የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ሮሜ 7:13-25

ሮሜ 7:13-25 NASV

ታዲያ በጎ የሆነው ነገር ሞት ሆነብኝን? ከቶ አይሆንም! ነገር ግን ኀጢአት በኀጢአትነቱ ይታወቅ ዘንድ በጎ በሆነው ነገር በኩል ሞትን አመጣብኝ፤ ይኸውም ኀጢአት በትእዛዝ በኩል ይብሱን ኀጢአት ይሆን ዘንድ ነው። ሕጉ መንፈሳዊ እንደ ሆነ እናውቃለን፤ እኔ ግን ለኀጢአት እንደ ባሪያ የተሸጥሁ ሥጋዊ ነኝ። የማደርገውን አላውቅም፤ ለማድረግ የምፈልገውን አላደርግም፤ ነገር ግን የምጠላውን ያን አደርጋለሁና። ማድረግ የማልፈልገውን የማደርግ ከሆነ፣ ሕጉ በጎ እንደ ሆነ እመሰክራለሁ፤ እንዲህ ከሆነ፣ ይህን የማደርገው እኔ ራሴ ሳልሆን፣ በእኔ ውስጥ የሚኖረው ኀጢአት ነው። በእኔ፣ ማለትም ኀጢአተኛ በሆነው ተፈጥሮዬ ውስጥ ምንም በጎ ነገር እንደማይኖር ዐውቃለሁ፤ በጎ የሆነውን የማድረግ ምኞት አለኝ፤ ነገር ግን ልፈጽመው አልችልም። የማደርገው ላደርገው የምፈልገውን በጎ ነገር አይደለም፤ ዳሩ ግን ለማድረግ የማልፈልገውን ክፉ ነገር ነው። ላደርገው የማልፈልገውን ነገር የማደርገው ከሆነ፣ ያን የማደርገው እኔ ራሴ ሳልሆን፣ የሚያደርገው በእኔ ውስጥ የሚኖረው ኀጢአት ነው። ስለዚህ ይህ ሕግ እየሠራ እንደ ሆነ ተረድቻለሁ፤ ይኸውም በጎ ነገር ለመሥራት ስፈልግ፣ ክፋት ከእኔ ጋራ አለ። በውስጤ በእግዚአብሔር ሕግ ሐሤት አደርጋለሁ፤ ነገር ግን በብልቶቼ ውስጥ ለሚሠራው የኀጢአት ሕግ እኔን እስረኛ በማድረግ፣ ከአእምሮዬ ሕግ ጋራ የሚዋጋ ሌላ ሕግ በብልቶቼ ውስጥ ሲሠራ አያለሁ። እኔ ምን ዐይነት ጐስቋላ ሰው ነኝ! ከዚህ ለሞት ከተሰጠ ሰውነት ማን ሊያድነኝ ይችላል? በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ምስጋና ለእግዚአብሔር ይሁን! እንግዲያስ እኔ ራሴ በአእምሮዬ ለእግዚአብሔር ሕግ ባሪያ ስሆን፣ በኀጢአተኛ ተፈጥሮዬ ግን ለኀጢአት ሕግ ባሪያ ነኝ።