1 ነገሥት 7:38-51

1 ነገሥት 7:38-51 NASV

ከዚያም ለእያንዳንዱ የዕቃ ማስቀመጫ የሚሆን፣ እያንዳንዱ አርባ የባዶስ መስፈሪያ የሚይዝ ዐሥር የናስ መታጠቢያ ገንዳ ሠራ፤ ስፋቱም አራት ክንድ ነበር። ከዕቃ ማስቀመጫዎቹም ዐምስቱን ከመቅደሱ በስተ ደቡብ፣ ዐምስቱን በስተሰሜን በኩል አኖረ፤ ገንዳውንም ከቤተ መቅደሱ በደቡብ ምሥራቅ ጫፍ ላይ በስተ ደቡብ አኖረው። ኪራምም ምንቸቶችን፣ መጫሪያዎችንና ጐድጓዳ ሳሕኖችን ሠራ። ኪራምም ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ አገልግሎት ለንጉሥ ሰሎሞን የሠራውን ሥራ ሁሉ ፈጸመ እነዚህም፦ ሁለቱን አዕማድ፣ በአዕማዱ ጫፎች ላይ ያሉትን ሁለት ባለሳሕን ጕልላቶችን፤ በአዕማዱ ላይ ያሉትን ባለሳሕን ቅርጽ ሁለት ጕልላቶችን ያስጌጡትን ሁለት መረቦች፤ በአዕማዱ ጫፎች ላይ ያሉትን ባለሳሕን ቅርጽ ጕልላቶች የሚሸፍኑና በሁለት ረድፍ የተቀረጹትን መረቦች የሚያስጌጡትን አራት መቶ ሮማኖች፤ ዐሥሩን የዕቃ ማስቀመጫዎች፣ ከዐሥር መታጠቢያ ገንዳዎቻቸው ጋራ፤ ገንዳውና ከሥሩ ያሉትን ዐሥራ ሁለት ኰርማዎች፤ ምንቸቶችን፣ መጫሪያዎችን እና ጐድጓዳ ሳሕኖችን። ኪራም ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መገልገያ እንዲሆኑ እነዚህን ዕቃዎች ሁሉ ለንጉሥ ሰሎሞን የሠራለት ከሚብረቀረቅ ናስ ነበር። ንጉሡም እነዚህ ዕቃዎች በዮርዳኖስ ሸለቆ፣ በሱኮትና በጻርታን መካከል ባለው በሸክላ ዐፈር ቦታ ቀልጠው በሸክላ ቅርጽ ተሠርተው እንዲወጡ አደረገ። ሰሎሞን ከብዛታቸው የተነሣ እነዚህ ሁሉ ዕቃዎች እንዲመዘኑ አላደረገም፣ ስለዚህም የናሱ ክብደት ምን ያህል እንደ ነበር አልታወቀም። እንደዚሁም ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ መገልገያ የሚሆኑትን ዕቃዎች ሠራ፤ እነዚህም፦ የወርቅ መሠዊያ፣ የገጸ ኅብስቱ ጠረጴዛ፣ በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ለፊት ዐምስቱ በቀኝ፣ ዐምስቱ በግራ የሚቀመጡ፣ ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ መቅረዞችን፣ ከወርቅ የተቀረጹ አበቦችን፣ ቀንዲሎችንና መኰስተሪያዎችን፤ ከንጹሕ ወርቅ የተሠሩ ጽዋዎችን፣ የመብራት መኰስተሪያዎችን፣ ለመርጫ የሚሆኑ ጐድጓዳ ሳሕኖችን፣ ጭልፋዎችን፣ የዕጣን ማቅረቢያ ዕቃዎችን፣ ለውስጠኛው ክፍል ለቅድስተ ቅዱሳኑ በሮችና እንዲሁም ለቤተ መቅደሱ በሮች የሚሆኑ የወርቅ ማጠፊያዎችን። ንጉሥ ሰሎሞን ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ የሠራው ሥራ ሁሉ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ አባቱ ዳዊት የቀደሰውን ብሩንና ወርቁን፣ ዕቃዎቹንም ሁሉ አምጥቶ በእግዚአብሔር ለእግዚአብሔር ቤተ መቅደስ ግምጃ ቤት አኖራቸው።