ከዚህ በኋላ ታላቅ ሥልጣን ያለው ሌላ መልአክ ከሰማይ ሲወርድ አየሁ፤ ከክብሩም የተነሣ ምድር በራች። በብርቱም ድምፅ “ታላቂቱ ባቢሎን ወደቀች! ወደቀች! የአጋንንትም ማደሪያ ሆነች፤ የርኩሳንም መናፍስት ሁሉ መጠጊያ የርኩሳንና የተጠሉም ወፎች ሁሉ መጠጊያ ሆነች፤ አሕዛብ ሁሉ ከዝሙትዋ ቁጣ ወይን ጠጅ ጠጥተዋልና፤ የምድርም ነገሥታት ከእርሷ ጋር ሴስነዋልና፤ የምድርም ነጋዴዎች ከቅምጥልነትዋ ኃይል የተነሣ ሀብታሞች ሆነዋልና፤” ብሎ ጮኸ። ከሰማይም ሌላ ድምፅ እንዲህ ሲል ሰማሁ “ሕዝቤ ሆይ! በኃጢአትዋ እንዳትተባበሩ ከመቅሠፍትዋም እንዳትቀበሉ ከእርሷ ዘንድ ውጡ፤ ኃጢአትዋ እስከ ሰማይ ድረስ ደርሶአልና፤ እግዚአብሔርም ዐመፃዋን አስታወሰ። እርሷ በሰጠችው መጠን መልሱላት፤ እንደ ሥራዋም ሁለት እጥፍ ደርቡባት፤ በቀላቀለችው ጽዋ ሁለት እጥፍ አድርጋችሁ ቀላቅሉባት፤ ራስዋን በአከበረችበትና በተቀማጠለችበት ልክ ሥቃይንና ኀዘንን ስጡአት። በልብዋ ‘ንግሥት ሆኜ እቀመጣለሁ፤ መበለትም አልሆንም፤ ኀዘንም ከቶ አላይም፤’ ስላለች፥ ስለዚህም ሞትና ኀዘን፥ ራብም የሆኑት መቅሰፍቶችዋ በአንድ ቀን ይመጣሉ፤ በእሳትም ትቃጠላለች፤ የሚፈርድባት ጌታ እግዚአብሔር ብርቱ ነውና።” ከእርሷም ጋር የሴሰኑና የተቀማጠሉ የምድር ነገሥታት የመቃጠልዋን ጢስ ሲያዩ ስለ እርሷ እየጮሁ ያለቅሳሉ፤ ሥቃይዋንም ከመፍራት የተነሣ በሩቅ ቆመው “አንቺ ታላቂቱ ከተማ! ብርቱይቱ ከተማ ባቢሎን! ወዮልሽ! ወዮልሽ! በአንድ ሰዓት ውስጥ ፍርድሽ ይፈጸማልና፤” እያሉ ይናገራሉ። የመርከባቸውንም ጭነት ከእንግዲህ ወዲህ የሚገዛ የለምና የምድር ነጋዴዎች ያለቅሱላታል፤ ያዝኑላትማል፤ ጭነቱም ወርቅና ብር፥ የከበረም ድንጋይ ዕንቁም፥ ቀጭንም ተልባ እግር፥ ቀይም ሐር፥ ሐምራዊም ልብስ፥ መልካም መዐዛ ያለውም እንጨት ሁሉ፥ ከዝሆን ጥርስም የተሠራ ዕቃ ሁሉ፥ እጅግም ከከበረ እንጨት፥ ከነሐስም ከብረትም ከዕብነ በረድም የተሠራ ዕቃ ሁሉ፥ ቀረፋም፥ ቅመምም፥ የሚቃጠልም ሽቱ፥ ቅባትም፥ ዕጣንም፥ የወይን ጠጅም፥ የወይራ ዘይትም፥ ምርጥ ዱቄትም፥ ስንዴም፥ ከብትም፥ በግም፥ ፈረስም፥ ሠረገላም፥ ባርያዎችም፥ የሰዎችም ነፍሳት ነው። “ነፍስሽም የጎመጀችለት ፍሬ ከአንቺ ተለይቶ ሄዶአል፤ የድሎትና የጌጥ ነገር ሁሉ ጠፍቶብሻል፤ ከእንግዲህ ወዲህም ከቶ አይገኙም።” እነዚህን የነገዱ በእርሷም ሀብታም የሆኑት እያለቀሱና እያዘኑ “በቀጭን ተልባ እግርና በቀይ ሐምራዊም ልብስ ለተጐናጸፈች በወርቅና በከበረ ድንጋይም በዕንቁም ለተሸለመች ለታላቂቱ ከተማ ወዮላት! ወዮላት! ይላሉ። ይህን የሚያህል ታላቅ ሀብት በአንድ ሰዓት ጠፍቶአልና፤” የመርከብም መሪ ሁሉ በመርከብም ወደ ማናቸውም ስፍራ የሚሄድ ሁሉ መርከበኞችም ከባሕርም የሚጠቀሙ ሁሉ በሩቅ ቆሙ፤
የዮሐንስ ራእይ 18 ያንብቡ
ያዳምጡ የዮሐንስ ራእይ 18
Share
ሁሉንም ሥሪቶች ያነጻጽሩ: የዮሐንስ ራእይ 18:1-17
ጥቅሶችን ያስቀምጡ፣ ያለበይነመረብ ያንብቡ፣ አጫጭር የትምህርት ቪዲዮዎችን ይመልከቱ እና ሌሎችም!
Home
Bible
Plans
Videos