መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ 15
15
የእግዚአብሔርን ታቦት ለማምጣት የተደረገ ዝግጅት
1ዳዊትም በከተማው ለራሱ ቤቶችን ሠራ፤ ለእግዚአብሔርም ታቦት ስፍራ አዘጋጀ፤ ድንኳንም ተከለላት። 2በዚያን ጊዜም ዳዊት፥ “የእግዚአብሔርን ታቦት ይሸከሙ ዘንድ፥ ለዘለዓለሙም ያገለግሉት ዘንድ እግዚአብሔር ከመረጣቸው ከሌዋውያን በቀር ማንም የእግዚአብሔርን ታቦት ይሸከም ዘንድ አይገባውም” አለ። 3ዳዊትም ወዳዘጋጀላት ስፍራ የእግዚአብሔርን ታቦት ያመጣ ዘንድ እስራኤልን ሁሉ ወደ ኢየሩሳሌም ሰበሰበ። 4ዳዊትም የአሮንን ልጆችና ሌዋውያንን ሰበሰበ። 5ከቀዓት ልጆች፤ አለቃው ኡርኤል፥ ወንድሞቹም መቶ ሃያ፤ 6ከሜራሪ ልጆችም፤ አለቃው ዓሣያ፥ ወንድሞቹም ሁለት መቶ ኀምሳ፤#ዕብ. እና አንዳንድ የግሪክ ሰባ. ሊ. ዘርዕ “ሁለት መቶ ሃያ” ይላል። 7ከጌድሶን ልጆች፤ አለቃው ኢዮሔት፥ ወንድሞቹም መቶ ሠላሳ፤ 8ከኤልሳፋን ልጆች፤ አለቃው ሰማያ፥ ወንድሞቹም ሁለት መቶ፤ 9ከኬብሮን ልጆች፤ አለቃው ኢዮሔል፥ ወንድሞቹም ሰማንያ፤ 10ከዑዝኤል ልጆች፤ አለቃው አሚናዳብ፥ ወንድሞቹም መቶ ዐሥራ ሁለት። 11ዳዊትም ካህናቱን ሳዶቅንና አብያታርን፥ ሌዋውያንንም፥ ኡርኤልን፥ ዓሣያን፥ ኢዮኤልን፥ ሰማያን፥ ኤሊኤልን፥ አሚናዳብንም ጠርቶ፦ 12“እናንተ የሌዋውያን አባቶች ቤቶች አለቆች ናችሁ፤ ወዳዘጋጀሁላት ስፍራ የእስራኤልን አምላክ የእግዚአብሔርን ታቦት ታመጡ ዘንድ እናንተና ወንድሞቻችሁ ተቀደሱ። 13በቀድሞ ሥራችን አምላካችን እግዚአብሔር እርስ በርሳችን አላጠፋንም፤ በጦር አልፈለገንምና” አላቸው።#ዕብ. “ቀድሞም እናንተ ያንን አላደረጋችሁምና እንደ ሥርዐቱም ስለ አልፈለግነው አምላካችን እግዚአብሔር በመካከላችን ስብራትን አደረገ አላቸው” ይላል። 14የእስራኤልንም አምላክ የእግዚአብሔርን ታቦት ያመጡ ዘንድ ካህናቱና ሌዋውያኑ ራሳቸውን አነጹ። 15በመጽሐፍም እንደ ተጻፈ ሙሴ በእግዚአብሔር ቃል እንደ አዘዛቸው የሌዋውያን ልጆች የእግዚአብሔርን ታቦት በትከሻቸው ላይ በመሎጊያዎቹ ተሸከሙ። መባእና ቍርባንም ከእነርሱ ጋር ነበረ።#“መባእና ቍርባንም ከእነርሱ ጋር ነበረ” የሚለው በግእዝ ብቻ ነው።
16ዳዊትም በዜማ ዕቃ፥ በመሰንቆና በበገና፥ በጸናጽልም እንዲያዜሙ፥ ድምፃቸውንም በደስታ ከፍ እንዲያደርጉ መዘምራኑን “ወንድሞቻችሁን ሹሙ” ብሎ ለሌዋውያን አለቆች ተናገረ። 17ሌዋውያኑም የኢዩኤልን ልጅ ኤማንን፥ ከወንድሞቹም የበራክያን ልጅ አሳፍን፥ ከወንድሞቻቸውም ከሜራሪ ልጆች የቂሳንን ልጅ ኢታንን፥ 18ከእነርሱም ጋር በሁለተኛው ተራ የሆኑትን ወንድሞቻቸውን ዘካርያስን፥ ቤንን፥#“ቤንን” የሚለው በግሪክና በግእዝ የለም። አዝኤልን፥ ስሜራሞትን፥ ኢያሄልን፥ ኡኒን፥ ኤልያብን፥ በናእያን፥ መዕሤያን፥ መታትያን፥ ኤልፋይን፥ ሜቄድያን፥ በረኞችንም አብዲዶምን፥ ኢያኤልንና ዖዝያስን አቆሙ። 19መዘምራንም ኤማንና አሳፍ ኤታንም በናስ ጸናጽል ከፍ አድርገው ያሰሙ ነበር። 20ዘካርያስ፥ አዝኤል፥ ሰሚራሞት፥ ኢያሔል፥ ዑኒ፥ ኤልያብ፥ መዕሤያ፥ በናያስ በመሰንቆ በልዑል ቃል ያዜሙ ነበር። 21ማታትያስ፥ ኤልፋላይ፥ ሜቄድያስ፥ አብዴዶም፥ ይዒኤል፥ ዖዝያስም ስምንት አውታር ባለው በገና ይዘምሩ ነበር። 22የሌዋውያኑም አለቃ ኮነንያስ በዜማ ላይ ተሾሞ ነበር። ብልሃተኛ ነበረና።#ዕብ. “ዜማ ያስተምራቸው ነበር” የሚል ይጨምራል። 23በራክያና ሕልቃናም ለታቦቷ በረኞች ነበሩ። 24ካህናቱም ሰበንያ፥ ኢዮሣፍጥ፥ ናትናኤል፥ ዓማሣይ፥ ዘካርያስ፥ በናያስ፥ አልዓዛርም በእግዚአብሔር ታቦት ፊት መለከት ይነፉ ነበር። አብዲዶምና ኢያኤያም የእግዚአብሔር ታቦት በረኞች ነበሩ።
25ዳዊትም፥ የእስራኤልም ሽማግሌዎች፥ የሻለቆችም የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት ከአቢዳራ ቤት በደስታ ያመጡ ዘንድ ሄዱ። 26የእግዚአብሔርንም ቃል ኪዳን ታቦት የተሸከሙትን ሌዋውያንን እግዚአብሔር በአበረታቸው ጊዜ ሰባት በሬዎችንና ሰባት አውራ በጎችን ሠዉ። 27ዳዊትም፥ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳኑን ታቦት የተሸከሙ ሌዋውያንም ሁሉ፥ መዘምራኑም፥ የመዘምራኑም አለቃ ኮኖንያስ የጥሩ በፍታ ቀሚስ ለብሰው ነበር፤ ዳዊትም የከበረ ልብስ ለብሶ ነበረ። 28እንዲሁ እስራኤል ሁሉ በይባቤ፥ ቀንደ መለከትና እንቢልታ እየነፉ፥ ጸናጽልና መሰንቆም፥ በገናም እየመቱ፥ የእግዚአብሔርን የቃል ኪዳን ታቦት አመጡ።
29የእግዚአብሔርም ቃል ኪዳን ታቦት ወደ ዳዊት ከተማ በደረሰች ጊዜ የሳኦል ልጅ ሜልኮል በመስኮት ሆና ተመለከተች፤ ንጉሡም ዳዊት ሲዘፍንና ሲጫወት አይታ በልብዋ ናቀችው።
Currently Selected:
መጽሐፈ ዜና መዋዕል ቀዳማዊ 15: አማ2000
ማድመቅ
ያጋሩ
ኮፒ

ያደመቋቸው ምንባቦች በሁሉም መሣሪያዎችዎ ላይ እንዲቀመጡ ይፈልጋሉ? ይመዝገቡ ወይም ይግቡ