ወደ ሮሜ ሰዎች 11:25-36

ወደ ሮሜ ሰዎች 11:25-36 መቅካእኤ

ወንድሞች ሆይ! አላዋቂዎች እንድትሆኑ አልፈልግም፤ ይህን ምሥጢር እንድታውቁ እወዳለሁ፤ የአሕዛብ ሙላት እስኪገባ ድረስ እስራኤል በከፊል መደንዘዝ ሆነበት፤ እንደዚሁም እስራኤል ሁሉ ይድናል፤ እንዲህ ተብሎ እንደ ተጻፈ “አዳኝ ከጽዮን ይወጣል፤ ከያዕቆብም ክፋትን ያስወግዳል። ኃጢአታቸውንም ስወስድላቸው ከእነርሱ ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነው። በወንጌልስ በኩል በእናንተ ምክንያት ጠላቶች ናቸው፤ በምርጫ በኩል ግን በአባቶች ምክንያት ተወዳጆች ናቸው፤ እግዚአብሔር በጸጋው ስጦታና በመጥራቱ አይጸጸትምና። እናንተም ቀድሞ ለእግዚአብሔር እንዳልታዘዛችሁ፥ አሁን ግን በማይታዘዙት ምክንያት ምሕረት እንዳገኛችሁ፥ እንዲሁም እናንተ ያገኛችሁትን ምሕረት፥ እነርሱ ደግሞ ምሕረትን እንዲያገኙ፥ እነዚህ ደግሞ አሁን አልታዘዙም። እግዚአብሔር በሁሉም ላይ ምሕረቱን ለማሳየት ሁሉን በአለመታዘዝ ዘግቶታልና።” የእግዚአብሔር ባለጸግነትና ጥበብ እውቀቱም እንዴት ጥልቅ ነው! ፍርዱ እንዴት የማይመረመር ነው! መንገዱም የማይታወቅ ነው። “የጌታን ልብ የሚያውቅ ማን ነው?” “ወይስ አማካሪው የሆነ ማን ነው? ወይስ ብድሩን እንዲመልስ ለእርሱ አስቀድሞ የሰጠው ማን ነው?” ሁሉም ከእርሱ፥ በእርሱና ለእርሱም ነውና፤ ክብር ለዘለዓለም ለእርሱ ይሁን፤ አሜን።