መጽሐፈ ዕዝራ ካልእ 2
2
1በፋርስ ንጉሥ በቂሮስ መንግሥት በመጀመሪያዪቱ ዓመት እግዚአብሔር በነቢዩ በኤርምያስ አፍ የተናገረው ቃል ደረሰ። 2እግዚአብሔርም የፋርስን ንጉሥ የቂሮስን መንፈስ አነሣሣ፤ በመንግሥቱም ሁሉ ዐዋጅ ነገረ፤ እንዲህም ብሎ ጻፈ። 3የፋርስ ንጉሥ ቂሮስ እንዲህ ይላል፥ “የእስራኤል አምላክ ልዑል እግዚአብሔር እኔን ለዘለዓለም አነገሠኝ። 4በይሁዳ ባለችው በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስን እሠራለት ዘንድ አዘዘኝ፤ 5ስለዚህ ከእናንተ ውስጥ ከሕዝቡ ወገን የሆነ ቢኖር እግዚአብሔር ከእርሱ ጋር ይሁን፤ በይሁዳ ወደ አለች ወደ ኢየሩሳሌም ይውጣ፤ ለእስራኤል ጌታ ለእግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስን ይሥራ።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “እግዚአብሔር በኢየሩሳሌም ያድራልና” የሚል ይጨምራል። 6በያገራችሁ ያላችሁ ሁሉ በየአውራጃችሁ ወርቁንና ብሩን ርዱ። 7እናንተም ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ፈረሱንና ከብቱን ስእለት ካለው ሁሉ ጋር ጨምሩ።
8“የይሁዳና የብንያም ሀገሮች መሳፍንትም በየነገዳቸው፥ ሕዝቡም፥ ካህናቱም፥ ሌዋውያኑም፥ እግዚአብሔርም ልቡናውን ያነሣሣለት ሁሉ ይውጣ፤ በኢየሩሳሌም ያለውንም የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ ይሥራ። 9ባውራጃቸው ያሉም በወርቅና በብር፥ በፈረስና በከብት ሁሉ፥ ስእለት ያለባቸውም፥ ልቡናውም የወደደ ሁሉ ይርዷቸው።”
10ንጉሥ ቂሮስም ናቡከደነፆር ከኢየሩሳሌም ወስዶ በጣዖቶቹ ቤት ያኖረውን የእግዚአብሔርን ንዋየ ቅድሳት አወጣ። 11የፋርስ ንጉሥ ቂሮስም ንዋየ ቅዱሳቱን ባወጣ ጊዜ ለጠባቂው ለሚትረዳጡ ሰጠው፥ 12ለይሁዳ የተሾመው ሰልምናስም#“ሰሳብሳር፥ ሸሻባፃር፥ ሰናባሳር” የሚል ዘርዕ አለ። ከእርሱ ተቀበለ፤ 13ቍጥሩም እንዲህ ነው፦ የወርቁ ወጭት አንድ ሺህ፥#ግእዙ “ሠላሳ” ይላል። የብሩም ወጭት አንድ ሺህ ነው። የብር ሳህኖች ሃያ ዘጠኝ፥ የወርቅ ጽዋዎችም ሠላሳ፥ የብርም ጽዋዎች ሁለት ሺህ አራት መቶ ዐሥር፥ ሌሎች ዕቃዎች ግን አንድ ሺህ ነበሩ። 14የተመለሰውም የወርቁና የብሩ ዕቃ ሁሉ ተዳምሮ አምስት ሺህ አራት መቶ ስድሳ ዘጠኝ ነበር። 15ስልምናሶርም ከምርኮኞቹ ጋር ከባቢሎን ወስዶ ወደ ኢየሩሳሌም አገባው።
በግንቡ ሥራ ላይ የደረሰ ተቃውሞ
16ከእነርሱም ውስጥ የፋርስ ንጉሥ አርጤክስስ በይሁዳና በኢየሩሳሌም አውራጃዎች ያስቈጠራቸው አሉ፤ ቤልሞስና ሚጥራዳጢ፥ ጠቢልዮስና ራቲሞስ፥ ቤሔልጤሞስና ጸሓፊው ሲሳዮስ፥#ሀ. ቤሴልሞስ ለ. ሮኡሞስ ሐ. ሳማሴዎስ። ከነዚህም በታች ያሉ በሰማርያ የሚኖሩ ሁሉ፥ በሌላም ሀገር ያሉ ሁሉ እንዲህ ብለው መልእክት ጻፉ። 17“ለጌታችን ለንጉሡ ለአርጤክስስ፦ ከብላቴኖችህ፥ ከታሪክ ጸሓፊህ ከራቲሞስና ከጸሓፊው ከሰሜልዮስ#ሮኡሞስ... ሳማሴዎስ ከእነርሱ በታች ከተሾሙት ሁሉና በቄሌ-ሶርያና በፊኒቄ ከሚኖሩ ሁሉ፦ 18አሁንም ጌታችን ንጉሥ ሆይ፥ ይህን ዕወቅ፤ ከእናንተ ወደ እኛ የመጡ አይሁድ ወደ ኢየሩሳሌም ሄደው፥ ክፉና ከዳተኛ ከተማን ይገነባሉ፤ የገበያ ቦታዎችዋንና ቅፅሮችዋን፥ ቤተ መቅደስዋንም ያድሳሉ። 19ያችም ከተማ ከተሠራች፥ ቅፅሯም ካለቀ፥ ከዚያ በኋላ ግብር አይገብሩም፤ ዳግመኛም መንግሥታችንን ይቀማሉ። 20ቤተ መቅደስንም አሳምረው ይሠራሉ። አሁንም ስለዚህ ቸል አትበል። 21በአባቶቻችሁ የታሪክ መጽሐፍ ይፈልጉ ዘንድ ወደ ንጉሡ ወደ ቂሮስ ላክ። 22ያች ከተማ ነገሥታቱን የምትከዳና ከተሞችን እንደምታውክ፥ ስለዚህ የተጻፈ ታገኛለህ። 23አይሁድም ከጥንት ጀምሮ ከዳተኞች እንደ ሆኑ ተጽፎ ታገኛለህ፤ ስለዚህም ያች ከተማ ጠፍታ ነበር። 24አሁንም ጌታችን ንጉሥ ሆይ፥ እንነግርሃለን፤ ያች ከተማ ከተሠራች፥ ቅጽሮችዋም ከተፈጸሙ በኋላ ወደ ቄሌ-ሶርያና ወደ ፊንቄ አያሳልፏችሁም።”
25ከዚህ በኋላ ንጉሡ ለጻፈለት ለታሪክ ጸሓፊው ለራቲሞስና ለቤሔልማቴም፥ ለጸሓፊው ለሳሚልዮስም በሰማርያና በፊኒቂስ ለሚኖሩ፥ ከእነርሱ በታች ላሉ፥ ለቀሩትም እንደ ጻፉለት እንዲህ የምትል ደብዳቤን ጻፈላቸው። 26“እኔም የላካችሁልኝን ደብዳቤ አንብቤ ይፈልጉ ዘንድ አዘዝሁ፤ ያቺም ከተማ ከጥንት ጀምሮ ነገሥታቱን የምትከዳ እንደ ሆነች አገኘሁ። 27ሰዎችም ከዳተኞች እንደ ነበሩ፥ ሥራቸውም ጦርነት እንደ ነበረ፥ የኢየሩሳሌምም ነገሥታት ጠንካሮችና ክፉዎች እንደ ነበሩ፥ ቄሌ-ሶርያንና ፊኒቄን እንደ ገዙና እንደገበሩላቸው አገኘሁ። 28አሁንም እነዚያን ሰዎች ያቺን ከተማ መሥራትን እንዲከለክሏቸው፥ 29ነገሥታትም ይደክሙ ዘንድ ክፋትን እንዳታበዛ በውስጧ ምንም የሚሠራ እንዳይኖር እነሆ አዘዝሁ።”
30ከዚህ በኋላ ራቲሞስና ጸሓፊው ስልምዮስ፥ ከእነዚህም በታች ያሉት ንጉሡ አርጤክስስ የጻፋትን ያችን መልእክት ባነበቧት ጊዜ ከብዙ ሰዎች ጋር በብዙ ችኮላ ወደ ኢየሩሳሌም ፈረሶቻቸውን አስነሡ፤ የሚሠሩትንም ይከለክሉ ጀመሩ። 31የኢየሩሳሌም ቤተ መቅደስ ሥራም እስከ ፋርስ ንጉሥ ዳርዮስ ሁለተኛዪቱ ዘመነ መንግሥት ድረስ ቆመ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዕዝራ ካልእ 2: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ