ዐሥሩንም የናስ መታጠቢያ ሰን ሠራ፤ አንዱ መታጠቢያ ሰን አርባ የባዶስ መስፈሪያ ያነሣ ነበር፤ እያንዳንዱም መታጠቢያ ሰን አራት ክንድ ነበረ፤ በዐሥሩም መቀመጫዎች ላይ በእያንዳንዱ አንድ አንድ መታጠቢያ ሰን ይቀመጥ ነበር። አምስቱንም መቀመጫዎች በቤቱ ቀኝ፥ አምስቱንም በቤቱ ግራ አኖራቸው፤ ኩሬውንም በቤቱ ቀኝ በአዜብ ፊት ለፊት በስተምሥራቅ አኖረው። ኪራምም ምንቸቶችንና መጫሪያዎችን፥ ድስቶችንም ሠራ፤ ኪራምም ለንጉሡ ለሰሎሞን በእግዚአብሔር ቤት የሠራውን ሥራ ሁሉ ጨረሰ። ሁለቱንም አዕማድ፥ በሁለቱም አዕማድ ራስ ላይ የነበሩትን ኩብ የሚመስሉትን ጕልላቶች፥ በሁለቱም አዕማድ ላይ የነበሩትን ሁለቱን ጕልላቶች የሚሸፍኑትን ሁለቱን መርበቦች፥ በሁለቱም አዕማድ ላይ የነበሩትን ሁለቱን ጕልላቶች ይሸፍኑ ዘንድ ለእያንዳንዱ መርበብ በሁለት በሁለት ተራ አድርጎ ለሁለቱ መርበቦች አራት መቶ ሮማኖችን አደረገ። ዐሥሩንም መቀመጫዎች፥ በመቀመጫዎቹም ላይ የሚቀመጡትን ዐሥሩን መታጠቢያ ሰን፥ አንዱንም ኩሬ፥ ከኩሬውም በታች የሚሆኑትን ዐሥራ ሁለቱን በሬዎች፥ ምንቸቶቹንም፥ መጫሪያዎቹንም፥ ድስቶቹንም፥ ዕቃዎቹንም ሁሉ ኪራም ለንጉሡ ለሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤት ሠራ። በንጉሡ ቤትና በእግዚአብሔር ቤትም አርባ ስምንት አዕማድ ነበሩ። ኪራምም ለንጉሡ የሠራቸው ዕቃዎች ሁሉ ከጥሩ ናስ ነበር። በዮርዳኖስም ሜዳ በሱኮትና በተርታን መካከል ባለው በወፍራሙ መሬት ውስጥ አስፈሰሰው። ይህ ሁሉ ሥራ ለተሠራበት ናስ ሚዛን አልነበረውም፤ የናሱም ሚዛን ብዙ ነበርና አይቈጠርም ነበር። ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር ቤት ዕቃን ሁሉ አሠራ፤ የወርቁን መሠዊያ፥ የገጹም ኅብስት የነበረበትን የወርቅ ገበታ፥ በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት አምስቱ በቀኝ፥ አምስቱም በግራ የሚቀመጡትን ከጥሩ ወርቅ የተሠሩትንም መቅረዞች፥ የወርቁንም አበባዎችና ቀንዲሎች፥ መኮስተሪያዎችንም፥ ከጥሩ ወርቅም የተሠሩትን ጽዋዎችና ጕጠቶች፥ ድስቶቹንና ጭልፋዎቹንም፥ ማንደጃዎቹንም፥ ጽንሐሖችን፥ ለውስጠኛውም ቤት ለቅድስተ ቅዱሳን ደጆች፥ ለቤተ መቅደሱም ደጆች የሚሆኑትን የወርቅ ማጠፊያዎች አሠራ። እንዲሁም ንጉሡ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤት የአሠራው ሥራ ሁሉ ተፈጸመ። አባቱም ዳዊት የቀደሰውን፥ ራሱም የቀደሰውን፥ የብርና የወርቅ ዕቃ ሰሎሞን በእግዚአብሔር ቤት ውስጥ በነበሩ ግምጃ ቤቶች አገባ።
መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 7 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 7:38-51
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች