ሑራም ለእያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ ዐሥር መታጠቢያ ገንዳዎች ሠራ፤ እያንዳንዱ ገንዳ ዙሪያ አጋማሽ ስፋት አንድ ሜትር ከሰማንያ ሳንቲ ሜትር ያኽል ሲሆን፥ ስምንት መቶ ሊትር ያኽል ውሃ ይይዝ ነበር፤ ሑራምም አምስቱን የዕቃ ማስቀመጫዎች ከቤተ መቅደሱ በስተደቡብ፥ የቀሩትንም አምስቱን በቤተ መቅደሱ በስተ ሰሜን በኩል አቆመ፤ ገንዳውን ደግሞ በቤተ መቅደሱ ደቡባዊ ምሥራቅ ማእዘን ላይ አቆመው። ሑራም ድስቶችን፥ መጫሪያዎችንና ጐድጓዳ ሳሕኖችን ሠራ፤ በዚህ ዐይነትም ለንጉሥ ሰሎሞን ሊሠራለት የጀመረውን የእግዚአብሔርን መቅደስ ሥራ ፈጸመ፤ ከሠራቸውም ነገሮች ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፦ ሁለቱ ምሰሶዎች፥ በምሰሶዎቹም ላይ የነበሩትን ማቶቶች የሚመስሉ ጉልላቶች፥ በምሰሶውም ላይ የነበሩትን ሁለቱን ጉልላቶች የሚሸፍኑት ሁለቱ መረቦች፥ በእያንዳንዱ ጒልላት ላይ በመረብ አምሳል የተሠሩት ሰንሰለቶች፥ በእያንዳንዱ ጒልላት ቅርጽ ላይ በሁለት ረድፍ አንዳንድ መቶ ዙር የሆኑ፥ ከነሐስ የተሠሩ አራት መቶ የሮማን ቅርጾች፥ ዐሥሩ ባለመንኰራኲር የዕቃ ማስቀመጫዎች፥ ዐሥሩ የመታጠቢያ ገንዳዎች፥ ውሃ ማጠራቀሚያ ገንዳ፥ ገንዳውን ደግፈው የሚይዙ የዐሥራ ሁለቱ በሬዎች ቅርጾች፥ ድስቶቹ፥ መጫሪያዎቹና ጐድጓዳ ሳሕኖቹ፤ ለቤተ መቅደሱ አገልግሎት ይውሉ ዘንድ ሑራም እነዚህን ሁሉ ዕቃዎች ለሰሎሞን የሠራለት ከተወለወለ ንጹሕ ነሐስ ነበር። ንጉሥ ሰሎሞን እነዚህን ሁሉ ያሠራው በዮርዳኖስ ሸለቆ በሱኮትና ጻርታን መካከል በሚገኘው በብረት ማቅለጫ ስፍራ ነበር። ከነሐስ የተሠራው ይህ ሁሉ ዕቃ እጅግ ብዙ ስለ ነበር፥ ሰሎሞን በሚዛን እንዲለካ አላደረገውም፤ ስለዚህ ክብደቱ ምን ያኽል እንደ ሆነ ተወስኖ አልታወቀም። ለቤተ መቅደሱ አገልግሎት ይውሉ ዘንድ ሰሎሞን የሚከተሉትን ዕቃዎች አሠራ፤ እነርሱም የወርቁ መሠዊያ፥ ለእግዚአብሔር የሚቀርበው ኅብስት ማኖሪያ የወርቅ ጠረጴዛ፥ በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት አምስቱ በስተደቡብ፥ አምስቱ ደግሞ በስተ ሰሜን የሚቀመጡት ዐሥሩ የወርቅ መቅረዞች፥ አበባዎች፥ የመብራት ቀንዲሎች፥ የእሳት መቈስቈሻዎች፥ ጽዋዎች፥ የዐመድ ማጠራቀሚያዎች፥ ጐድጓዳ ሳሕኖች፥ የዕጣን ማቅረቢያ ዕቃዎች፥ ማንደጃዎች፥ ለቅድስተ ቅዱሳን በሮችና ለቤተ መቅደሱ ውጫዊ በሮች የሚያገለግሉ ማጠፊያዎች ነበሩ። እነዚህ ሁሉ ዕቃዎች ከወርቅ የተሠሩ ናቸው። ንጉሥ ሰሎሞን የቤተ መቅደሱን ሥራ ሁሉ ከፈጸመ በኋላ አባቱ ዳዊት ለእግዚአብሔር ቤት አገልግሎት እንዲውል የለየውን ብሩን፥ ወርቁንና ሌላውንም ዕቃ በሙሉ በቤተ መቅደሱ ግምጃ ቤት ውስጥ አኖረው።
አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 7 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: አንደኛ መጽሐፈ ነገሥት 7:38-51
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች