መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል 2
2
የሰው አእምሮ ውሱንነት
1ስሙ ዑርኤል የተባለው ወደ እኔ የተላከው መልአክ መለሰልኝ። 2“የልዑልን#“በዚህ ዓለም የሚሆነውን ነገር ልታውቅ አትችልም” የሚል ዘርዕ ይገኛል። የጌትነቱን ምክር ታገኝ ዘንድ ልቡናህ ማድነቅን አደነቀን?” አለኝ። 3“አዎ ጌታዬ፥” አልሁት፤ እርሱም እንዲህ አለኝ፥ “ሦስቱን መንገዶች አሳይህ ዘንድ፥ ሦስቱንም ምሳሌዎች በፊትህ አኖር ዘንድ ተላክሁ፥ 4ከእነዚህም አንዲቱን የተረጐምህልኝ እንደ ሆነ እኔም ታውቅ ዘንድ የምትወዳትን ይህችን መንገድ እነግርሃለሁ፤ ይህ ክፉ ልቡናም ስለምን እንደ ሆነ አስተምርሃለሁ።”
5እኔም አልሁት፥ “አቤቱ ተናገር” እርሱም አለኝ፥ “እሳቱን በሚዛን መዝን፤ ነፋሱንም በመስፈሪያ ስፈር፤ ያለፈችውንም ቀን ጥራት።”
6እኔም መልሼ እንዲህ አልሁት፥ “ስለዚህ ነገር እኔን እንደ ጠየቅኸኝ ይህን ነገር ማድረግ የሚችል የተፈጠረ ሰው ማን ነው?” 7እርሱም አለኝ፥ “በባሕር ውስጥ ምን ያህል ቤቶች አሉ? ወይም በጥልቁ ውስጥ ምን ያህል ምንጮች አሉ? ወይም በሰማያት ላይ ምን ያህል መንገድ አለ? ወይም የሲኦል መንገድ በየት ነው? ወይም የገነት መንገድ በየት ነው? ብዬ ጠይቄህስ ቢሆን፥ 8ወደ ጥልቁ አልወረድሁም፤ ወደ ሲኦልም ፈጽሜ አልወረድሁም፤ ወደ ሰማይም አልወጣሁም ባልኸኝ ነበር። 9አሁን ግን ስለ ነፋስና ስለ እሳት፥ ስላለፈችውም ቀን እንጂ ይህን አልጠየቅሁህም፤ እነሆ፥ ልታውቀው አትችልም፤ ስለ እነዚህም የመለስህልኝ የለም። 10በአንተ ዘንድ ያለውን ማወቅ ያልቻልህ፥ 11የልዑልን የመንገዱን ሥርዐት እንዴት ማወቅ ትችላለህ? የልዑል መንገዱ ፍጻሜ በሌለው ተወስኗልና፥ የምትፈርስ፥ የምትበሰብስ አንተ የማይፈርስ፥ የማይበሰብስ የልዑልን መንገድ ማወቅ አትችልም።” 12ይህንም በሰማሁ ጊዜ በግንባሬ ወደቅሁ፤ “ተፈጥረን በኀጢአት ከምንኖርና መከራን ከምንቀበል ባልተፈጠርን በተሻለን ነበር፤ መከራ እንድንቀበልም አናውቅም” አልሁት።
የዛፎችና የባሕር ምሳሌ
13መልሶም እንዲህ አለኝ፥ “ዛፍና የዱር እንጨቶች ሄደው ምክርን ተማከሩ። 14ከፊታችን እናርቃት ዘንድ ኑ ሄደን ባሕርን እንውጋት፤ ለዛፍነታችንም ሌላ ሀገር እናቅና” አሉ። 15እንደዚሁም የባሕር ማዕበላት ምክርን መከሩ፤ “ለማዕበልነታችን በዚያ ሌላ ሀገር እንድናቀና በምድረ በዳ ያለ ዛፍን እንወጋው ዘንድ ኑ እንዝመት” አሉ። 16የዛፎች ምክር ከንቱ ሆነ፤ እሳት ወጥታ በልታቸዋለችና። 17እንዲሁም የባሕር ማዕበላት ምክር ከንቱ ሆነ፤ አሸዋው ገድቦ ከልሎአቸዋልና። 18“ፍርድ የምታውቅ ከሆነ ከእነዚህ ማንን እውነተኛ፥ ማንንስ ሐሰተኛ ታደርጋለህ?” አለኝ።
19መልሼም እንዲህ አልሁ፥ “ሁለቱ ከንቱን ዐሰቡ፤ የብስ ለዛፍ፥ ባሕርም ማዕበልን ትሸከም ዘንድ ተሰጥታለችና።”
20እርሱም መልሶ እንዲህ አለኝ፦“ መልካም ፈረድህ፤ እንዲሁ ለራስህ ለምን አትፈርድም? 21የብስ ለዛፍ፥ ባሕርም ለማዕበልዋ እንደ ተሰጠች እንዲሁም በምድር የሚኖሩ ሰዎች በምድር ያለውን ማወቅ ይችላሉ እንጂ በሰማያትና ከሰማያት በላይ ያለውን አይደለም።”
የዘመኑ ፍጻሜ
22መልሼም እንዲህ አልሁት፥ “አቤቱ እጠይቅሃለሁ፤ እንግዲያው እናስብ ዘንድ ልብ ለምን ተሰጠን? 23እኔ ግን የልዑልን መንገድ እጠይቅ ዘንድ አልወደድሁም፤ ሁልጊዜ በእኛ ላይ ስለሚያልፈው እንጂ፤ እስራኤል በውርደት ለአሕዛብ፥ የወደድኸውም ሕዝብ ለኀጢአተኞች ሕዝብ ተሰጥቶአልና። የአባቶቻችንም ኦሪት ጠፍታለችና፤ በውስጧም የተጻፈው ቃል ኪዳን የለምና። 24ከዓለም እንደ አንበጣ እናልፋለን፤ ሕይወታችንም እንደ ጢስ ነው፤ ምሕረትንም ለማግኘት የተገባን አይደለንም። 25ነገር ግን በእኛ ስለ ተጠራ ስለ ቅዱስ ስሙ ምን እናደርጋለን? ስለዚህ ነገር ጠየቅሁህ።”
26እርሱም መለሰልኝ፤ እንዲህም አለኝ፥ “በሕይወት ካለህ ታየዋለህ፤ በሕይወት ብትኖርም በጊዜው ታውቀዋለህ፤ ዓለም ያልፍ ዘንድ ይቸኩላልና። 27ዓለም የጻድቃንን ተስፋ ማስቀረት አይችልምና፥ ይህ ዓለም ጭንቅን የተሞላ ነውና፥ ደዌንም የተሞላ ነውና። 28ስለእርሷ የጠየቅኸኝ ክፋት ተዘርታለችና፥ መከርዋም አልደረሰምና። 29በውስጡም የተዘራው ካልታጨደና ካልተነሣ ክፋት የተዘራችበት ቦታው አይወገድም። 30በመጀመሪያ ክፉ የዘር ቅንጣት በአዳም ልቡና ተዘርቶ ነበርና፥ የኀጢአት ፍሬም ተወልዷልና እስከ ዛሬም ድረስ ደርሷልና፥ መከሩም እስኪደርስ ድረስ ይወለዳል፤ 31አንተ ራስህ እስኪ አስበው! የክፉ ዘር ቅንጣት ቢዘራ ይህን ያህል የኀጢአት ፍሬ ተወለደች። 32የመልካም ዘር ቅንጣት ግን ብትዘራ ቍጥር የሌለውን መልካም ፍሬን እንዴት ባፈራች ነበር!!”
33መልሼም እንዲህ አልሁት፥ “ደገኛው እስከ መቼ ይሆናል? የዚህ ዓለም ዘመኑ ክፉም፥ ጥቂትም ነውና።” 34መልሶም እንዲህ አለኝ፥ “ከልዑል ይልቅ አንተ እጅግ የምትቸኩል አይደለህም፤ አንተስ ስለ ራስህ ትቸኩላለህ፤ ልዑል ግን ስለ ብዙዎች ይቸኩላል። 35ስለዚህ የጻድቃን ነፍሳት በማደሪያቸው ሁነው ጠየቁ፤ በዚህ እስከ መቼ ድረስ እንኖራለን? የዋጋችንስ መከር መቼ ይደርሳል?” አሉ። 36መልአኩ ኢይሩማኤልም#“ሊቀ መላእክት ኢይሩማኤልም” የሚል ዘርዕ ይገኛል። እንዲህ ብሎ መለሰላቸው፥ “እንደ እናንተ ያሉት ጻድቃን ቍጥራቸው በተፈጸመ ጊዜ ነው። 37ይህ ዓለም በሚዛን ተመዝኗልና፥ ባሕሩንም በመስፈሪያ ሰፍሮታልና፤ የተሰጠውም መስፈርት እስኪፈጸም ድረስ ዝም ይላል፤ አይነቃምም።”
38እኔም መልሼ እንዲህ አልሁት፥ “አቤቱ ጌታዬ እነሆ፥ እኛ ሁላችን ኀጢአትን የተመላን ነን፤ 39ምናልባት የጻድቃን የዋጋቸው መከር በእኛ ምክንያት ይከለከላልን? ወይስ በዚህ ዓለም ስለሚኖሩት ሰዎች ኀጢአት ነው?” 40እርሱም መለሰልኝ እንዲህም አለኝ፥ “ዘጠኝ ወር ከተፈጸመ በኋላ በማኅፀንዋ ያለውን ልጅዋን ማስቀረት ይቻላት እንደ ሆነ ሄደህ የፀነሰች ሴትን ጠይቃት።” 41እኔም መልሼ አልሁት፥ “አቤቱ አትችልም፥” እርሱም አለኝ፥ “ሲኦልና የጻድቃን ነፍሳት ማደሪያዎችም እንዲሁ ናቸው። 42ማኅፀን በምጥ ጊዜ ለመውለድ እንደምትቸኩል ምድርም ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተቀበሩባት ሰዎችን ትሰጥ ዘንድ ትቸኩላለች። 43ያንጊዜም ታውቅ ዘንድ የምትወድደውን ነገር እነግርሃለሁ፥”
ምን ያህል ዘመን እንደ ቀረ
44እኔም መለስሁለት እንዲህም አልሁት፥ “በፊትህ ባለሟልነትን ካገኘሁ፥ ልጠይቅም እንዲቻለኝ ካደረግኸኝ ይኽን ንገረኝ። 45ይመጣ ዘንድ ያለው ዘመን ባለፈው ዘመን ልክ ነውን? ወይስ ያለፈው ዘመን ይበዛል? 46ያለፈውን አውቀዋለሁና፥ የሚመጣውን ግን አላውቀውምና።” 47እርሱም አለኝ፥ “በቀኝ በኩል ባንድ ወገን ሁነህ ቁም፤ የምሳሌውንም ትርጓሜ አሳይሀለሁ።” 48እኔም ቆምሁ፤ እነሆም ምድጃ በፊቴ እየነደደ ሲሄድ አየሁ፤ ከዚህም በኋላ እሳቱ በሄደ ጊዜ እነሆ ጢሱ ቀረ። 49ከእርሱም በኋላ ውኃን የተመላች ደመና በፊቴ ሄደች፤ ታላቅና ብዙ የሆነ ዝናምንም ታዘንማለች፤ ታላቁ ዝናምም ካለፈ በኋላ ካፊያው ቀረ። 50እርሱም አለኝ፥ “እንግዲህ እስኪ አንተ ዐስበው፤ ከካፊያው ዝናሙ፥ ከጢሱ እሳቱ እንደሚበዛ፥ እንደዚሁም ያለፈው መስፈርት ይበዛል፤ ነገር ግን ካፊያውም ጢሱም ይቀራል።
51“እስከ እነዚያ ዘመኖች ድረስ እኖራለሁን? እንጃ! በእነዚያስ ወራቶች ምን ይደረጋል?” ብዬ ማለድሁት። 52እርሱም መለሰልኝ እንዲህም አለኝ፥ “ስለ ጠየቅኸኝ ምልክትስ ከብዙ በጥቂቱ መንገር ይቻለኛል፤ ስለ ሕይወትህ ግን እነግርህ ዘንድ አልተላክሁም፤ እኔም አላውቀውም።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዕዝራ ሱቱኤል 2: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ