1 ቆሮንቶስ 12:4-27
1 ቆሮንቶስ 12:4-27 የአማርኛ መጽሐፍ ቅዱስ (ሰማንያ አሃዱ) (አማ2000)
መንፈስ ቅዱስ አንድ ሲሆን ስጦታው ልዩ ልዩ ነው። ጌታም አንድ ሲሆን ልዩ ልዩ አገልግሎቶች አሉ። ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔርም አንድ ሲሆን ልዩ ልዩ አሠራር አለ። ለሁሉም ጌታ እየረዳ በየዕድሉ እንደሚገባውና እንደሚጠቅመው ለእያንዳንዱ በግልጥ ይሰጠዋል፤ በመንፈስ ቅዱስ የጥበብ ቃል የሚሰጠው አለ፤ በመንፈስ ቅዱስም የዕውቀት ቃል የሚሰጠው አለ። ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፥ ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፥ ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ፥ ለአንዱም ትንቢትን መናገር፥ ለአንዱም መናፍስትን መለየት፥ ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፥ ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጐም ይሰጠዋል። በዚህም ሁሉ ያው አንዱ መንፈስ ቅዱስ ሁሉን ይረዳል፤ ለሁሉም እንደ ወደደ ያድላቸዋል። አካል አንድ እንደ ሆነ ብዙ የአካል ክፍሎችም እንደ አሉበት፥ ነገር ግን የአካል ክፍሎች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፤ እኛ ሁላችንም በአንድ መንፈስ አንድ አካል ለመሆን ተጠምቀናል፤ አይሁድ ብንሆን፥ አረማውያንም ብንሆን፥ ባሪያዎችም ብንሆን፥ ነጻዎችም ብንሆን ሁላችን አንድ መንፈስ ጠጥተናልና። የአካላችንም ክፍሉ ብዙ ነው እንጂ አንድ አይደለም። እግርም፥ “እኔ እጅ አይደለሁምና የአካል ክፍል አይደለሁም” ብትል ይህን በማለቷ የአካል ክፍል መሆንዋ ይቀራልን? ጆሮም፥ “እኔ ዐይን አይደለሁምና የአካል ክፍል አይደለሁም” ብትል ይህን በማለቷ የአካል ክፍል መሆንዋ ይቀራልን? አካል ሁሉ ዐይን ቢሆን ኖሮ መስማት ከየት በተገኘ ነበር፤ አካልስ ሁሉ ጆሮ ቢሆን ኖሮ ማሽተት ከየት በተገኘ ነበር? አሁን ግን እግዚአብሔር የአካላችንን ክፍል በሰውነታችን ውስጥ እርሱ እንደ ወደደ እየራሱ አከናውኖ መደበው። የአካል ክፍሉ አንድ ቢሆን ኖሮ አካል የት በተገኘ ነበር? አሁንም የአካል ክፍሎች ብዙዎች ናቸው ፤ አካሉ ግን አንድ ነው። ዐይን እጅን፥ “አልፈልግሽም” ልትላት አትችልም፤ ራስም፥ “እግሮችን አልፈልጋችሁም” ልትላቸው አትችልም። ደካሞች የሚመስሉህ የአካል ክፍሎች ይልቁን የሚያስፈልጉህ ናቸው። ከአካልም ክፍሎች የተናቁ ለሚመስሉን ክብርን እንጨምርላቸዋለን፤ ለምናፍርባቸውም የአካል ክፍሎች ክብር ይጨመርላቸዋል። ለከበረው የአካላችን ክፍል ክብርን አንሻለትም፤ እግዚአብሔር ግን ሰውነታችንን አስማምቶታል፤ ይልቁንም ታናሹን የአካል ክፍል አክብሮታል። የአካላችን ክፍሎች እርስ በርሳቸው እንዳይለያዩ፥ አካላችን ሳይነጣጠል በክብር እንዲተካከል አስማማው። አንዱ የአካል ክፍል ቢታመም ከእርሱ ጋር የአካል ክፍሎች ሁሉ ይታመማሉ፤ አንዱ የአካል ክፍል ደስ ቢለውም የአካል ክፍሎች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል። እንግዲህ እናንተ የክርስቶስ አካሉ ናችሁ፤ እያንዳንዳችሁም የአካሉ ክፍሎች ናችሁ።
1 ቆሮንቶስ 12:4-27 አዲሱ መደበኛ ትርጒም (NASV)
ስጦታዎች ልዩ ልዩ ሲሆኑ፣ መንፈስ ግን አንድ ነው፤ አገልግሎትም ልዩ ልዩ ሲሆን፣ ጌታ ግን አንድ ነው፤ አሠራርም ልዩ ልዩ ሲሆን፣ ሁሉን በሁሉ የሚሠራው ግን ያው አንዱ እግዚአብሔር ነው። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ሰው የሚሰጠው ለጋራ ጥቅም ነው። ለአንዱ በመንፈስ የጥበብን ቃል መናገር ይሰጠዋል፤ ለሌላው ደግሞ በዚያው መንፈስ የዕውቀትን ቃል መናገር ይሰጠዋል፤ ለአንዱ በዚያው መንፈስ እምነት ይሰጠዋል፤ ለሌላው ደግሞ በዚያው በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታዎች ይሰጠዋል፤ ለአንዱ ታምራትን የማድረግ፣ ለሌላው ትንቢትን የመናገር፣ ለሌላው ደግሞ መናፍስትን የመለየት፣ ለአንዱ በልዩ ልዩ ልሳን የመናገር፣ ለሌላው ደግሞ በልዩ ልዩ ልሳን የተነገረውን የመተርጐም ስጦታ ይሰጠዋል። እነዚህ ሁሉ የዚያው የአንዱ መንፈስ ስጦታዎች ሲሆኑ፣ ለእያንዳንዱ ሰው እርሱ ራሱ እንደ ፈቀደ ይሰጠዋል። አካል ብዙ ብልቶች ቢኖሩትም አንድ አካል ነው፤ ነገር ግን ብልቶች ብዙ ቢሆኑም አካል አንድ ነው። ክርስቶስም እንደዚሁ ነው። አይሁድ ወይም የግሪክ ሰዎች ብንሆን፣ ባሪያ ወይም ነጻ ሰዎች ብንሆን፣ እኛ ሁላችን አንድ አካል እንድንሆን በአንድ መንፈስ ተጠምቀናልና፤ ሁላችንም አንዱን መንፈስ እንድንጠጣ ተሰጥቶናል። አካል የተሠራው ከብዙ ብልቶች እንጂ ከአንድ ብልት አይደለም። እግር፣ “እኔ እጅ ስላልሆንሁ የአካል ክፍል አይደለሁም” ቢል ይህን በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ ይቀራልን? ጆሮም፣ “እኔ ዐይን ስላልሆንሁ የአካል ክፍል አይደለሁም” ቢል ይህን በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ ይቀራልን? አካል በሙሉ ዐይን ቢሆን ኖሮ፣ መስማት ከየት ይገኝ ነበር? አካል በሙሉ ጆሮ ቢሆን ኖሮ፣ ማሽተት ከየት ይገኝ ነበር? ነገር ግን እግዚአብሔር እንደ ወደደ እያንዳንዱን በአካል ውስጥ መድቧል። ሁሉም አንድ ብልት ቢሆን ኖሮ አካል ከየት ይገኝ ነበር? እንግዲህ ብልቶች ብዙ ናቸው፣ አካል ግን አንድ ነው። ዐይን እጅን፣ “አታስፈልገኝም” ሊለው አይችልም፤ ራስም እግርን፣ “አታስፈልገኝም” ሊለው አይችልም። እንዲያውም ደካማ የሚመስሉት የአካል ብልቶች እጅግ አስፈላጊ ናቸው። የተናቁ ለሚመስሉን ብልቶች ይበልጥ ክብር እንሰጣቸዋለን፤ ደግሞም የምናፍርባቸውን ብልቶች ይበልጥ እንንከባከባቸዋለን፤ የማናፍርባቸው ብልቶቻችን ግን ይህ አያስፈልጋቸውም። እግዚአብሔር ግን የአካል ብልቶችን አንድ ላይ አገጣጥሞ ክብር ለሚጐድላቸው የበለጠ ክብር ሰጥቷቸዋል፤ ይህንም ያደረገው በአካል ብልቶች መካከል መለያየት ሳይኖር፣ እርስ በርሳቸው እኩል እንዲተሳሰቡ ነው። አንድ ብልት ቢሠቃይ፣ ብልቶች ሁሉ ዐብረው ይሠቃያሉ፤ አንድ ብልት ቢከብር፣ ሌሎቹም ብልቶች ዐብረው ደስ ይላቸዋል። እንግዲህ እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ፤ እያንዳንዳችሁም የአካሉ ብልቶች ናችሁ።
1 ቆሮንቶስ 12:4-27 መጽሐፍ ቅዱስ (የብሉይና የሐዲስ ኪዳን መጻሕፍት) (አማ54)
የጸጋም ስጦታ ልዩ ልዩ ነው መንፈስ ግን አንድ ነው፤ አገልግሎትም ልዩ ልዩ ነው ጌታም አንድ ነው፤ አሠራርም ልዩ ልዩ ነው፥ ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ እግዚአብሔር ግን አንድ ነው። ነገር ግን መንፈስ ቅዱስን መግለጥ ለእያንዳንዱ ለጥቅም ይሰጠዋል። ለአንዱ ጥበብን መናገር በመንፈስ ይሰጠዋልና፥ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እውቀትን መናገር ይሰጠዋል፥ ለአንዱም በዚያው መንፈስ እምነት፥ ለአንዱም በአንዱ መንፈስ የመፈወስ ስጦታ፥ ለአንዱም ተአምራትን ማድረግ፥ ለአንዱም ትንቢትን መናገር፥ ለአንዱም መናፍስትን መለየት፥ ለአንዱም በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፥ ለአንዱም በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም ይሰጠዋል፤ ይህን ሁሉ ግን ያ አንዱ መንፈስ እንደሚፈቅድ ለእያንዳንዱ ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል። አካልም አንድ እንደ ሆነ ብዙም ብልቶች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ብልቶች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ፥ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፤ አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባሪያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና። ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል። አካል ብዙ ብልቶች እንጂ አንድ ብልት አይደለምና። እግር፦ እኔ እጅ አይደለሁምና የአካል ክፍል አይደለሁም ብትል፥ ይህን በማለትዋ የአካል ክፍል መሆንዋ ይቀራልን? ጆሮም፦ እኔ ዓይን አይደለሁምና የአካል ክፍል አይደለሁም ቢል፥ ይህን በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ ይቀራልን? አካል ሁሉ ዓይን ቢሆን መስማት ወዴት በተገኘ? ሁሉም መስማት ቢሆን ማሽተት ወዴት በተገኘ? አሁን ግን እግዚአብሔር እንደ ወደደ ብልቶችን እያንዳንዳቸው በአካል አድርጎአል። ሁሉም አንድ ብልት ቢሆንስ አካል ወዴት በሆነ? ዳሩ ግን አሁን ብልቶች ብዙዎች ናቸው አካል ግን አንድ ነው። ዓይን እጅን፦ አታስፈልገኝም ልትለው አትችልም፥ ወይም ራስ ደግሞ እግሮችን፦ አታስፈልጉኝም ሊላቸው አይችልም። ነገር ግን ደካሞች የሚመስሉ የአካል ብልቶች ይልቁን የሚያስፈልጉ ናቸው፤ ከአካልም ብልቶች ያልከበሩ ሆነው የሚመስሉን በሚበዛ ክብር እናለብሳቸዋለን፥ በምናፍርባቸውም ብልቶቻችን ክብር ይጨመርላቸዋል፤ ክብር ያላቸው ብልቶቻችን ግን ይህ አያስፈልጋቸውም። ነገር ግን ብልቶች እርስ በርሳቸው በትክክል ይተሳሰቡ ዘንድ እንጂ በአካል መለያየት እንዳይሆን፥ ለጎደለው ብልት የሚበልጥ ክብር እየሰጠ እግዚአብሔር አካልን አገጣጠመው። አንድም ብልት ቢሣቀይ ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሣቀያሉ፤ አንድ ብልትም ቢከበር ብልቶች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል። እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ እያንዳንዳችሁም ብልቶች ናችሁ።
1 ቆሮንቶስ 12:4-27 አማርኛ አዲሱ መደበኛ ትርጉም (አማ05)
ልዩ ልዩ የመንፈስ ቅዱስ ስጦታዎች አሉ፤ መንፈስ ቅዱስ ግን አንድ ነው። ልዩ ልዩ አገልግሎቶች አሉ፤ ጌታ ግን አንድ ነው። ልዩ ልዩ የሥራ ዐይነቶችም አሉ፤ ነገር ግን ሁሉንም በሁሉ የሚያከናውን አንዱ እግዚአብሔር ነው። ለእያንዳንዱ መንፈስ ቅዱስን የመግለጥ ስጦታ የሚሰጠው ለጋራ ጥቅም ነው። መንፈስ ቅዱስ ለአንዱ ሰው በጥበብ የመናገር ችሎታን ይሰጠዋል፤ ለሌላው ሰው ደግሞ ያው መንፈስ በዕውቀት የመናገርን ችሎታ ይሰጠዋል፤ ያው አንዱ መንፈስ ለአንዱ እምነትን ይሰጠዋል፤ ለሌላውም የመፈወስ ስጦታን ይሰጠዋል፤ እንዲሁም ለአንዱ ተአምራትን የማድረግ ኀይል ይሰጠዋል፤ ለሌላው የትንቢትን ቃል የመናገር ችሎታ ይሰጠዋል፤ ለሌላው ደግሞ ስጦታዎች ከመንፈስ ቅዱስ መሆናቸውን ወይም ከርኩሳን መናፍስት መሆናቸውን ለይቶ የማወቅ ችሎታን ይሰጠዋል፤ እንዲሁም ለአንዱ በተለያዩ ቋንቋዎች የመናገር ችሎታን ይሰጠዋል፤ ለሌላው ደግሞ በተለያዩ ቋንቋዎች የተነገረውን የመተርጐም ችሎታን ይሰጠዋል፤ ይሁን እንጂ ይህን ሁሉ የሚያደርገው ያው አንዱ መንፈስ ቅዱስ ነው፤ መንፈስ ቅዱስ እንደ ፈቀደ ለእያንዳንዱ ሰው የተለየ ስጦታን ይሰጠዋል። አንድ ሰው ብዙ የአካል ክፍሎች አሉት፤ የአካል ክፍሎች ብዙዎች ሆነው ሳሉ የሚገኙት በዚያው በአንዱ አካል ነው። እንዲሁም ክርስቶስ ብዙ የሰውነት ክፍሎች እንዳሉት እንደ አንድ አካል ነው። አይሁድም ብንሆን የግሪክ ሰዎች ብንሆን፤ ባሪያዎችም ብንሆን፥ ነጻ ሰዎችም ብንሆን፥ አንድ ሰውነት ለመሆን በመንፈስ ቅዱስ ተጠምቀናል፤ ሁላችንም ከዚሁ ከአንዱ መንፈስ ጠጥተናል። አንድ አካል የተሠራው ከብዙ የአካል ክፍሎች እንጂ ከአንድ የአካል ክፍል ብቻ አይደለም! እግር “እኔ እጅ ስላልሆንኩ የአካል ክፍል አይደለሁም!” ቢል ታዲያ እንዲህ በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ ይቀራልን? ጆሮም “እኔ ዐይን ስላልሆንኩ የአካል ክፍል አይደለሁም” ቢል፥ ታዲያ፥ እንዲህ በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ ይቀራልን? አንድ አካል በሙሉ ዐይን ብቻ ቢሆን ኖሮ በምን መስማት ይቻል ነበር? አንድ አካል በሙሉ ጆሮ ብቻ ቢሆን ኖሮ በምን ማሽተት ይቻል ነበር? አሁን ግን እግዚአብሔር እንደ ፈለገው እያንዳንዱን የአካል ክፍል በአካል ውስጥ ተገቢ ስፍራውን ይዞ እንዲገኝ አድርጎታል። ሁላቸውም አንድ ክፍል ብቻ ቢሆን ኖሮ ሙሉ አካል የት በተገኘ ነበር! አሁን ግን ብዙ የአካል ክፍሎች ቢኖሩም አካል ግን አንድ ብቻ ነው። ዐይን እጅን “አንተ አታስፈልገኝም!” ሊለው አይችልም፤ ራስም እግርን “አንተ አታስፈልገኝም!” ሊለው አይችልም፤ እንዲያውም በጣም ደካሞች መስለው የሚታዩ የአካል ክፍሎች ይበልጥ አስፈላጊ ናቸው። አነስተኛ ክብር ያላቸው መስለው ለሚታዩን የአካል ክፍሎች ይበልጥ ክብር እንሰጣቸዋለን፤ ለማየት የሚያሳፍሩ መስለው ለሚታዩን የሰውነት ክፍሎች ይበልጥ ክብር ሰጥተን እንጠነቀቅላቸዋለን፤ ፊት ለፊት ለሚታዩት የአካል ክፍሎች ግን ይህ ሁሉ አያስፈልጋቸውም፤ እግዚአብሔር ግን ለማየት የሚያሳፍሩ መስለው የሚታዩንን የአካል ክፍሎች በበለጠ ክብር እንዲያዙ አድርጎ የአካል ክፍሎችን አገጣጥሞአል። ይህንንም ያደረገው በአካል ክፍሎች መካከል መለያየት ሳይኖር እርስ በርሳቸው እንዲተሳሰቡ ነው። አንዱ የአካል ክፍል ሲሠቃይ ሌሎችም የአካል ክፍሎች በሙሉ አብረው ይሠቃያሉ፤ አንዱ የሰውነት ክፍል ሲከበር ሌሎቹም የሰውነት ክፍሎች አብረው ከእርሱ ጋር ይደሰታሉ። እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ፤ እያንዳንዳችሁም የአካሉ ክፍሎች ናችሁ።
1 ቆሮንቶስ 12:4-27 መጽሐፍ ቅዱስ - (ካቶሊካዊ እትም - ኤማሁስ) (መቅካእኤ)
ልዩ ልዩ ስጦታዎች አሉ፤ መንፈስ ግን አንድ ነው፤ ጌታም አንድ ሲሆን፤ ልዩ ልዩ አገልግሎቶችም አሉ፤ አሠራሮችም ልዩ ልዩ አሉ፤ ሁሉን በሁሉ የሚያደርግ ግን አንዱ እግዚአብሔር ነው። ለእያንዳንዱ የመንፈስን መገለጥ የሚሰጠው ለጥቅም ነው። ለአንዱ ጥበብን መናገር በመንፈስ ይሰጠዋል፤ ለሌላውም ያው መንፈስ እውቀትን መናገር ይሰጠዋል፤ በዚያው መንፈስ ለአንዱ እምነት ይሰጠዋል፤ ለሌላው የመፈወስ ስጦታን በዚያው አንድ መንፈስ ይሰጠዋል፤ ለሌላው ተአምራትን የማድረግ ኃይል ይሰጠዋል፤ ለሌላው ትንቢትን መናገር፥ ለአንዱ መናፍስትን መለየት፥ ለሌላው በልዩ ዓይነት ልሳን መናገር፥ ለሌላውም በልሳኖች የተነገረውን መተርጎም ይሰጠዋል፤ ይህን ሁሉ ግን አንዱና ያው መንፈስ ያደርጋል፤ እንደፈቃዱም ለእያንዳንዱ ሰው ለብቻው እያካፈለ ያደርጋል። አካልም አንድ እንደሆነ ብዙም የአካል ክፍሎች እንዳሉበት ነገር ግን የአካል ክፍሎች ሁሉ ብዙዎች ሳሉ አንድ አካል እንደ ሆኑ፥ ክርስቶስ ደግሞ እንዲሁ ነው፤ አይሁድ ብንሆን የግሪክ ሰዎችም ብንሆን ባርያዎችም ብንሆን ጨዋዎችም ብንሆን እኛ ሁላችን በአንድ መንፈስ አንድ አካል እንድንሆን ተጠምቀናልና። ሁላችንም አንዱን መንፈስ ጠጥተናል። አካል ብዙ የአካል ክፍሎች እንጂ አንድ የአካል ክፍል አይደለምና። እግር “እኔ እጅ አይደለሁምና የአካል ክፍል አይደለሁም፤” ብትል፥ ይህን በማለትዋ የአካል ክፍል መሆንዋ ይቀራልን? ጆሮም “እኔ ዐይን አይደለሁምና የአካል ክፍል አይደለሁም፤” ቢል፥ ይህን በማለቱ የአካል ክፍል መሆኑ ይቀራልን? አካል ሁሉ ዐይን ቢሆን መስማት ወዴት በተገኘ? ሁሉም መስማት ቢሆን ማሽተት ወዴት በተገኘ? አሁን ግን እግዚአብሔር እንደ ወደደ የአካል ክፍሎችን እያንዳንዳቸው በአካል አድርጎአል። ሁሉም አንድ የአካል ክፍል ቢሆንስ አካል ወዴት በሆነ? ዳሩ ግን አሁን የአካል ክፍሎች ብዙዎች ናቸው፤ አካል ግን አንድ ነው። ዐይን እጅን “አታስፈልገኝም፤” ልትለው አትችልም፤ ወይም ራስ ደግሞ እግሮችን “አታስፈልጉኝም፤” ሊላቸው አይችልም። ነገር ግን ደካሞች የሚመስሉ የአካል ክፍሎች ይልቁን የሚያስፈልጉ ናቸው፤ ከአካልም ክፍሎች ያልከበሩ ሆነው የሚመስሉንን በሚበዛ ክብር እናለብሳቸዋለን፤ በምናፍርባቸውም የአካላችን ክፍሎች ክብር ይጨመርላቸዋል፤ ፊት ለፊት ለሚታዩት የአካላችን ክፍሎች ግን ይህ አያስፈልጋቸውም። እግዚአብሔር ግን ለማየት የሚያሳፍሩ መስለው የሚታዩንን የአካል ክፍሎች በበለጠ ክብር እንዲያዙ አድርጎ የአካል ክፍሎችን አስማምቷል። ይህም በአካል ክፍሎች መካከል መለያየት ሳይኖር እርስ በርሳቸው እንዲተሳሰቡ ነው። አንድም አካል ቢሠቃይ የአካል ክፍሎች ሁሉ ከእርሱ ጋር ይሠቃያሉ፤ አንድ አካልም ቢከበር የአካል ክፍሎች ሁሉ ከእርሱ ጋር ደስ ይላቸዋል። እናንተም የክርስቶስ አካል ናችሁ፤ እያንዳንዳችሁም የአካሉ ክፍሎች ናችሁ።