እኔ ተኝቻለሁ፥ ልቤ ግን ነቅቶአል፥ የውዴ ድምፅ ነው፥ እርሱም ያንኳኳል፥ እኅቴ፥ ወዳጄ፥ ርግቤ፥ የእኔ እንከን የለሽ፥ ራሴ በጠል፥ ጸጉሬም በሌሊት ነጠብጣብ ርሶአል። ቀሚሴን አወለቅሁ፥ እንዴት እለብሰዋለሁ? እግሬን ታጠብሁ፥ እንዴት አሳድፈዋለሁ? ውዴ እጁን በቀዳዳ ሰደደ፥ አንጀቴም ስለ እርሱ ታወከ። ለውዴ እከፍትለት ዘንድ ተነሣሁ፥ እጆቼ በደጁ መወርወሪያ ላይ ከርቤን አፈሰሱ፥ ጣቶቼ ፈሳሹን ከርቤ አንጠባጠቡ። ለውዴ ከፈትሁለት፥ ውዴ ግን ፈቀቅ ብሎ አልፎ ነበር። ነፍሴ ከመራቁ የተነሣ ደነገጠች፥ ፈለግሁት፥ አላገኘሁትም፥ ጠራሁት፥ ነገር ግን አልመለሰልኝም። ከተማይቱን የሚዞሩት ጠባቂዎች አገኙኝ፥ መቱኝ፥ አቈሰሉኝም፥ ቅጥር ጠባቂዎችም የዓይነ ርግብ መሸፈኛዬን ወሰዱት። እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ አስምላችኋለሁ፥ ውዴን ያገኛችሁት እንደሆነ፥ እኔ ከፍቅር የተነሣ መታመሜን ንገሩት። አንቺ በሴቶች ዘንድ የተዋብሽ ሆይ፥ ከሌላ ወዳጅ ይልቅ ፍቅረኛሽ ምን አለው? ይህን የሚያህል የምታስምይን? ከሌላ ወዳጅ ይልቅ ፍቅረኛሽ ምን አለው? ውዴ ብሩህና ቀይ ነው፥ ከእልፍ የተመረጠ ነው። ራሱ ምዝምዝ ወርቅ ነው፥ ጸጉሩ የተዝረፈረፈ ነው፥ እንደ ቁራም ጥቁር ነው። ዐይኖቹ በውሃ ምንጮች አጠገብ እንዳሉ በወተት እንደ ታጠቡ በፈሳሽ ውኃ አጠገብ እንደ ተቀመጡ እንደ ርግቦች ናቸው። ጉንጩና ጉንጩ የሽቱ መደብ እርከን እንዳለበት እንደ ሽቱ አትክልት ናቸው፥ ከንፈሮቹ እንደ አበቦች ናቸው፥ የሚፈስስ ከርቤንም ያንጠበጥባሉ። እጆቹ የቢረሌ ፈርጥ ያለበት የወርቅ ቀለበት ናቸው፥ አካሉ በሰንፔር ያጌጠ የዝሆን ጥርስ ነው። እግሮቹ በምዝምዝ ወርቅ ላይ የተመሠረቱ የዕብነ በረድ ምሰሶች ናቸው፥ መልኩ እንደ ሊባኖስ፥ እንደ ዝግባ ዛፍ ምርጥ ነው። አፉ እጅግ ጣፋጭ ነው፥ እርሱም ፈጽሞ ያማረ ነው፥ እናንተ የኢየሩሳሌም ቈነጃጅት ሆይ፥ ውዴ ይህ ነው፥ ባልንጀራዬም ይህ ነው።
መኃልየ መኃልይ 5 ያንብቡ
ያጋሩ
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: መኃልየ መኃልይ 5:2-16
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
ቤት
መጽሐፍ ቅዱስ
እቅዶች
ቪዲዮዎች