የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

1 ቆሮንቶስ 12:4-27

1 ቆሮንቶስ 12:4-27 NASV

ስጦታዎች ልዩ ልዩ ሲሆኑ፣ መንፈስ ግን አንድ ነው፤ አገልግሎትም ልዩ ልዩ ሲሆን፣ ጌታ ግን አንድ ነው፤ አሠራርም ልዩ ልዩ ሲሆን፣ ሁሉን በሁሉ የሚሠራው ግን ያው አንዱ እግዚአብሔር ነው። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ሰው የሚሰጠው ለጋራ ጥቅም ነው። ለአንዱ በመንፈስ የጥበብን ቃል መናገር ይሰጠዋል፤ ለሌላው ደግሞ በዚያው መንፈስ የዕውቀትን ቃል መናገር ይሰጠዋል፤ ለአንዱ በዚያው መንፈስ እምነት ይሰጠዋል፤ ለሌላው ደግሞ በዚያው በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታዎች ይሰጠዋል፤ ለአንዱ ታምራትን የማድረግ፣ ለሌላው ትንቢትን የመናገር፣ ለሌላው ደግሞ መናፍስትን የመለየት፣ ለአንዱ በልዩ ልዩ ልሳን የመናገር፣ ለሌላው ደግሞ በልዩ ልዩ ልሳን የተነገረውን የመተርጐም ስጦታ ይሰጠዋል። እነዚህ ሁሉ የዚያው የአንዱ መንፈስ ስጦታዎች ሲሆኑ፣ ለእያንዳንዱ ሰው እርሱ ራሱ እንደ ፈቀደ ይሰጠዋል። አካል ብዙ ብልቶች ቢኖሩትም አንድ አካል ነው፤ ነገር ግን ብልቶች ብዙ ቢሆኑም አካል አንድ ነው። ክርስቶስም እንደዚሁ ነው። አይሁድ ወይም የግሪክ ሰዎች ብንሆን፣ ባሪያ ወይም ነጻ ሰዎች ብንሆን፣ እኛ ሁላችን አንድ አካል እንድንሆን በአንድ መንፈስ ተጠምቀናልና፤ ሁላችንም አንዱን መንፈስ እንድንጠጣ ተሰጥቶናል። አካል የተሠራው ከብዙ ብልቶች እንጂ ከአንድ ብልት አይደለም። እግር፣ “እኔ እጅ ስላልሆንሁ የአካል ክፍል አይደለሁም” ቢል ይህን በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ ይቀራልን? ጆሮም፣ “እኔ ዐይን ስላልሆንሁ የአካል ክፍል አይደለሁም” ቢል ይህን በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ ይቀራልን? አካል በሙሉ ዐይን ቢሆን ኖሮ፣ መስማት ከየት ይገኝ ነበር? አካል በሙሉ ጆሮ ቢሆን ኖሮ፣ ማሽተት ከየት ይገኝ ነበር? ነገር ግን እግዚአብሔር እንደ ወደደ እያንዳንዱን በአካል ውስጥ መድቧል። ሁሉም አንድ ብልት ቢሆን ኖሮ አካል ከየት ይገኝ ነበር? እንግዲህ ብልቶች ብዙ ናቸው፣ አካል ግን አንድ ነው። ዐይን እጅን፣ “አታስፈልገኝም” ሊለው አይችልም፤ ራስም እግርን፣ “አታስፈልገኝም” ሊለው አይችልም። እንዲያውም ደካማ የሚመስሉት የአካል ብልቶች እጅግ አስፈላጊ ናቸው። የተናቁ ለሚመስሉን ብልቶች ይበልጥ ክብር እንሰጣቸዋለን፤ ደግሞም የምናፍርባቸውን ብልቶች ይበልጥ እንንከባከባቸዋለን፤ የማናፍርባቸው ብልቶቻችን ግን ይህ አያስፈልጋቸውም። እግዚአብሔር ግን የአካል ብልቶችን አንድ ላይ አገጣጥሞ ክብር ለሚጐድላቸው የበለጠ ክብር ሰጥቷቸዋል፤ ይህንም ያደረገው በአካል ብልቶች መካከል መለያየት ሳይኖር፣ እርስ በርሳቸው እኩል እንዲተሳሰቡ ነው። አንድ ብልት ቢሠቃይ፣ ብልቶች ሁሉ ዐብረው ይሠቃያሉ፤ አንድ ብልት ቢከብር፣ ሌሎቹም ብልቶች ዐብረው ደስ ይላቸዋል። እንግዲህ እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ፤ እያንዳንዳችሁም የአካሉ ብልቶች ናችሁ።