መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 17
17
ኤልያስ ዝናብ እንዳይዘንብ ስለ መከልከሉ
1በገለዓድ ቴስባን የነበረው ቴስብያዊው ነቢዩ ኤልያስ አክዓብን፥ “በፊቱ የቆምሁት የኀያላን አምላክ የእስራኤል አምላክ ሕያው እግዚአብሔርን! ከአፌ ቃል በቀር በእነዚህ ዓመታት ዝናብም ጠልም አይወርድም” አለው። 2የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኤልያስ እንዲህ ሲል መጣ፦ 3“ከዚህ ተነሥተህ ወደ ምሥራቅ ሂድ፤ በዮርዳኖስም ትይዩ ባለው በኮራት ፈፋ ውስጥ ተሸሸግ። 4ከፈፋው ትጠጣለህ፤ ቁራዎችም በዚያ ይመግቡህ ዘንድ አዝዣለሁ።” ሄደም፥ እግዚአብሔርም እንዳዘዘው አደረገ። 5ሄዶም በዮርዳኖስ ትይዩ ባለው በኮራት ፈፋ ተቀመጠ። 6ቁራዎችም በየጥዋቱና በየማታው እንጀራና ሥጋ ያመጡለት ነበር፤ ከፈፋውም ይጠጣ ነበር። 7ከብዙ ቀንም በኋላ በምድር ላይ ዝናብ አልነበረምና ፈፋው ደረቀ።
ኤልያስ ወደ ሰራፕታዪቱ መበለት እንደ ሄደና የመበለቲቱን ልጅ ከሞት እንዳስነሣ
8የእግዚአብሔርም ቃል ወደ ኤልያስ መጣ እንዲህም አለው፦ 9“ተነሥተህ በሲዶና አጠገብ ወዳለችው ወደ ሰራፕታ ሂድ፤ በዚያም ተቀመጥ፤ እነሆም፥ ትመግብህ ዘንድ አንዲት መበለት አዝዣለሁ።” 10ተነሥቶም ወደ ሰራፕታ ሄደ፤ ወደ ከተማዪቱም በር በደረሰ ጊዜ አንዲት መበለት በዚያ እንጨት ትለቅም ነበር፤ ኤልያስም ጠርቶ፥ “የምጠጣው ጥቂት ውኃ በጽዋ ታመጭልኝ ዘንድ እለምንሻለሁ” አላት። 11ውኃም ልታመጣለት በሄደች ጊዜ ወደ እርስዋ ጠርቶ፥ “እግረ መንገድሽን ቍራሽ እንጀራ በእጅሽ አምጭልኝ” አላት። 12ሴትየዋም፥ “አምላክህ ሕያው እግዚአብሔርን! በማድጋ ካለው ከእፍኝ ዱቄት በማሰሮም ካለው ከጥቂት ዘይት በቀር እንጀራ የለኝም፤ እነሆም፥ ጥቂት እንጨት እሰበስባለሁ፤ ሄጄም ለእኔና ለልጄ እጋግረዋለሁ፤ በልተነውም እንሞታለን” አለችው። 13ኤልያስም አላት፥ “በእግዚአብሔር እመኚ፤ አትፍሪ፤ ሄደሽም እንዳልሽው አድርጊ፤ አስቀድመሽ ግን ከዱቄቱ ለእኔ ታናሽ እንጎቻ አድርገሽ አምጭልኝ፥ ከዚያም በኋላ ለአንቺና ለልጅሽ አድርጊ፤ 14የእስራኤል አምላክ እግዚአብሔር እንዲህ ይላልና፦ በምድር ላይ እግዚአብሔር ዝናብ እስከሚሰጥበት ቀን ድረስ፥ ዱቄቱ ከማድጋው አይጨረስም፥ ዘይቱም ከማሰሮው አይጐድልም።” 15እርስዋም ሄዳ እንዲሁ አደረገች፤ እርስዋና እርሱ ልጆችዋም በሉ። 16በአገልጋዩ በኤልያስም ቃል እንደ ተናገረው እንደ እግዚአብሔር ቃል ዱቄቱ ከማድጋው አልተጨረሰም፤ ዘይቱም ከማሰሮው አልጐደለም።
17ከዚያም በኋላ የባለቤቲቱ የዚያች ሴት ልጅ ታመመ፤ ትንፋሹም እስኪታጣ ድረስ ደዌው እጅግ ከባድ ነበረ። 18እርስዋም ኤልያስን፥ “የእግዚአብሔር ሰው ሆይ፥ እኔ ከአንተ ጋር ምን አለኝ? አንተስ ከእኔ ጋር ምን አለህ? ኀጢአቴንስ ታሳስብ ዘንድ፥ ልጄንስ ትገድል ዘንድ ወደ እኔ መጥተሃልን?” አለችው። 19ኤልያስም፥ “ልጅሽን ስጪኝ” አላት፥ ከብብቷም ወስዶ ተቀምጦበት ወደ ነበረው ሰገነት አወጣው፤ በአልጋውም ላይ አስተኛው። 20ኤልያስም፥ “እኔ በቤቷ ያደርሁ የዚች መበለት ምስክርዋ ጌታዬ ሆይ፥ ልጅዋን በመግደልህ ክፉ አድርገህባታልና ወዮልኝ!” ብሎ ጮኸ። 21በብላቴናውም ላይ ሦስት ጊዜ እፍ አለበት፤ ወደ እግዚአብሔርም፥ “አቤቱ አምላኬ ሆይ፥ የዚህ ብላቴና ነፍስ ወደ እርሱ ትመለስ ዘንድ እለምንሃለሁ” ብሎ እግዚአብሔርን ጠራው። 22እግዚአብሔርም የኤልያስን ቃል ሰማ፤ የሕፃኑም ነፍስ ተመለሰች፥ ዳነም፤#ግሪክ ሰባ. ሊ. “እንዲህም ሆነ ሕፃኑም ጮኸ” ይላል። 23ኤልያስም ብላቴናውን ይዞ ከሰገነቱ ወደ ቤት አወረደው፥ ለእናቱም ሰጣት፥ “እነሆ፥ ተመልከች ልጅሽ ድኖአል” አለ። 24ሴቲቱም ኤልያስን፥ “የእግዚአብሔር ሰው እንደ ሆንህ፥ የእግዚአብሔርም ቃል በአፍህ እውነት እንደ ሆነ አሁን ዐወቅሁ” አለችው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 17: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ