መዝሙረ ዳዊት 78:34-55

መዝሙረ ዳዊት 78:34-55 መቅካእኤ

በገደላቸውም ጊዜ ወዲያው ፈለጉት፥ ተመለሱ ወደ እግዚአብሔርም ገሠገሡ፥ ዓለታቸው እግዚአብሔር፥ መድኃኒታቸውም ልዑል አምላክ እንደሆነ አስታወሱ። በአፋቸው ሸነገሉት፥ በአንደበታቸውም ዋሹት፥ ልባቸውም ከእርሱ ጋር አልቀናም፥ ለቃል ኪዳኑም አልታመኑም። እርሱ ግን ርኅሩኅ ነው፥ በደላቸውንም ይቅር አላቸው፥ አላጠፋቸውምም፥ ከቁጣውም መመለስን አበዛ፥ መዓቱንም ሁሉ አላቃጠለም። ወጥቶ የማይመለስ ነፋስ፥ ሥጋም እንደ ሆኑ አሰበ። በምድረ በዳ ምን ያህል አስቈጡት፥ በበረሃም አሳዘኑት። መላልሰው፥ እግዚአብሔርንም ተፈታተኑት፥ የእስራኤልንም ቅዱስ አሳዘኑት። እነርሱም እጁን አላሰቡም፥ ከጠላቶቻቸው እጅ ያዳነበትን ቀን፥ በግብጽ ያደረገውን ተኣምራቱን፥ በጾዓን አገር ያደረገውን ድንቁን። ወንዞቻቸውንም ወደ ደም ለወጠ፥ ምንጮቻቸውን እንዳይጠጡ። ዝንቦችንም በላያቸው ሰደደባቸው፥ በሉአቸውም፥ በጓጉንቸርም አጠፋቸው። ሰብላቸውን ለኩብኩባ፥ ምርታቸውንም ለአንበጣ ሰጠ። ወይናቸውን በበረዶ፥ በለሳቸውንም በአመዳይ አጠፋ። እንስሶቻቸውን ለበረዶ፥ ሀብታቸውንም ለመብረቅ ሰጠ። የቁጣውን ንዳድ በላያቸው ሰደደ፥ መቅሠፍትን መዓትንም መከራንም በክፉዎች መላእክት ሰደደ። ለቁጣው መንገድን ጠረገ፥ ነፍሳቸውንም ከሞት አላዳናትም፥ ሕይወታቸውንም ለመቅሰፍት አሳልፎ ሰጠ። በኩሮቻቸውን ሁሉ በግብጽ፥ የድካማቸውንም መጀመሪያ በካም ድንኳኖች መታ። ሕዝቡን ግን እንደ በጎች አሰማራቸው፥ እንደ መንጋም በምድረ በዳ መራቸው። በተስፋም መራቸው አልፈሩምም፥ ጠላቶቻቸውንም ባሕር ደፈናቸው። ወደ መቅደሱም ተራራ አገባቸው፥ ቀኙ ወደ ገዛችው ወደዚህች ተራራ፥ ከፊታቸውም አሕዛብን አባረረ፥ ርስቱንም በገመድ አካፈላቸው፥ የእስራኤልንም ወገኖች በድንኳናቸው አኖረ።