ወደ ሮም ሰዎች 11:25-36

ወደ ሮም ሰዎች 11:25-36 አማ05

ወንድሞቼ ሆይ! “ዐዋቂዎች ነን” ብላችሁ አትመኩ፤ የምነግራችሁ አንድ ምሥጢር አለ፤ ይኸውም የእስራኤላውያን እምቢተኛነት ለዘለቄታው ሳይሆን አሕዛብ ሁሉ በሙላት ወደ እግዚአብሔር እስኪመጡ ድረስ መሆኑን ነው። እንግዲህ በዚህ ዐይነት እስራኤላውያን ሁሉ ይድናሉ። ስለዚህም እንዲህ ተብሎ ተጽፎአል፦ “አዳኝ ከጽዮን ይመጣል፤ ከያዕቆብም ዘር ሁሉ ክፋትን ያስወግዳል፤ ኃጢአታቸውንም በደመሰስኩላቸው ጊዜ ከእነርሱ ጋር የምገባው ቃል ኪዳን ይህ ነው።” እስራኤላውያን የወንጌልን ቃል ባለመቀበላቸው ስለ እናንተ ስለ አሕዛብ ጥቅም የእግዚአብሔር ጠላቶች ሆነዋል፤ ነገር ግን በምርጫ በኩል በነገድ አባቶች ምክንያት የእግዚአብሔር ወዳጆች ናቸው። እግዚአብሔር ከመረጠና ጸጋውን ከሰጠ በኋላ ባደረገው ነገር ሐሳቡን አይለውጥም። እናንተ አሕዛብ ቀድሞ ለእግዚአብሔር የማትታዘዙ ነበራችሁ፤ አሁን ግን አይሁድ ባለመታዘዛቸው ምክንያት እናንተ የእግዚአብሔርን ምሕረት አገኛችሁ። እናንተ ምሕረትን ባገኛችሁበት ዐይነት እነርሱም ምሕረትን እንዲያገኙ እነርሱ አሁን ለእግዚአብሔር የማይታዘዙ ሆነዋል። እግዚአብሔር ምሕረቱን ለሰው ሁሉ ለማሳየት ሲል ሰዎችን ሁሉ የእምቢተኛነታቸው እስረኞች እንዲሆኑ አደረጋቸው። የእግዚአብሔር ባለጸግነትና ጥበብ ዕውቀትም እንዴት ጥልቅ ነው! ፍርዱ የማይመረመር፥ መንገዱም የማይታወቅ ነው። “የጌታን አሳብ የሚያውቅ ማነው? የእርሱ አማካሪ የሚሆንስ ማነው? ለእግዚአብሔር የሚያበድርና ያበደረውንም የሚወስድ ማነው?” ሁሉም ነገር የተገኘው ከእርሱ፥ በእርሱና ለእርሱ ነው፤ ለዘለዓለም ክብር ለእርሱ ይሁን! አሜን!