ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1 11
11
የመምህራንን ፍለጋ መከተል
1 #
1ቆሮ. 4፥16፤ ፊል. 3፥17። እኔ ክርስቶስን እንደምመስለው እኔን ምሰሉ።
2ወንድሞች ሆይ፥ አመሰግናችኋለሁ፤ ዘወትር ታስቡኛላችሁና፤ ያስተማርኋችሁንም ትምህርት ጠብቃችኋልና። 3ነገር ግን የወንድ ሁሉ ራሱ ክርስቶስ፥ የሴትም ራስዋ ወንድ፤ የክርስቶስም ራሱ እግዚአብሔር እንደ ሆነ ልታውቁ እወድዳለሁ።
የጸሎት ሥርዐት
4ራሱን ተከናንቦ የሚጸልይ ወይም የሚያስተምር ወንድ ሁሉ ራሱን ያዋርዳል። 5ራስዋን ሳትከናነብ የምትጸልይ ወይም የምታስተምር ሴት ሁላ ራስዋን ታዋርዳለች፤ ራስዋን እንደ ተላጨች መሆንዋ ነውና። 6ሴት ካልተከናነበች ትላጭ ወይም ጠጕርዋን ትቈረጥ፤ ለሴት ጠጕርዋን መቈረጥ ወይም መላጨት ውርደት ከሆነ ትከናነብ። 7#ዘፍ. 1፥26-27። ወንድ በሚጸልይበት ጊዜ#“በሚጸልይበት ጊዜ” የሚለው በግሪኩ የለም። ሊከናነብ አይገባውም፤ የእግዚአብሔር አርአያውና አምሳሉ #ግሪኩ “አርአያውና ክብሩ” ይላል። ነውና፤ ሴትም ለባልዋ ክብር ናት። 8ሴት ከወንድ ተገኝታለችና፤ ወንድ ግን ከሴት የተገኘ አይደለም። 9#ዘፍ. 2፥18-23። ወንድ ስለ ሴት አልተፈጠረም፤ ሴት ስለ ወንድ ተፈጠረች እንጂ። 10ስለዚህም ሴት ስለ መላእክት፥ ሥልጣን ለራስዋ ሊሆን ይገባል፤#ምሥጢሩ ትከናነብ ማለት ነው። 11ነገር ግን አሁን ሴት ከባሏ አትለይ፤ ወንድም ከሚስቱ አይለይ፤ ሁላችሁም በጌታችን ኑሩ።#ግሪኩ “... በጌታ ዘንድ ሴት ያለወንድ ወንድም ያለሴት አይሆንም” ይላል። 12ሴት ከወንድ እንደ ተገኘች እንዲሁ ወንድ ከሴት ተገኘ፤ ነገር ግን ሁሉ ከእግዚአብሔር ነው። 13እስኪ እናንተ ራሳችሁ ፍረዱ፤ ሴት ወደ እግዚአብሔር በምትጸልይበት ጊዜ ልትከናነብ አይገባምን? 14ተፈጥሮዋስ አያስረዳችሁምን? ወንድ ግን ጠጕሩን ቢያሳድግ ነውር ነው። 15ለሴት ግን ጠጕርዋን ብታሳድግ ክብርዋ ነው፤ ለሴት ጠጕርዋ እንደ ቀጸላ ሆኖ ተሰጥቶአታልና። 16ነገር ግን የሚጠራጠር ቢኖር እኛ ወይም የእግዚአብሔር ቤተ ክርስቲያን እንዲህ ያለ ልማድ የለንም።
ጸብና ክርክር እንደማይገባ
17ይህንም የነገርኋችሁ ላመሰግናችሁ አይደለም፤ በምትሰበሰቡበት ጊዜ ወደ ዝቅተኛ እንጂ ወደሚሻል ግብር አትሄዱምና። 18ከሁሉ አስቀድሞ በቤተ ክርስቲያን በምትሰበሰቡ ጊዜ እንደምትጣሉና እንደምትከራከሩ ሰምቻለሁ፤ የማምነውም አለኝ። 19ከእናንተ የተመረጡት ወንድሞች ተለይተው እንዲታወቁ ትለያዩ ዘንድ ግድ ነው። 20እንግዲህ እናንተም በምትሰበሰቡበት ጊዜ የምትበሉና የምትጠጡ ለጌታችን ቀን#ግሪኩ “የጌታን እራት የምትበሉ አይደለም” ይላል። እንደሚገባ አይደለም። 21ወደ ምግብ ትሽቀዳደማላችሁ፤ የተራቡ በአጠገባችሁ እያሉ እናንተ ትበላላችሁ፤ ትጠግባላችሁ፤ ትሰክራላችሁም።#ምዕ. 11 ቍ. 21 ግሪኩ “በመብላት ጊዜ እያንዳንዱ የራሱን እራት ይበላልና አንዱም ይራባል አንዱ ግን ይሰክራል” ይላል። 22በውኑ የምትበሉበትና የምትጠጡበት ቤት የላችሁምን? ወይስ የእግዚአብሔርን ቤተ ክርስቲያን ታስነቅፋላችሁን? ነዳያንንስ ታሳፍሩአቸዋላችሁን? ምን እላለሁ? በዚህ አመሰግናችኋለሁን? አላመሰግናችሁም።
ስለ ጌታችን ሥጋና ደም
23ከእግዚአብሔር እንደ ተማርሁ አስተምሬአችኋለሁና፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እርሱን ራሱን በያዙባት በዚያች ሌሊት ኅብስቱን አነሣ። 24አመሰገነ፤ ባረከ፤#“ባረከ” የሚለው በግሪኩ የለም። ፈተተ፤ እንዲህም አላቸው፥ “እንኩ ብሉ፤ ስለ እናንተ የሚሰጠው ሥጋዬ ይህ ነው፤ መታሰቢያዬንም እንዲሁ አድርጉ።” 25#ዘፀ. 24፥6-8፤ ኤር. 31፥31-34። እንዲሁም ኅብስቱን ከተቀበሉ በኋላ ጽዋውን አንሥቶ፥ “አዲስ ሥርዐት የሚጸናበት ይህ ጽዋ ደሜ ነው እንዲህ አድርጉ፤ በምትጠጡበትም ጊዜ አስቡኝ” አላቸው። 26ይህን ኅብስት በምትበሉበት፥ ይህንም ጽዋ በምትጠጡበት ጊዜ ሁሉ ጌታችን እስከሚመጣበት ቀን ድረስ ሞቱን ትናገራላችሁ።
27አሁንም ሳይገባው ይህን ኅብስት የበላ፥ ይህንም ጽዋ የጠጣ የጌታችን ሥጋውና ደሙ ስለሆነ ዕዳ አለበት። 28አሁንም ሰው ራሱን መርምሮና አንጽቶ ከዚህ ኅብስት ይብላ፤ ከዚህም ጽዋ ይጠጣ። 29ሳይገባው፥ የጌታችን ሥጋም እንደ ሆነ ሳያውቅ፥ ሰውነቱንም ሳያነጻ፥#“ሰውነቱንም ሳያነጻ” የሚለው በግሪኩ የለም። የሚበላና የሚጠጣ ለራሱ ፍርዱንና መቅሠፍቱን ይበላል፤ ይጠጣልም። 30ስለዚህ ከመካከላችሁ የደከሙና የታመሙ ብዙዎች ናቸው፤ ብዙዎችም በድንገት አንቀላፍተዋል። 31እኛ በራሳችን ብንፈርድ ኖሮ ባልተፈረደብንም ነበር። 32ነገር ግን በተፈረደብን ጊዜ ከዓለም ጋር እንዳንኰነን በጌታ እንገሠጻለን።
33አሁንም ወንሞቻችን ሆይ፥ ለምሳ በምትሰበሰቡበት ጊዜ እርስ በርሳችሁ ተጠባበቁ፤ 34መሰብሰባችሁ ለፍዳ እንዳይሆን፥ የተራበ ቢኖር በቤቱ ይብላ፤ አትነቃቀፉም፤#“አትነቃቀፉም” የሚለው በግሪኩ የለም። ሌላውን ሥርዐት ግን መጥቼ እሠራላችኋለሁ።
Currently Selected:
ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 1 11: አማ2000
ማድመቅ
Share
Copy
ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ