እንደ ንጉሡም እንደ ኢዮስያስ ትእዛዝ በእግዚአብሔር መሠዊያ ላይ የሚቃጠለውን መሥዋዕት ያቀርቡ ዘንድ፥ ፋሲካውንም ያደርጉ ዘንድ፥ የእግዚአብሔር አገልግሎት ሁሉ በዚያ ቀን ተዘጋጀ። የተገኙትም የእስራኤል ልጆች በዚያ ቀን ፋሲካውን፥ ሰባት ቀንም የቂጣውን በዓል አደረጉ። ከነቢዩም ከሳሙኤል ዘመን ጀምሮ እንደዚህ ያለ ፋሲካ በእስራኤል ዘንድ ከቶ አልተደረገም፤ ከእስራኤልም ነገሥታት ሁሉ ኢዮስያስና ካህናቱ፥ ሌዋውያኑም፥ በዚያም የተገኙ የይሁዳና የእስራኤል ሰዎች ሁሉ፥ በኢየሩሳሌምም የሚኖሩት እንዳደረጉት ያለ ፋሲካ ያደረገ የለም። ይህም ፋሲካ ኢዮስያስ በነገሠ በዐሥራ ስምንተኛው ዓመት ተደረገ። 19 ‘ሀ’ ንጉሡ ኢዮስያስ ካህኑ ኬልቅያስ በእግዚአብሔር ቤት ባገኘው መጽሐፍ የተጻፉትን ቃላት ሁሉ ለመጠበቅ አስማተኞችንና ጠንቋዮችን፥ ሟርተኞችንና በኢየሩሳሌም ምድርና በይሁዳ የሚገኙትን ምስሎችና ቃሪያሲም የተባሉ ጣዖታትን በእሳት አቃጠለ። 19 ‘ለ’ እንደ ሙሴ ሕግ ሁሉ በፍጹም ልቡ፥ በፍጹም ነፍሱ፥ በፍጹም ኀይሉ ከእርሱ በፊት ከነበሩት ወደ እግዚአብሔር የተመለሰ የሚመስለው ሰው አልነበረም። ከእርሱም በኋላ የሚመስለው አልተነሣም። 19 ‘ሐ’ ነገር ግን እግዚአብሔር ንጉሥ ምናሴ በይሁዳ ላይ በአደረገውና በአነሣሣው ጥፋት ሁሉ ከአስከተለው ታላቅ ቍጣ አልተመለሰም። 19 ‘መ’ እግዚአብሔርም አለ፥ “እስራኤልን እንዳራቅሁ ይሁዳን ከፊቴ አርቃለሁ። የመረጥኋትንም ከተማ ኢየሩሳሌምንና ስሜ በዚያ ይጠራበታል ያልሁትን ቤት እጥላለሁ።” ከዚህም ሁሉ በኋላ፥ ኢዮስያስም ቤተ መቅደሱን ካሰናዳ በኋላ፥ የግብጽ ንጉሥ ፈርዖን ኒካዑ በኤፍራጥስ ወንዝ አጠገብ የአሦርን ንጉሥ ይዋጋ ዘንድ ወጣ፤ ኢዮስያስም ሊጋጠመው ወጣ። እርሱም፥ “የይሁዳ ንጉሥ ሆይ፥ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? በምዋጋበት በሌላ ቤት ላይ ነው እንጂ በአንተ ላይ ዛሬ አልመጣሁም፤ እግዚአብሔርም እንድቸኩል አዝዞኛል፤ ከእኔ ጋር ያለው እግዚአብሔር እንዳያጠፋህ ተጠንቀቅ” ብሎ መልእክተኞችን ላከበት። ኢዮስያስ ግን ይዋጋው ዘንድ ተጽናና እንጂ ፊቱን ከእርሱ አልመለሰም፤ በእግዚአብሔርም አፍ የተነገረውን የኒካዑን ቃል አልሰማም፤ በመጊዶንም ሸለቆ ይዋጋ ዘንድ መጣ። ቀስተኞቹም ንጉሡን ኢዮስያስን ወጉት፤ ንጉሡም ብላቴኖቹን፥ “እጅግ ቈስያለሁና ከሰልፉ ውስጥ አውጡኝ” አላቸው። ብላቴኖቹም ከሰረገላው አውርደው ለእርሱ በነበረው በሁለተኛው ሰረገላ ውስጥ አስቀመጡት፤ ወደ ኢየሩሳሌምም አመጡት፤ እርሱም በዚያ ሞተ፤ በአባቶቹም መቃብር ተቀበረ፤ ይሁዳና ኢየሩሳሌምም ሁሉ ለኢዮስያስ አለቀሱ። ኤርምያስም ለንጉሡ ለኢዮስያስ የልቅሶ ግጥም ገጠመለት፤ እስከ ዛሬም ድረስ ወንዶችና ሴቶች መዘምራን ሁሉ በልቅሶ ግጥማቸው ስለ ኢዮስያስ ይናገሩ ነበር፤ ይህም በእስራኤል ሁሉ ዘንድ ወግ ሆኖ በልቅሶ ግጥም ተጽፎአል። የቀሩትም የኢዮስያስ ነገሮች፥ በእግዚአብሔርም ሕግ እንደ ተጻፈ ያደረገው ቸርነት፥ የፊተኛውና የኋለኛውም ነገሩ፥ እነሆ፥ በእስራኤልና በይሁዳ ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፈዋል።
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 35 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 35:16-27
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች