መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 28
28
የይሁዳ ንጉሥ የአካዝ ዘመነ መንግሥት
(2ነገ. 16፥1-4)
1አካዝም መንገሥ በጀመረ ጊዜ የሃያ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ሃያ አምስት” ይላል። ዓመት ጐልማሳ ነበረ፤ በኢየሩሳሌምም ዐሥራ ስድስት ዓመት ነገሠ፤ እንደ አባቱም እንደ ዳዊት በእግዚአብሔር ፊት ቅን ነገር አላደረገም። 2ነገር ግን በእስራኤል ነገሥታት መንገድ ሄደ፤ ደግሞም ቀልጠው የተሠሩትን ምስሎች ሠራ። 3ደግሞም በሄኖም ልጅ ሸለቆ ውስጥ ለምስሉ ሠዋ፤ እግዚአብሔር ከእስራኤል ልጆች ፊት እንዳሳደዳቸው እንደ አሕዛብም ክፉ ልማድ ልጆቹን በእሳት አቃጠለ። 4በኮረብታው መስገጃዎችና በተራሮች ላይ በለመለመውም ዛፍ ሁሉ በታች ያጥን ነበር።
5ስለዚህ አምላኩ እግዚአብሔር በሶርያ ንጉሥ እጅ አሳልፎ ሰጠው፤ እርሱም መታው፤ ከእርሱም ብዙ ምርኮኞችን ወሰደ፤ ወደ ደማስቆም አመጣው። ደግሞም በእስራኤል ንጉሥ እጅ አሳልፎ ሰጠው፤ እርሱም በታላቅ አመታት መታው። 6የአባቶቻቸውንም አምላክ እግዚአብሔርን ትተው ነበርና የእስራኤል ንጉሥ#“የእስራኤል ንጉሥ” የሚለው በዕብ. የለም። የሮሜልዩ ልጅ ፋቁሔ በአንድ ቀን ከይሁዳ ጽኑዓን የነበሩ መቶ ሃያ ሺህ ሰልፈኞችን ገደለ፤ 7ከኤፍሬም ወገን የነበረው ኀያል ሰው ዝክሪም የንጉሡን ልጅ ማዓሥያንና የቤቱን አዛዥ ዓዝሪቃምን፥#ግእዝ “ኤዝራ” ይላል። ለንጉሡም በማዕርግ ሁለተኛ የሆነውን ሕልቃናን ገደለ።
8የእስራኤል ልጆች ከወንድሞቻቸው ሦስት#ዕብ. “ሁለት” ይላል። መቶ ሺህ ሴቶችን፥ ወንዶችና ሴቶች ልጆችንም ማረኩ፤ እጅግም ምርኮ ከእነርሱ ወስደው ወደ ሰማርያ አገቡ። 9በዚያም ዖዴድ የተባለ የእግዚአብሔር ነቢይ ነበረ፤ ወደ ሰማርያም የሚመጣውን ጭፍራ ሊገናኘው ወጣ፤ እንዲህም አላቸው፤ “እነሆ፥ የአባቶቻችሁ አምላክ እግዚአብሔር ይሁዳን ስለ ተቈጣ በእጃችሁ አሳልፎ ሰጣቸው፤ እናንተም ወደ ሰማይ በሚደርስ ቍጣ ገደላችኋቸው። 10አሁንም የይሁዳንና የኢየሩሳሌምን ልጆች ባሪያዎች አድርገን እንግዛ ትላላችሁ፤ የፈጣሪያችሁ የእግዚአብሔር ምስክር የምሆን እኔም ከእናንተ ጋር ያለሁ አይደለምን?#ዕብ. “ነገር ግን አምላካችሁን እግዚአብሔርን የበደላችሁት በደል በእናንተ ዘንድ የለምን?” ይላል። 11አሁንም ስሙ፤ የእግዚአብሔር ቍጣ በላያችሁ ነድዶአልና ከወንድሞቻችሁ የወሰዳችኋቸውን ምርኮኞች መልሱ።” 12ደግሞም ከኤፍሬም ልጆች አለቆች የአናን ልጅ ዓዛርያስ፥ የመስለሞት ልጅ በራክያ፥ የሳሎም ልጅ ሕዝቅያስ፥ የአዳሊ ልጅ አማስያ ከሰልፍ የተመለሱትን ተቃወሙአቸው። 13“ደግሞም በእግዚአብሔር ፊት በእኛ ላይ በደል ታመጡብናላችሁና፥ ኀጢአታችንንና በደላችንን ታበዙብናላችሁና የተማረኩትን ወደዚህ አታግቡ፤ በደላችን ታላቅ ነውና፥ የእግዚአብሔርም የመቅሠፍቱ ቍጣ በእስራኤል ላይ ነውና” አሉአቸው። 14ሰልፈኞቹም ምርኮኞቹንና ምርኮውን በአለቆችና በጉባኤ ሁሉ ፊት ተዉ። 15በስማቸውም የተጻፉ ሰዎች ተነሥተው ምርኮኞቹን ወሰዱ፤ በመካከላቸውም ራቁታቸውን ለነበሩት ሁሉ ከምርኮው አለበሱአቸው፤ አጐናጸፉአቸውም፤ ጫማም በእግራቸው አደረጉላቸው፤ መገቡአቸውም፤ አጠጡአቸውም፤ ቀቡአቸውም፤ ደካሞቹንም ሁሉ በአህዮች ላይ አስቀመጡአቸው፤ ዘንባባም ወዳለበት ከተማ ወደ ኢያሪኮ ወደ ወንድሞቻቸው አመጡአቸው፤ ወደ ሰማርያም ተመለሱ።
ንጉሡ አካዝ የአሦርን ንጉሥ ርዳታ እንደ ጠየቀ
(2ነገ. 16፥7-9)
16በዚያም ጊዜ ንጉሡ አካዝ ርዳታ ፈልጎ ወደ አሦር ንጉሥ ላከ፤ 17የኤዶምያስ ሰዎች ዳግመኛ መጥተው፥ ይሁዳንም መትተው ብዙ ምርኮኛ ወስደው ነበርና። 18ደግሞም ፍልስጥኤማውያን በቆላውና በደቡብ በኩል ባሉት በይሁዳ ከተሞች አደጋ ጥለው ነበር፤ ቤትሳሚስንና ኤሎንን፥ ጋቤሮትንም፥ ሠካዕንና መንደሮችዋን፥ ቴምናንና መንደሮችዋንም፥ ጋማዚእንና መንደሮችዋን ወስደው በዚያ ተቀምጠው ነበር። 19በይሁዳም ንጉሥ በአካዝ ምክንያት እግዚአብሔር ይሁዳን አዋረደው፤ እርሱ ከእግዚአብሔር እጅግ ርቆአልና። 20የአሦርም ንጉሥ ቴልጌልቴልፌልሶር መጥቶ አስጨነቀው። 21አካዝም ከእግዚአብሔር ቤት ከንጉሡና ከአለቆቹም ቤት የነበረውን ሁሉ ወሰደ፤ ለአሦርም ንጉሥ ሰጠ፥ ነገር ግን አስጨነቀው እንጂ አልረዳውም።
22ዳግመኛም ንጉሡ አካዝ ፈጽሞ ከእግዚአብሔር ራቀ። 23ንጉሡም፥ “የመቱኝን የደማስቆን አማልክት እፈልጋቸዋለሁ፤ የሶርያን ንጉሥ እርሱን ረድተውታልና እኔንም ይረዱኝ ዘንድ እሠዋላቸዋለሁ” አለ። ነገር ግን ለእርሱና ለእስራኤል ሁሉ ዕንቅፋት ሆኑ። 24አካዝም የእግዚአብሔርን ቤት ዕቃዎች ሁሉ ወስዶ ሰባበራቸው፤ የእግዚአብሔርንም ቤት ደጆች ዘጋ፤ በኢየሩሳሌምም ማዕዘን ሁሉ ለራሱ መሠዊያ ሠራ። 25በይሁዳም ከተሞች ሁሉ ለሌሎች አማልክት ያጥን ዘንድ የኮረብታ መስገጃዎችን አሠራ፤ የአባቶቻቸውንም አምላክ እግዚአብሔርን አስቈጣ። 26የቀሩትም ነገሮቹና ሥራው ሁሉ፥ የፊተኞቹና የኋለኞቹ እነሆ፥ በይሁዳና በእስራኤል ነገሥታት መጽሐፍ ተጽፈዋል። 27አካዝም ከአባቶቹ ጋር አንቀላፋ፤ በዳዊትም ከተማ ቀበሩት፤ ነገር ግን ወደ እስራኤል ነገሥታት መቃብር አላገቡትም፤ ልጁም ሕዝቅያስ በእርሱ ፋንታ ነገሠ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 28: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ