መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 6
6
ሰሎሞን የእግዚአብሔርን ቤተ መቅደስ እንደ ሠራ
1የእስራኤል ልጆች ከግብፅ ምድር ከወጡ አራት መቶ ሰማንያ አራት#ግሪክ ሰባ. ሊ. “አራት መቶ አርባ” ይላል። ዓመት በሆነ ጊዜ፥ ሰሎሞን በእስራኤል ላይ በነገሠ በአራተኛው ዓመት፥ ዚፍ በሚባለው በሁለተኛው ወር የእግዚአብሔርን ቤት መሥራት ጀመረ። 2ንጉሡ ሰሎሞንም ለእግዚአብሔር የሠራው ቤት ርዝመቱ ስድሳ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “አርባ” ይላል። ክንድ፥ ወርዱም ሃያ ክንድ፥ ቁመቱም ሠላሳ#ግሪክ ሰባ. ሊ. “ሃያ አምስት” ይላል። ክንድ ነበረ። 3በመቅደሱም ፊት ወለል ነበረ፤ ርዝመቱም እንደ መቅደሱ ወርድ ሃያ ክንድ፥ ወርዱም ከቤቱ ወደ ፊት ዐሥር ክንድ ነበረ፤ ቤቱንም ሠርቶ ጨረሰ። 4ለቤቱም በዐይነ ርግብ የተዘጉ መስኮቶችን አደረገ። 5በቤቱም ግንብ ዙሪያ፥ በመቅደሱና በቅድስተ ቅዱሳኑ ግንብ ዙሪያ ደርብ ሠራ፤ በዙሪያውም ጓዳዎች አደረገ። 6የታችኛውም ደርብ ወርዱ አምስት ክንድ፥ የመካከለኛውም ደርብ ወርዱ ስድስት ክንድ፥ የሦስተኛውም ደርብ ወርዱ ሰባት ክንድ ነበረ። ሰረገሎቹ በቤቱ ግንብ ውስጥ እንዳይገቡ ከቤቱ ግንብ ውጭ አረፍቶችን አደረገ። 7ቤቱም በተሠራ ጊዜ ፈጽመው በተወቀሩ ድንጋዮች ተሠራ፤ ሲሠሩትም መራጃና መጥረቢያ፥ የብረትም ዕቃ ሁሉ በቤቱ ውስጥ አልተሰማም። 8የታችኛውም ደርብ ጓዳዎች በር በቤቱ ቀኝ አጠገብ ነበረ። ከዚያም ወደ መካከለኛው ደርብ፥ ከመካከለኛውም ወደ ሦስተኛው ደርብ የሚወጡበት መውጫ ነበረው። 9ቤቱንም ሠርቶ ፈጸመው፤ የቤቱንም ጠፈር በዝግባ ሳንቃዎች አደረገ። 10በቤቱም ዙሪያ ሁሉ ቁመታቸው አምስት አምስት ክንድ የሆኑ ደርቦችን ሠራ፤ ከቤቱም ጋር በዝግባ እንጨት አጋጠማቸው።
11የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ሰሎሞን እንዲህ ሲል መጣ፦ 12“ስለዚህ ስለምትሠራልኝ ቤት በሥርዐቴ ብትሄድ፥ ፍርዴንም ብታደርግ፥ ትመላለስባቸውም ዘንድ ትእዛዞቼን ሁሉ ብትጠብቅ፥ ለአባትህ ለዳዊት የነገርሁትን ቃል ከአንተ ጋር አጸናለሁ። 13በእስራኤልም ልጆች መካከል እኖራለሁ፤ ሕዝቤንም እስራኤልን አልጥልም።”
14ሰሎሞንም ቤቱን ሠራው፤ ፈጸመውም። 15የቤቱንም ግንብ ውስጡን በዝግባ ሳንቃ ለበጠ፤ ከቤቱም መሠረት ጀምሮ እስከ ጣራው ድረስ የውስጡን ግንብ በእንጨት ለበጠው፤ ደግሞም የቤቱን ወለል በጥድ እንጨት አነጠፈው። 16ከቤተ መቅደሱ አያይዞ ከመሠረቱ ጀምሮ እስከ ጣራው ድረስ ሃያውን ክንድ በዝግባ ጠርብ ሠራ፤ ከመቅደሱም ከፍሎ ቅድስተ ቅዱሳኑን አደረገ። 17በቅድስተ ቅዱሳኑ ፊት ያለውም መቅደስ ርዝመቱ አርባ ክንድ ነበረ። 18የቤቱንም ውስጥ በተጐበጐበና በፈነዳ አበባ፥ በተቀረጸ ዝግባ ለበጠው፤ ሁሉም ዝግባ ነበረ፤ ድንጋዩም አልታየም ነበር። 19በዚያም የእግዚአብሔርን ቃል ኪዳን ታቦት ያኖር ዘንድ በቤቱ ውስጥ ቅድስተ ቅዱሳኑን አበጀ። 20የቅድስተ ቅዱሳኑም ርዝመት ሃያ ክንድ፥ ስፋቱም ሃያ ክንድ፥ ቁመቱም ሃያ ክንድ ነበረ፤ በጥሩም ወርቅ ለበጠው። 21በቅድስተ ቅዱሳኑም ፊት ከዝግባ መሠዊያን ሠራ፤ በጥሩ ወርቅም ለበጠው። 22የሠራው ቤት ሁሉ እስከ ተፈጸመ ድረስ ቤቱን ሁሉ በወርቅ ለበጠው፤ በቅድስተ ቅዱሳኑም ፊት የነበረውን መሠዊያ ሁሉ በወርቅ ለበጠው።
23በቅድስተ ቅዱሳኑም ውስጥ ቁመታቸው ዐሥር ክንድ የሆነ ከወይራ እንጨት#“ከወይራ እንጨት” የሚለው በግሪክ ሰባ. ሊ. የለም። ሁለት ኪሩቤልን ሠራ። 24የኪሩብም አንደኛው ክንፍ አምስት ክንድ፥ የኪሩብም ሁለተኛው ክንፍ አምስት ክንድ ነበረ፤ ከአንደኛው ክንፍ ጫፍ ጀምሮ እስከ ሁለተኛው ክንፍ ጫፍ ድረስ ዐሥር ክንድ ነበረ። 25እንደዚሁም ሁለተኛው ኪሩብ ዐሥር ክንድ ነበረ፤ ሁለቱም ኪሩቤል አንድ ልክና አንድ መልክ ነበሩ። 26የአንዱ ኪሩብ ቁመት ዐሥር ክንድ ነበረ፤ የሁለተኛውም ኪሩብ እንዲሁ ነበረ። 27ሁለቱም ኪሩቤል በውስጠኛው ቤት መካከል ነበሩ። የኪሩቤልም ክንፎቻቸው ተዘርግተው ነበር፤ የአንዱም ኪሩብ ክንፍ አንደኛውን ግንብ ይነካ ነበር፤ የሁለተኛውም ኪሩብ ክንፍ ሁለተኛውን ግንብ ይነካ ነበር፤ የሁለቱም ክንፎች በቤቱ መካከል እርስ በርሳቸው ይነካኩ ነበር። 28ኪሩቤልንም በወርቅ ለበጣቸው።
29በቤቱም ግንብ ሁሉ ዙሪያ በውስጥና በውጭ የኪሩቤልና የዘንባባ ዛፍ፥ የፈነዳም አበባ ሥዕል ቀረጸ። 30የቤቱንም ወለል በውስጥና በውጭ በወርቅ ለበጠ። 31ለቅድስተ ቅዱሳኑም መግቢያ ከወይራ እንጨት ሳንቃዎችን ሠራ፤ መድረኩንና መቃኖቹን፥ ደፉንም አምስት ማዕዘን አደረገ። 32ሁለቱንም ሣንቃዎች ከወይራ እንጨት ሠራ፤ የኪሩቤልንና የዘንባባ ዛፍ፥ የፈነዳም አበባ ሥዕል ቀረጸባቸው፤ በወርቅም ለበጣቸው፤ ኪሩቤልንና የዘንባባውን ዛፍ በወርቅ ለበጠ። 33እንዲሁም ለመቅደሱ መግቢያ ከወይራ እንጨት አራት ማዕዘን መቃን አደረገ። 34ሁለቱንም ደጆች ከጥድ እንጨት ሠራ፤ አንዱ ደጅ በማጠፊያ ከተያያዙ ከሁለት ሣንቃዎች ተሠራ፤ ሁለተኛውም ደጅ በማጠፊያ ከተያያዙ ከሁለት ሣንቃዎች ተሠራ። 35የኪሩቤልንና የዘንባባ ዛፍ፥ የፈነዳም አበባ ሥዕል ቀረጸባቸው፤ በተቀረጸውም ሥራ ላይ በወርቅ ለበጣቸው፤ እስከ መድረካቸውም የተያያዙ ነበሩ። 36የውስጠኛውንም አደባባይ ቅጥር ሦስቱን ተራ በተጠረበ ድንጋይ፥ አንዱንም ተራ በዝግባ ሣንቃ ሠራው፤ በመቅደሱ ፊት ለፊት ላለው ቤት ወለልም መጋረጃ ሠራ።#“በመቅደሱ ፊት ለፊት ላለው ቤት ወለልም መጋረጃ ሠራ” የሚለው በዕብ. የለም።
37በአራተኛው ዓመት ከሚያዝያ በሁለተኛው ወር#ዕብ. “ዚፍ” ይላል። የእግዚአብሔርን ቤት መሠረተ። 38በዐሥራ አንደኛውም ዓመት ቡል በሚባል በስምንተኛው ወር ቤቱ እንደ ክፍሎቹና እንደ ሥርዐቱ ሁሉ ተጨረሰ። በሰባት ዓመትም ሠራው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 6: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ