ዳዊትም ከአውቴዘራማ ሸሸ፤ ወደ ዮናታንም መጣ፤ እንዲህም አለው፥ “ምን አደረግሁ? ምንስ በደልሁ? ነፍሴንም ይሻት ዘንድ በአባትህ ፊት ጥፋቴና ኀጢአቴ ምንድን ነው?” ዮናታንም፥ “ይህንስ ያርቀው፤ አትሞትም፤ እነሆ፥ አባቴ አስቀድሞ ለእኔ ሳይገልጥ ትልቅም ሆነ ትንሽ ነገር ቢሆን አያደርግም፤ አባቴስ ይህን ነገር ለምን ይሰውረኛል? እንዲህ አይደለም” አለው። ዳዊትም፥ “እኔ በፊትህ ሞገስን እንዳገኘሁ አባትህ በእውነት ያውቃል፤ እርሱም፦ ዮናታን እንዳይቃወም አይወቅ ይላል፤ ነገር ግን ሕያው እግዚአብሔርን! በሕያው ነፍስህም እምላለሁ፤ እኔ እንዳልሁት በእኔና በሞት መካከል አንድ ርምጃ ያህል ቀርቶአል” ብሎ ማለ። ዮናታንም ዳዊትን፥ “ነፍስህ ምን ትፈልጋለች? እኔስ ምን ላድርግልህ?” አለው። ዳዊትም ዮናታንን አለው፥ “እነሆ ነገ መባቻ ነው፤ በንጉሥም አጠገብ ለምሳ አልቀመጥም፤ እስከ ማታ ድረስ በውጭ በሜዳ እንድሸሸግ አሰናብተኝ ። አባትህም ቢፈልገኝ፦ ለዘመዶቹ ሁሉ በዚያ በቤተ ልሔም የዓመት መሥዋዕት አላቸውና ዳዊት ወደ ከተማው ፈጥኖ ይሄድ ዘንድ አጽንቶ ለምኖኛል በለው። እርሱም፦ መልካም ነው ቢል ለእኔ ለባሪያህ ሰላም ይሆናል፤ ቢቈጣ ግን ክፋት ከእርሱ ዘንድ በእኔ ላይ እንደ ተቈረጠች ዕወቅ። እንግዲህ የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ከባሪያህ ጋር አድርገሃልና ለባሪያህ ቸርነትን አድርግ፤ በደል ግን ቢገኝብኝ አንተ ግደለኝ፤ ለምን ወደ አባትህ ታደርሰኛለህ?” ዮናታንም፥ “ይህ ከአንተ ይራቅ፤ ከአባቴ ዘንድ ክፋት በላይህ እንደ ተቈረጠች ያወቅሁ እንደ ሆነ በከተማ ባትኖርም እንኳን ወደ አንተ መጥቼ እነግርሃለሁ” አለው። ዳዊትም ዮናታንን፥ “አባትህ ስለ እኔ ክፉ ነገር የነገረህ እንደ ሆነ ማን ይነግረኛል?” አለው። ዮናታንም ዳዊትን፥ “ና፤ ወደ ሜዳ እንውጣ” አለው። ሁለቱም ወደ ሜዳ ወጡ። ዮናታንም ዳዊትን አለው፥ “የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር ያውቃል፤ እስከ ሦስት ቀን ድረስ በዚህ ጊዜ አባቴን መርምሬ እነሆ፥ በዳዊት ላይ መልካም ቢያስብ፥ እነሆ፥ ወደ ሜዳ ወደ አንተ አልልክም፤ ይህም ምልክት ይሁንህ፤ አባቴም በአንተ ላይ ክፋት ማድረግ ቢወድድ፥ እኔም ባላስታውቅህ፥ በሰላምም ትሄድ ዘንድ ባላሰናብትህ፥ እግዚአብሔር በዮናታን ይህን ያድርግ፤ ይህንም ይጨምር፤ እግዚአብሔርም ከአባቴ ጋር እንደ ነበረ ከአንተ ጋር ይሁን። እኔም በሕይወት ሳለሁ ቸርነትን ታደርግልኛለህ፤ ብሞትም ቸርነትህን እስከ ዘለዓለም ከቤቴ አትተው፤ ደግሞም እግዚአብሔር የዳዊትን ጠላቶች ሁሉ እያንዳንዱን ከምድር ፊት ባጠፋቸው ጊዜ የዮናታን ስም በዳዊት ቤት ይገኛል።” ዮናታንም፥ “እግዚአብሔር ከዳዊት ጠላቶች እጅ ይፈልገው” ብሎ ከዳዊት ቤት ጋር ቃል ኪዳን አደረገ። ዮናታንም ዳዊትን እንደ ነፍሱ ይወድድ ነበርና እንደ ገና ማለለት።
መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 20 ያንብቡ
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ሳሙኤል ቀዳማዊ 20:1-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos