መጽሐፈ ዕዝራ ካልእ 1
1
1ኢዮስያስ ለፈጣሪው የፋሲካውን በግ ወደ ኢየሩሳሌም አመጣ፤ በመጀመሪያው ወርም በዐሥራ አራተኛው ቀን የፋሲካውን በግ ሠዋ። 2ካህናቱንም የአገልግሎት ልብሳቸውን አልብሶ አቆማቸው፤ በእግዚአብሔርም ቤተ መቅደስ በየሰሞናቸው ሠራቸው። 3#ግሪክ ሰባ. ሊ. “የእስራኤል የቤተ መቅደስ አገልጋዮች ሌዋውያንን ራሳቸውን እንዲያነጹና የዳዊት ልጅ ሰሎሞን በሠራው ቤተ መቅደስ የጌታን ቅዱስ ታቦት እንዲያስቀምጡ ነገራቸው” ይላል።ሌዋውያንንም አላቸው፥ “ለእስራኤል ካህናት ተገዙ፤ የንጉሡ የዳዊት ልጅ ሰሎሞን በሠራው ቤተ መቅደስም በእግዚአብሔር ታቦት ቅድስና ሥርዐት አክብሯቸው። 4ታቦቱንም በጫንቃችሁ መሸከም አይገባችሁም። አሁንም ፈጣሪያችን እግዚአብሔርን አምልኩት፤ የእስራኤልንም ሕዝብ አገልግሉ። 5እንደ እስራኤል ንጉሥ እንደ ዳዊት መጽሐፍና እንደ ልጁ ሰሎሞንም ገናናነት በየሀገራችሁና በየነገዳችሁ ተዘጋጁ፤ ሌዋውያንም በወንድሞቻችሁ በእስራኤል ልጆች ፊት በቤተ መቅደስ በየቦታችሁና በየሀገራችሁ ግዛት በየሹመታችሁ ቁሙ። 6የፋሲካውንም በግ ሠዉ፤ ለወንድሞቻችሁም መሥዋዕቱን አዘጋጁ፤ ለሙሴ በተሰጠው በእግዚአብሔርም ሕግ ፋሲካን አድርጉ።”
7ኢዮስያስም በዚያ ለነበሩ ሰዎች ሠላሳ ሺህ ፍየሎችንና በጎችን፥ ሦስት ሺህ በሬዎችንም ሰጣቸው፤ እንደዚሁም ለሕዝቡ፥ ለካህናቱና ለሌዋውያኑም ከንጉሥ ቤት አዝዞ ሰጠ። 8የቤተ መቅደሱም ሹሞች ኬልቅያስ፥ ዘካርያስና ሲሉያስ ለካህናቱ ለፋሲካ በዓል ሁለት ሺህ ስድስት መቶ በጎችንና ሦስት መቶ በሬዎችን ሰጧቸው። 9መሳፍንቱም ኢኮንያስና ሳሚያስ፥ ወንድሙ ናትናኤልና ሲብያስ፥ ኪያሎስና ኢዮራም ለሌዋውያን ለፋሲካቸው ሺህ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “አምስት ሺህ” ይላል። በጎችንና ሰባት መቶ በሬዎችን ሰጧቸው።
10ካህናቱና ሌዋውያኑም እንደ ሕጉ እንዲሁ መልካም አደረጉ፤ ቂጣውንም በየነገዳቸው ተመገቡ። 11በሙሴ መጽሐፍም እንደ ተጻፈ በሕዝቡ ፊት በየአባቶቻቸው ሹመት መሥዋዕቱን ለእግዚአብሔር አቀረቡ። 12በነጋውም እንደዚሁ እንደ ሥርዐታቸው የፋሲካውን በግ በእሳት ሠዉ፤ መሥዋዕቶችንም በጋንና በብረት ምጣድ አበሰሉ። 13ለሕዝቡም ሁሉ በጎ መዓዛ ያለውን መሥዋዕት ሠሩላቸው፤ ከዚህም በኋላ ለራሳቸውና ለወንድሞቻቸው ለአሮን ልጆች ካህናት አዘጋጁላቸው።
14ካህናቱ ግን ቀኑ እስኪመሽ ድረስ የሰባውን መሥዕዋት ሠዉ፤ ሌዋውያኑም ለራሳቸውና ለወንድሞቻቸው ለአሮን ልጆች ሠዉ። 15መዘምራኑ የአሳፍ ልጆችም ዳዊት በሠራው ሥርዐት በሹመታቸው ነበሩ፤ ከንጉሡ የተሾሙ አሳፍና ዘካርያስ፥ ዐዲኑስም ነበሩ። 16የበሩ ሁሉ ጠባቂዎችም ነበሩ፤ ከሰሞኑም የሚያጓድል አልነበረም፤ ወንድሞቻቸው ሌዋውያን ያዘጋጁላቸው ነበርና። 17ያንጊዜም የእግዚአብሔርን መሥዋዕት አቅርበው ጨረሱ። 18ንጉሡ ኢዮስያስ እንዳዘዘም ፋሲካቸውን አደረጉ፤ ወደ እግዚአብሔርም መሠዊያ መሥዋዕታቸውን አቀረቡ።
19በእነዚያም ወራቶች የነበሩ የእስራኤል ልጆች ፋሲካንና የቂጣውን በዓል ለሰባት ቀን አደረጉ። 20ከነቢዩ ከሳሙኤልም ዘመን ወዲህ በእስራኤል ዘንድ እንደ እርሱ ያለ በዓል አልተደረገም። 21የእስራኤልም ነገሥታት ሁሉ ኢዮስያስ እንዳደረገው ፋሲካን አላደረጉም፤ ሌዋውያንና ካህናት፥ አይሁድና ወደ ኢየሩሳሌም መጥተው በዚያ የነበሩ እስራኤልም ሁሉ አላደረጉም። 22ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት ይህን ፋሲካ አደረገ።
የኢዮስያስ ዘመነ መንግሥት ፍጻሜ
23የኢዮስያስም ሥራው እግዚአብሔርን መፍራት በተመላበት ልቡና በፈጣሪው ፊት የቀና ነበር። 24በቀድሞው ዘመን ከአሕዛብና ከመንግሥታት ሁሉ እግዚአብሔርን ፈጽመው ስለ በደሉትና ስለ አሳዘኑት ሰዎች እንደ ተጻፈ እግዚአብሔር በእስራኤል ላይ ቃሉን አጸና። 25ከዚህም ከኢዮስያስ ሥራ ሁሉ በኋላ፦ የግብፅ ንጉሥ ፈርዖን በኤፍራጥስ ወንዝ በከርከሚስ ሠራዊቱን ይዞ ዘመተ፤ ኢዮስያስም ወጥቶ ተቀበለው። 26የግብፅ ንጉሥም፥ “የይሁዳ ንጉሥ ሆይ፥ እኔ ካንተ ጋራ ምን አለኝ?” ብሎ ላከበት። 27“ከጌታ ከእግዚአብሔር ዘንድ በአንተ ላይ የተላክሁ አይደለም፥ እኔ የምወጋ ኤፍራጥስን ነውና፥ አሁንም እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ነው፤ እግዚአብሔር በእኔ ዘንድ አለ፤ እርሱም ይረዳኛል፤ ገለል በል፤ ከእግዚአብሔርም ጋር አትከራከር” አለው። 28ኢዮስያስም በሠረገላዎቹ ሆኖ ገለል አልልም አለ፤ ይዋጋም ዘንድ ጀመረ፤ ከእግዚአብሔርም አፍ በነቢዩ በኤርምያስ የተነገረውን ቃል መስማት እንቢ አለ። 29ነገር ግን መጊዶስ በሚባል ምድረ በዳ ይዋጋቸው ዘንድ ጸና፤ አለቆችም ወደ ንጉሡ ወደ ኢዮስያስ ወረዱ። 30ንጉሡም ብላቴኖቹን አላቸው፥ “እጅግ ደክሜአለሁና ከሰልፉ ውስጥ አውጡኝ፥” ብላቴኖቹም ወዲያውኑ ከሰልፉ ውስጥ አወጡት። 31በሌላ ሰረገላውም ተቀምጦ ወደ ኢየሩሳሌም ገባ፤ በዚያም ሞተ፤ በአባቱ መቃብርም ተቀበረ። 32በይሁዳም ሁሉ ለኢዮስያስ አለቀሱለት፤ ኤርምያስም ለኢዮስያስ አለቀሰለት፤ እስከዚች ቀን ድረስም ወንዶች ሁሉ ከሴቶች ጋር አለቀሱለት፤ ለዘለዓለምም እንዲሁ ያደርጉ ዘንድ ለእስራኤል ወገኖች ሥርዐት ሆኖ ተሰጠ። 33ይህም በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ተጻፈ፤ ኢዮስያስም የሠራው ሥራ ሁሉ፥ ክብሩም፥ የእግዚአብሔርንም ሕግ ማወቁ፥ በፊትም፥ በኋላም የሠራው ሥራ ሁሉ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ተጽፏል።
የመጨረሻዎቹ የይሁዳ ነገሥታት
34ሕዝቡም የኢዮስያስን ልጅ ኢዮአክስን ወስደው በተወለደ በሃያ ሦስት ዓመት ዕድሜው በአባቱ በኢዮስያስ ፋንታ አነገሡት። 35#2ነገሥት ምዕ. 23 ቍ. 31 “ለእስራኤል” እይልም።ለእስራኤልም በኢየሩሳሌም ሦስት ወር ነገሠ፤ የግብፅ ንጉሥም በኢየሩሳሌም ከመንግሥት አወረደው። 36ሕዝቡንም ሁለት መቶ መክሊት ብርና አንድ መክሊት ወርቅ አስገበራቸው።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “አንድ መቶ መክሊት ብር” ይላል። 37የግብፅ ንጉሥም ወንድሙን ኢዮአቄምን የይሁዳ ንጉሥ አድርጎ በኢየሩሳሌም አነገሠው። 38ኢዮአቄምም መሳፍንቱን አሰራቸው፤ ወንድሙ ዛርዮንንም ይዞ ወደ ግብፅ አገባው።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ከግብፅ መለሰው” ይላል። 39ኢዮአቄምም በይሁዳ በኢየሩሳሌም በነገሠ ጊዜ ዕድሜው ሃያ አምስት ዓመት ሆኖት ነበር፤ በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ። 40ከዚህም በኋላ የባቢሎን ንጉሥ ናቡከደነፆር ወደ እርሱ ዘመተ፤ በብረት ሰንሰለትም አስሮ ወደ ባቢሎን ሰደደው። 41ናቡከደነፆርም የእግዚአብሔርን ንዋየ ቅድሳት ወስዶ ወደ ባቢሎን አገባው፤ በጣዖቱም ቤት አኖረው። 42ይህም በይሁዳ ነገሥታት ታሪክ መጽሐፍ ተጽፎአል።#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ስለ ኢዮአቄም የተነገረው ርኵሰቱና ክፋቱ ሁሉ...” ይላል 43ከዚህም በኋላ ልጁ ኢኮንያስ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ኢዮአኪም” ይላል። ነገሠ፤ ዕድሜውም ዐሥራ ስምንት ዓመት ነበረ። 44ሦስት ወር ከዐሥር ቀን በኢየሩሳሌም ነገሠ፤ እርሱም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ አደረገ።
45ከዓመትም በኋላ ናቡከደነፆር ከእግዚአብሔር ንዋየ ቅድሳት ጋር ልኮ ወደ ባቢሎን አገባው። 46ሴዴቅያስንም በተወለደ በሃያ አንድ ዓመቱ በኢየሩሳሌምና በይሁዳ አነገሠው፤ ዐሥራ አንድ ዓመትም ነገሠ። 47በእግዚአብሔርም ፊት ክፉ አደረገ፤ በነቢዩ በኤርምያስ አፍ ከተነገረው ከእግዚአብሔርም ቃል የተነሣ አልፈራም። 48ንጉሡ ናቡከደነፆርም በእግዚአብሔር ስም አማለው፤ እርሱ ግን ከዳው፤ አንገቱንም አደነደነ፤ ልቡናውንም አስታበየ፤ የእስራኤል ፈጣሪ የእግዚአብሔርንም ሕግ ተላለፈ። 49የሕዝቡና የካህናቱ መሪዎችም ብዙ ተላለፉ፤ ከአሕዛብም ርኵሰት ይልቅ እጅግ በደሉ፤ በኢየሩሳሌምም የተቀደሰችውን የእግዚአብሔርን መቅደስ አሳደፉ።
የኢየሩሳሌም ጥፋት
50የአባቶቻቸው አምላክ እግዚአብሔርም ይገሥጻቸውና ይመልሳቸው ዘንድ መልእክተኛውን ላከ፤ ለእነርሱና ለመቅደሳቸው ይራራልና። 51እነርሱ ግን በመልእክተኞቹ ዘበቱባቸው፤ እግዚአብሔርም በተናገራቸው ጊዜ በሕዝቡ እስኪቈጣ ድረስ በነቢያት ይስቁባቸው ነበር። 52ጣዖቱን እጥፍ አድርገው ያመልኩ ነበርና የከላውዴዎን ክፍል የአሦር ነገሥታትም ይዘምቱባቸው ዘንድ አዘዘ። 53መጥተውም በቤተ መቅደሱ አደባባይ ጐልማሶቻቸውን በሰይፍ ገደሉ፤ ለጐልማሳውም፥ ለቆንጆዋም፥ ለትልቁም፥ ለትንሹም ቢሆን አልራሩም፤ ሁሉንም በእጃቸው አሳልፎ ሰጣቸው። 54የእግዚአብሔርንም ንዋየ ቅድሳት ትልቁንም ትንሹንም ሁሉ፥ የእግዚአብሔርንም ታቦት፥ የንጉሡንም ቤት ዕቃ ሁሉ ዘርፈው ወደ ባቢሎን ወሰዱ። 55የእግዚአብሔርንም ቤት አቃጠሉ፤ የኢየሩሳሌምንም ቅጽሯን አፈረሱ፤ ግንቧንም በእሳት አቃጠሉ። 56ያማረውንም ዕቃዋን ሁሉ አጠፉ፤ ከጦር የቀሩትንም ማርከው ወደ ባቢሎን ወሰዱአቸው። 57በነቢዩ በኤርምያስ አፍ የተነገረው የእግዚአብሔር ቃል ይደርስ ዘንድ፥ ፋርሳውያን መግዛት እስከ ጀመሩበት ድረስ ለእርሱና ለልጆቹ አገልጋዮች ሆኑ። 58ምድርም በማረፍዋ ደስ ይላታል፤ በተፈታችበትም ዘመን ሁሉ ሰብዓው ዘመን እስኪፈጸም ድረስ ታርፋለች።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዕዝራ ካልእ 1: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ