ወደ ሮሜ ሰዎች 7:13-25

ወደ ሮሜ ሰዎች 7:13-25 መቅካእኤ

እንግዲህ መልካም የሆነው ነገር ሞት ሆነብኝን? በጭራሽ! ነገር ግን ኃጢአት ኃጢአትነቱ እንዲታይ፥ መልካም በሆነው ነገር ሞትን ይሠራብኝ ነበር። ይኸውም ኃጢአት በትእዛዝ አማካይነት ያለ ልክ ኃጢአት እንዲሆን ነው። ሕግ መንፈሳዊ መሆኑን እናውቃለን፤ እኔ ግን ከኃጢአት በታች ልሆን የተሸጥሁ የሥጋ ነኝ። ምን እየሠራሁ እንደሆነ አላውቅም፤ የምፈልገውን ነገር አላደርግም፤ ነገር ግን የምጠላውን ነገር አደርጋለሁና። እንግዲህ የማልፈልገውን ነገር የማደርግ ከሆነ ሕግ ትክክል ነው እላለሁ። እንግዲህ አሁን ይህን የማደርገው እኔ ሳልሆን፥ በእኔ ውስጥ የሚያድረው ኃጢአት ነው። በእኔ ማለትም በሥጋዬ ምንም መልካም ነገር እንደማይኖር አውቃለሁና፤ መልካምን የማድረግ ፍላጎት ቢኖረኝም ነገር ግን ልፈፅመው አልችልም። ማድረግ የምፈልገውን መልካም ነገር አላደርግም፥ ነገር ግን ማድረግ የማልፈልገውን ክፉ ነገር አደርጋለሁና። የማልፈልገውን ነገር የማደርግ ከሆነ፥ ያን የማደርገው እኔ ሳልሆን በእኔ ውስጥ የሚያድረው ኃጢአት ነው። ስለዚህ መልካም ነገርን ማድረግ ስፈልግ ክፋት ወደ እኔ ይቀርባል፤ ይኸውም ሕግ ሆኖ አግኝቼዋለሁ። በውስጣዊ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለኛልና፥ ነገር ግን ከአእምሮዬ ሕግ ጋር የሚዋጋውንና በሰውነቴ ክፍሎች ባለ በኃጢአት ሕግ ምርኮኛ የሚያደርገኝ ሌላ ሕግ በሰውነቴ ክፍሎች አያለሁ። እኔ ምንኛ ጎስቋላ ሰው ነኝ! ከዚህ ለሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ያድነኛል? በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን። እንግዲያስ እኔ ራሴ በአእምሮዬ ለእግዚአብሔር ሕግ ባርያ ስሆን፥ በሥጋዬ ግን ለኃጢአት ሕግ ባርያ ነኝ።