ንጉሡም ሰሎሞን ሴቶችን ይወድ ነበር፥ ከባዕዳን ሕዝብም የፈርዖንን ልጅ፥ ሞዓባውያትንና አሞናውያትን፥ ሶርያውያትንና ሲዶናውያትን፥ ኤዶማውያትንና አሞሬዎናውያትንም፥ ኬጤዎናውያትንም፦ ሚስቶችን አገባ። እግዚአብሔር የእስራኤልን ልጆች፥ “አምላኮቻቸውን ትከተሉ ዘንድ ልባችሁን እንዳይመልሱ ወደ እነርሱ አትግቡ፥ እነርሱም ወደ እናንተ አይግቡ” ካላቸው ከአሕዝብ አገባ፤ ሰሎሞን ግን እነርሱን ተከተለ፤ ወደዳቸውም። ለእርሱም ሰባት መቶ ሚስቶችና ሦስት መቶ ቁባቶች ነበሩት። ከዚህ በኋላ ሰሎሞን በሸመገለ ጊዜ ልቡ እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ልብ ከአምላኩ ከእግዚአብሔር ጋር አልነበረም። ከባዕድ ያገባቸው ሚስቶቹም ሌሎችን አማልክት ይከተል ዘንድ ልቡን መለሱት። ሰሎሞንም የሲዶናውያንን አምላክ አስጠራጢስን የአሞናውያንንም ርኵሰት ኮሞስን ተከተለ። ሰሎሞንም በእግዚአብሔር ፊት ክፉ ነገርን አደረገ፤ እንደ አባቱም እንደ ዳዊት እግዚአብሔርን አልተከተለውም። ያንጊዜም ሰሎሞን ለሞአብ ርኵሰት ለኮሞስ፥ ለአሞን ልጆች ርኵሰት ለሞሎክ በኢየሩሳሌም አንጻር በአለው ተራራ ላይ መስገጃን ሠራ። ሰሎሞንም ልዩ ከሆኑ ከአሕዝብ ለአገባቸው ሚስቶቹ ሁሉ እንዲህ አደረገ፤ ለጣዖቶቻቸውም መሥዋዕትን ሠዋ፤ ዕጣንም አጠነ። ሁለት ጊዜም ከተገለጠለት ከእስራኤል አምላክ ከእግዚአብሔር ልቡናውን መልሶአልና እግዚአብሔር በሰሎሞን ላይ ቍጣን ተቈጣ። ስለዚህም ነገር ወደ ባዕድ አምልኮት እንዳይሄድ፥ እግዚአብሔርም ያዘዘውን ሁሉ ይጠብቅና ያደርግ ዘንድ አዘዘው፤ ልቡናው ግን እንደ አባቱ እንደ ዳዊት ልብ ከእግዚአብሔር ጋር ፍጹም አልሆነም።
መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 11 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መጽሐፈ ነገሥት ቀዳማዊ 11:1-10
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች