የYouVersion አርማ
የፍለጋ አዶ

ወደ ሮም ሰዎች 7:13-25

ወደ ሮም ሰዎች 7:13-25 አማ05

ታዲያ፥ ይህ መልካም የሆነው ነገር በእኔ ሞትን አመጣብኝ ማለት ነውን? አይደለም! ነገር ግን ኃጢአት፥ ኃጢአት ሆኖ እንዲገለጥ በመልካሙ ነገር አማካይነት ሞትን አመጣብኝ፤ ስለዚህ ኃጢአት በትእዛዝ አማካይነት የበለጠ ኃጢአተኛ ሆነ። ሕግ መንፈሳዊ መሆኑን እናውቃለን። እኔ ግን የኃጢአት ባሪያ ለመሆን የተሸጥሁ ሥጋዊ ነኝ። እኔ የማደርገውን አላውቅም፤ የምወደውን ነገር ማድረግ ትቼ የምጠላውን ነገር አደርጋለሁ። እንግዲህ እኔ የማደርገው የማልፈልገውን ነገር ከሆነ ሕግ መልካም እንደ ሆነ እመሰክራለሁ። ማድረግ የማልፈልገውን ነገር የሚያደርገው በእኔ ውስጥ ያለው ኃጢአት ነው እንጂ እኔ አይደለሁም። በእኔ ወይም በእኔ ሥጋዊ ባሕርይ ምንም መልካም ነገር እንደሌለ ዐውቃለሁ፤ መልካም ነገርን የማድረግ ፍላጎት ቢኖረኝም እንኳ ያን መልካም ነገር ለማድረግ ችሎታ የለኝም። ማድረግ የምፈልገውን መልካም ነገርን አላደርግም፤ ዳሩ ግን የማልፈልገውን ክፉ ነገር አደርጋለሁ። ማድረግ የማልፈልገውን ክፉ ነገር የማደርግ ከሆንኩ ይህን የሚያደርገው በእኔ ውስጥ ያለው ኃጢአት ነው እንጂ እኔ አይደለሁም ማለት ነው። ስለዚህ ሕግ በሥራ ላይ ውሎ አያለሁ፤ መልካም ነገርን ማድረግ ስፈልግ ክፉ ነገርን ለማድረግ እገደዳለሁ። ውስጣዊ ሰውነቴ በእግዚአብሔር ሕግ ደስ ይለዋል። ይሁን እንጂ ከአእምሮዬ ሕግ ጋር እየተቃረነ በሰውነቴ ክፍሎች ውስጥ ለሚሠራው የኃጢአት ሕግ እስረኛ የሚያደርገኝ ሌላ የተፈጥሮ ዝንባሌ በሰውነቴ ክፍሎች ውስጥ መኖሩን አያለሁ። እኔ ምንኛ ጐስቋላ ሰው ነኝ! ከዚህ ሟች ሰውነትስ ማን ያድነኛል? በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል ለሚያድነኝ ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን! እንግዲህ እኔ በአእምሮዬ፥ ለእግዚአብሔር ሕግ ተገዢ ስሆን በሥጋ ባሕርዬ ለኃጢአት ሕግ ተገዢ ሆኜአለሁ።