መጽሐፈ ዕዝራ ካልእ 3
3
የሦስቱ ጠባቂዎች ውድድር
1ንጉሡ ዳርዮስም በመንግሥቱ ላሉ ሁሉ ለቤተ ሰዎቹ፥ ለሜዶንና ለፋርስ መኳንንት ሁሉ፥ 2ለመሳፍንቱ ሁሉ፥ በሥሩ ለሚገኙ ከሕንድ እስከ ኢትዮጵያ ባሉ መቶ ሃያ ሰባት ግዛቶች ላሉ አዛዦችና ሹሞች ሁሉ ታላቅ በዓል አደረገ። 3በልተውና ጠጥተውም ጠገቡ፤ ከዚህም በኋላ ወደ ቤታቸው ገቡ፤ ንጉሡ ዳርዮስም ወደ እልፍኙ ገብቶ ተኛ።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ግን ወዲያው ነቃ” የሚል ይጨምራል።
4ንጉሡንም የሚጠብቁት ሦስት ጐልማሶች ራስ ጠባቂዎች ነበሩ። እርስ በርሳቸውም እንዲህ ተባባሉ፦ 5“ሁላችን የሚያስጐመጅና የሚወደድ አንዳንድ ቃል አሻሽለን እንናገር ዘንድ ኑ፤ ነገሩ በጥበብ ከባልንጀራው ለተሻለለት ንጉሡ ዳርዮስ ብዙ ስጦታ ይስጠው፤ የአሸናፊነቱንም ዋጋ ይስጠው። 6ነጭ ሐርም ያልብሰው፤ በወርቅ ጽዋም ይጠጣ፤ በወርቅ አልጋም ይተኛ፤ በወርቅ ሰረገላም ላይ ይቀመጥ፤ ከተልባ እግርም የተሠራ መጠምጠሚያ በራሱ ላይ ያድርግ፤ በአንገቱም ላይ ዝርግፍ ወርቅ ይሰር። 7ስለ ጥበቡም ከንጉሡ ቀጥሎ ይቀመጥ፤ የንጉሡም ዘመድ ይሁን።”
8ከዚህም በኋላ ሁሉም የየራሳቸውን ቃል ጻፉ፤ አትመውም ከንጉሡ ከዳርዮስ መከዳ በታች አኖሩት። 9እንዲህም አሉ፥ “ንጉሡ ከዕንቅልፉ በነቃ ጊዜ ይህቺን ደብዳቤ እንሰጠዋለን፤ ንጉሡና ሦስቱ የፋርስ ሹሞቹም በቃሉ ለተወደደውና ብልህ ለሆነው ይፍረዱለት።” 10አንደኛው “ወይን ያሸንፋል” ብሎ ጻፈ። 11ሁለተኛውም “ንጉሥ ያሸንፋል” ብሎ ጻፈ። 12ሦስተኛውም “ሴቶች ያሸንፋሉ፤ ከሁሉም ይልቅ እውነት ታሸንፋለች” ብሎ ጻፈ።
13ከዚህም በኋላ ዳርዮስ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ንጉሡ” ይላል። በነቃ ጊዜ ያቺን መጽሐፍ አንሥተው ሰጡት፤ አነበባትም። 14በሜዶንና በፋርስ ያሉ አዛዦችን ሁሉ፥ መሳፍንቱንና ሹሞቹን፥ አለቆቹንና መኳንንቱንም ወደ አዳራሹ ይጠሩ ዘንድ ላከ፤ 15በአጠገቡም ተቀምጠው ያችን መጽሐፍ በፊታቸው አስነበቧት። 16እርሱም፥ “እነዚያን ጐልማሶች ሰዎች ጥሯቸው፤ እነርሱ ራሳቸው ነገራቸውን ይናገሩ” አለ፤ ጠርተውም አገቡአቸው።
ስለ ወይን አሸናፊነት የቀረበው ሐተታ
17እንዲህም አላቸው፥ “ነገራችሁን ተናገሩ፥” ወይን ያሸንፋል ብሎ መጀመሪያ የተናገረውም ይናገር ጀመር። 18እንዲህም አለ፥ “እናንተ ሰዎች፥ ወይን የሚጠጣውን ሰው ሁሉ እንደሚያሸንፈው፥ አእምሮውንም እንደሚያሳጣው አስተውሉ። 19የንጉሡንና የድኃ አደጉን፥ የባሪያዉንና የነጻዉን፥ የድኃውንና የባለጸጋውን ልቡና አንድ ያደርገዋል። 20የሰውን ሁሉ ልቡና ወደ ደስታ መልሶ ደስ ያሰኛቸዋል፤ ኀዘኑንም ሁሉ አያስቡትም፤ ጭንቀቱንም ሁሉ አያስቡትም። 21የሰውን ሁሉ ልቡና ባለ ጸጋ ያደርገዋል፤ ንጉሡንም አያስቡትም፤ ፈጣሪያቸውንም አያስቡትም #“ፈጣሪያቸውን አያስቡትም” እና “ከባድ ነገር” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ሰውንም ሁሉ ከባድ ነገር ያናግረዋል። 22በጠጡትም ጊዜ ወዳጅ ወዳጁን፥ ወንድምም ወንድሙን ይረሳዋል፥ ሾተላቸውንም ያማዝዛቸዋል። 23ከስካራቸውም በነቁ ጊዜ ያደረጉትን አያስቡትም። 24እናንተ ሰዎች፥ በግድ እንዲህ የሚያደርገው ወይን አያሸንፍምን?” ከዚህም በኋላ እርሱ እንዲህ ብሎ ተናግሮ ዝም አለ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዕዝራ ካልእ 3: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ