መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 18
18
ነቢዩ ሚክያስ በአክዓብ ላይ ትንቢት እንደ ተናገረ
(1ነገ. 22፥1-28)
1ለኢዮሣፍጥም ብዙ ብልጥግናና ክብር ነበረው፤ ከአክዓብም ወገን ሚስት አገባ። 2ከጥቂት ዓመታት በኋላም ወደ አክዓብ ወደ ሰማርያ ወረደ። አክዓብም ለእርሱና ከእርሱ ጋር ለነበሩት ሕዝብ ብዙ በጎችንና በሬዎችን አረደ፤ ወደደውም፤ ከእርሱም ጋር ወደ ሬማት ዘገለዓድ ይሄድ ዘንድ አባበለው። 3የእስራኤልም ንጉሥ አክዓብ የይሁዳን ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፥ “ከእኔ ጋር ወደ ሬማት ዘገለዓድ ትሄዳለህን?” አለው። እርሱም፥ “እኔ እንደ አንተ ነኝ፤ ሕዝቤም ለሰልፍ እንደ ሕዝብህ ናቸው፤” ብሎ መለሰለት።
4ኢዮሣፍጥም የእስራኤልን ንጉሥ፥ “ዛሬ እግዚአብሔርን ጠይቅ” አለው። 5የእስራኤልም ንጉሥ ከነቢያቱ አራት መቶ ሰዎችን ሰብስቦ፥ “ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ ልሂድን? ወይስ ልቅር?” አላቸው። እነርሱም፥ “እግዚአብሔር በንጉሥ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ውጣ” አሉት። 6ኢዮሣፍጥ ግን፥ “እንጠይቀው ዘንድ የእግዚአብሔር ነቢይ የሆነ ሌላ ሰው በዚህ አይገኝምን?” አለ። 7የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፥ “እግዚአብሔርን የምንጠይቅበት አንድ ሰው አለ፤ ነገር ግን ሁልጊዜ ክፉ እንጂ ከቶ መልካም ትንቢት አይናገርልኝምና እጠላዋለሁ፤ እርሱም የይምላ ልጅ ሚክያስ ነው” አለው። ኢዮሣፍጥም፥ “ንጉሡ እንዲህ አይበል” አለው። 8የእስራኤልም ንጉሥ#ግእዙ “አክዓብ” ይላል። አንድ ጃንደረባ ጠርቶ፥ “የይምላን ልጅ ሚክያስን ፈጥነህ አምጣው” አለው። 9የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ልብሰ መንግሥት ለብሰው በሰማርያ በር መግቢያ አጠገብ በአደባባይ በዙፋኖቻቸው ላይ ተቀምጠው ነበር፤ ነቢያትም ሁሉ በፊታቸው ትንቢት ይናገሩ ነበር። 10የካህናን ልጅ ሴዴቅያስም የብረት ቀንዶች ሠርቶ፦ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፥ “ሶርያውያንን እስክታጠፋቸው ድረስ በእነዚህ ትወጋለህ” አለ። 11ነቢያትም ሁሉ፥ “እግዚአብሔር በንጉሡ እጅ አሳልፎ ይሰጣታልና ወደ ሬማት ዘገለዓድ ውጣና ተከናወን” እያሉ እንዲሁ ትንቢት ይናገሩ ነበር።
12ሚክያስንም ሊጠራ የሄደ መልእክተኛ፥ “እነሆ፥ ነቢያት በአንድ አፍ ሆነው ለንጉሡ መልካም ይናገራሉ፤ ቃልህም እንደ ቃላቸው እንዲሆን መልካም እንድትናገር እለምንሃለሁ” አለው። 13ሚክያስም፥ “ሕያው እግዚአብሔርን! አምላኬ የሚለውን እርሱን እናገራለሁ” አለ። 14ወደ ንጉሡም በመጣ ጊዜ ንጉሡ፥ “ሚክያስ ሆይ፥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ለሰልፍ ልሂድን? ወይስ ልቅር?” አለው። 15ነቢዩ ሚክያስም፥ “ውጣ፤ ተከናወን፤ በእጅህም አልፈው ይሰጣሉ” አለ። ንጉሡም፥ “በእግዚአብሔር ስም ከእውነት በቀር እንዳትነግረኝ ስንት ጊዜ አምልሃለሁ?” አለው። 16እርሱም፥ “እስራኤል ሁሉ ጠባቂ እንደሌላቸው በጎች በተራሮች ላይ ተበትነው አየሁ፤ እግዚአብሔርም፦ ለእነዚህ ጌታ የላቸውም፥ እያንዳንዱም በሰላም ወደ ቤቱ ይመለስ አለ” ብሎ ተናገረ። 17የእስራኤልም ንጉሥ ኢዮሣፍጥን፥ “ክፉ እንጂ መልካም ትንቢት አይናገርልኝም አላልሁህምን?” አለው። 18ሚክያስም#“ሚክያስም” የሚለው በዕብ. ብቻ። አለ፥ “እንዲህ አይደለም፤ እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ስሙ፤ እግዚአብሔር በዙፋኑ ተቀምጦ፥ የሰማይ ሠራዊት ሁሉ በቀኙና በግራው፤ ቆመው አየሁ።” 19እግዚአብሔርም፥ “ወጥቶ በሬማት ዘገለዓድ ይወድቅ ዘንድ የእስራኤልን ንጉሥ አክዓብን የሚያታልል ማን ነው?” አለ። አንዱም እንደዚህ፥ ሌላውም እንደዚያ ያለ ነገር ተናገረ። 20መንፈስም መጣ፤ በእግዚአብሔርም ፊት ቆሞ፥ “እኔ አታልለዋለሁ” አለ። እግዚአብሔርም፥ “በምን ታታልለዋለህ?” አለው። 21እርሱም፥ “ወጥቼ በነቢያት ሁሉ አፍ የሐሰት መንፈስ እሆናለሁ” አለ። እግዚአብሔርም፥ “ታታልለዋለህ፤ ይቀናሃል፥ ውጣ፤ እንዲህም አድርግ” አለው። 22“አሁንም እነሆ፥ እግዚአብሔር በእነዚህ በነቢያትህ አፍ የሐሰት መንፈስን አድርጎአል፤ እግዚአብሔርም በአንተ ላይ ክፉ ተናግሮብሃል።”
23የካህናንም ልጅ ሴዴቅያስ ቀረበ፤ ሚክያስንም በጥፊ መታውና፥ “የእግዚአብሔር መንፈስ ከአንተ ጋር ይናገር ዘንድ በምን መንገድ ከእኔ አለፈ?” አለው። 24ሚክያስም፥ “እነሆ፥ በዚያ ቀን ልትሸሸግ ከእልፍኝ ወደ እልፍኝ ስትሄድ ታያለህ” አለ። 25የእስራኤልም ንጉሥ እንዲህ አለ፥ “ሚክያስን ውሰዱ፤ ወደ ከተማዪቱም አለቃ ወደ ኤሜር፥#ዕብ. “አሞን” ይላል። ወደ ንጉሡም ልጆች አለቃ ወደ ኢዮአስ መልሱት 26እንዲህም በሉአቸው፦ ንጉሡ እንዲህ ይላል፦ በደኅና እስክመለስ ድረስ ይህን ሰው በግዞት አኑሩት፤ የመከራም እንጀራ መግቡት፤ የመከራም ውኃ አጠጡት።” 27ሚክያስም፥ “በደኅና ብትመለስ እግዚአብሔር በእኔ አልተናገረም” አለ። “ደግሞም እናንተ ሕዝቡ ሁሉ ስሙኝ” አለ። 28የእስራኤል ንጉሥና የይሁዳ ንጉሥ ኢዮሣፍጥ ወደ ሬማት ዘገለዓድ ወጡ። 29የእስራኤል ንጉሥም ኢዮሣፍጥን፥ “ልብሴን ለውጬ ወደ ጦርነት እገባለሁ፤ አንተ ግን የእኔን ልብስ ልበስ” አለው። የእስራኤልም ንጉሥ ልብሱን ለወጠ፤ ወደ ሰልፍም ገባ። 30የሶርያም ንጉሥ ከእርሱ ጋር የነበሩትን የሰረገሎቹን አለቆች፦ ከእስራኤልም ንጉሥ በቀር ትንሽ ቢሆን ወይም ትልቅ ከማናቸውም ጋር አትጋጠሙ ብሎ አዝዞ ነበር። 31የሰረገሎችም አለቆች ኢዮሣፍጥን ባዩ ጊዜ፥ “የእስራኤል ንጉሥ ነው” አሉ፤ ሊጋጠሙትም ከበቡት፤ ኢዮሣፍጥ ግን ጮኸ፤ እግዚአብሔርም አዳነው፤ አምላኩም ከእርሱ መለሳቸው። 32የሰረገሎቹም አለቆች የእስራኤል ንጉሥ እንዳልሆነ ባዩ ጊዜ ከእርሱ ተመለሱ። 33አንድ ሰውም ቀስቱን በድንገት ገትሮ የእስራኤልን ንጉሥ በጥሩሩ መጋጠሚያ በኩል ሳንባውን ወጋው። ሰረገለኛውንም፥ “ተወግቻለሁና እጅህን ግታ፤ ከጦርነት ውስጥ አውጣኝ” አለው። 34በዚያም ቀን ጦርነት በረታ፤ የእስራኤልም ንጉሥ በሶርያውያን ፊት እስከ ማታ ድረስ በሰረገላው ላይ ራሱን ይደግፍ ነበር፤ ፀሐይም በገባ ጊዜ ሞተ።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልእ 18: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ