መንፈስ ቅዱስ አንድ ሲሆን ስጦታው ልዩ ልዩ ነው። ጌታም አንድ ሲሆን ልዩ ልዩ አገልግሎቶች አሉ። ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔርም አንድ ሲሆን ልዩ ልዩ አሠራር አለ። ለሁሉም ጌታ እየረዳ በየዕድሉ እንደሚገባውና እንደሚጠቅመው ለእያንዳንዱ በግልጥ ይሰጠዋል፤ በመንፈስ ቅዱስ የጥበብ ቃል የሚሰጠው አለ፤ በመንፈስ ቅዱስም የዕውቀት ቃል የሚሰጠው አለ። ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፥ ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፥ ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ፥ ለአንዱም ትንቢትን መናገር፥ ለአንዱም መናፍስትን መለየት፥ ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፥ ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጐም ይሰጠዋል። በዚህም ሁሉ ያው አንዱ መንፈስ ቅዱስ ሁሉን ይረዳል፤ ለሁሉም እንደ ወደደ ያድላቸዋል። አካል አንድ እንደ ሆነ ብዙ የአካል ክፍሎችም እንደ አሉበት፥ ነገር ግን የአካል ክፍሎች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፤ እኛ ሁላችንም በአንድ መንፈስ አንድ አካል ለመሆን ተጠምቀናል፤ አይሁድ ብንሆን፥ አረማውያንም ብንሆን፥ ባሪያዎችም ብንሆን፥ ነጻዎችም ብንሆን ሁላችን አንድ መንፈስ ጠጥተናልና። የአካላችንም ክፍሉ ብዙ ነው እንጂ አንድ አይደለም። እግርም፥ “እኔ እጅ አይደለሁምና የአካል ክፍል አይደለሁም” ብትል ይህን በማለቷ የአካል ክፍል መሆንዋ ይቀራልን? ጆሮም፥ “እኔ ዐይን አይደለሁምና የአካል ክፍል አይደለሁም” ብትል ይህን በማለቷ የአካል ክፍል መሆንዋ ይቀራልን? አካል ሁሉ ዐይን ቢሆን ኖሮ መስማት ከየት በተገኘ ነበር፤ አካልስ ሁሉ ጆሮ ቢሆን ኖሮ ማሽተት ከየት በተገኘ ነበር? አሁን ግን እግዚአብሔር የአካላችንን ክፍል በሰውነታችን ውስጥ እርሱ እንደ ወደደ እየራሱ አከናውኖ መደበው። የአካል ክፍሉ አንድ ቢሆን ኖሮ አካል የት በተገኘ ነበር? አሁንም የአካል ክፍሎች ብዙዎች ናቸው ፤ አካሉ ግን አንድ ነው። ዐይን እጅን፥ “አልፈልግሽም” ልትላት አትችልም፤ ራስም፥ “እግሮችን አልፈልጋችሁም” ልትላቸው አትችልም። ደካሞች የሚመስሉህ የአካል ክፍሎች ይልቁን የሚያስፈልጉህ ናቸው። ከአካልም ክፍሎች የተናቁ ለሚመስሉን ክብርን እንጨምርላቸዋለን፤ ለምናፍርባቸውም የአካል ክፍሎች ክብር ይጨመርላቸዋል። ለከበረው የአካላችን ክፍል ክብርን አንሻለትም፤ እግዚአብሔር ግን ሰውነታችንን አስማምቶታል፤ ይልቁንም ታናሹን የአካል ክፍል አክብሮታል። የአካላችን ክፍሎች እርስ በርሳቸው እንዳይለያዩ፥ አካላችን ሳይነጣጠል በክብር እንዲተካከል አስማማው። አንዱ የአካል ክፍል ቢታመም ከእርሱ ጋር የአካል ክፍሎች ሁሉ ይታመማሉ፤ አንዱ የአካል ክፍል ደስ ቢለውም የአካል ክፍሎች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል። እንግዲህ እናንተ የክርስቶስ አካሉ ናችሁ፤ እያንዳንዳችሁም የአካሉ ክፍሎች ናችሁ።
ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1 12 ያንብቡ
ያዳምጡ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1 12
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1 12:4-27
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች