በአንድነት ተሾሙ።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “አናጢዎችም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ሠሩ” የሚል ይጨምራል። 59ካህናቱም ልብሰ ተክህኖውን ለብሰው፥ መሰንቆውንና መለከቱን ይዘው ቆሙ። የአሳፍ ልጆች ሌዋውያንም እግዚአብሔርን በጸናጽል ያመሰግኑ ነበር። 60በእሴይ ልጅ በእስራኤል ንጉሥ በዳዊት መዝሙርም ያመሰግኑት ነበር። 61ጮኸውም እያስተዛዘሉ እግዚአብሔርን ያመሰግኑ ነበር፤ ምስጋናው ለዘለዓለም ነውና፥ ቸርነቱም በእስራኤል ሁሉ ላይ ነውና። 62የእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ በመነሣቱ ሕዝቡ ሁሉ መለከቱን እየነፉ፥ ከፍ ባለ ድምፅም እየጮሁ እግዚአብሔርን አመሰገኑ። 63ቀድሞ በዚያ በያገራቸው ይኖሩ ከነበሩ ከካህናትና ከሌዋውያንም የዚያን ቤት ሥራውን ቀድሞ ያዩት አለቆችም በታላቅ ድምፅ ፈጽመው እያለቀሱ መጡ። 64ሕዝቡም እስኪሰማ ድረስ ደስ ብሏቸው ቀንደ መለከት የሚነፉ ብዙ ሰዎች ነበሩ። 65በሩቅ እስኪሰማ ድረስ በታላቅ ድምፅ ቀንደ መለከት የሚነፉ ብዙ ሰዎች ነበሩና ከሕዝቡ ልቅሶ የተነሣ የመለከቱን ድምፅ አልሰሙም። 66የይሁዳና የብንያም ወገኖች ጠላቶችም ያን በሰሙ ጊዜ የቀንደ መለከቱ ድምፅ ምን እንደ ሆነ ያውቁ ዘንድ መጡ። 67ከምርኮ የተመለሱ እስራኤልም የፈጣሪያቸው የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ እንደሚሠሩ ባወቁ ጊዜ፥ 68ወደ ዘሩባቤልና ወደ ኢያሱ ወደ አገሮቻቸውም ሹሞች ሄደው እንዲህ አሏቸው፥ “እኛ ከእናንተ ጋራ እንሥራ፥ 69የአሦር ንጉሥ ስልምናሶር#ግሪክ ሰባ. ሊ. “አስባሳሬት ንጉሠ አሦር” ይላል ግእዙ “ዐስበ ቀፈት ንጉሠ ፋርስ” ይላል። ወደዚህ ካመጣን ጀምሮ እንደ እናንተ ለፈጣሪያችሁ እንገዛለንና፥ መሥዋዕቱንም ለእርሱ እንሠዋለንና።” 70ዘሩባቤልና ኢያሱም፥ የየሀገሮቻቸው ሹሞችም እንዲህ አሉአቸው፥ “የእስራኤልን ጌታ የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት ለእኛም፥ ለእናንተም አይገባንም፤ 71ሐጌ እንደ ተናገረ፥ የፋርስ ንጉሥ ቂሮስም እንዳዘዘን የእስራኤልን ጌታ የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ እኛ ለብቻችን እንሠራለን።” 72የሚመክቱ ያገሩ ሰዎች አሕዛብ ግን በይሁዳ ያሉትን ፈጽመው ተሰብስበው ተዋጓቸው። 73አወኳቸው፤ ሥራቸውንም አስቆሙ፤ በንጉሡ በቂሮስ ዘመንም ሁሉ እንዳይሠሩ ከለከሏቸው፤ እስከ ዳርዮስ ሁለተኛ ዓመተ መንግሥትም ድረስ ሥራውን አስተዉአቸው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዕዝራ ካልእ 5: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ
![None](/_next/image?url=https%3A%2F%2Fimageproxy.youversionapi.com%2F58%2Fhttps%3A%2F%2Fweb-assets.youversion.com%2Fapp-icons%2Fam.png&w=128&q=75)
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ