መዝሙረ ዳዊት 37:23-40

መዝሙረ ዳዊት 37:23-40 መቅካእኤ

መንገዱን በወደደ ጊዜ፥ የሰው አካሄድ በጌታ ይጸናል። ቢወድቅም አይጣልም፥ ጌታ እጁን ይዞ ይደግፈዋልና። ጐለመስሁ አረጀሁም፥ ጻድቅ ሲጣል፥ ዘሩም እህል ሲለምን አላየሁም። ሁልጊዜ ይራራል ያበድርማል፥ ዘሩም በበረከት ይኖራል። ከክፉ ሽሽ፥ መልካምንም አድርግ፥ ለዘለዓለምም ትኖራለህ። ጌታ ፍርድን ይወድዳልና፥ ቅዱሳኑንም አይጥላቸውምና፥ ለዘለዓለምም ይጠብቃቸዋል ለንጹሓንም ይበቀልላቸዋል፥ የክፉዎች ዘር ግን ይጠፋል። ጻድቃን ምድርን ይወርሳሉ፥ በእርሷም ለዘለዓለም ይኖራሉ። የጻድቅ አፍ ጥበብን ያናገራል፥ አንደበቱም ፍርድን ይናገራል። የአምላኩ ሕግ በልቡ ውስጥ ነው፥ በእርምጃውም አይሰናከልም። ክፉ ጻድቁን ይመለከተዋል፥ ሊገድለውም ይወድዳል። ጌታ ግን በእጁ አይተወውም፥ በፍርድም እንዲሸነፍ አይፈቅድም። በጌታ ተስፋ አድርግ፥ መንገዱንም ጠብቅ፥ ምድርንም ትወርስ ዘንድ ከፍ ከፍ ያደርግሃል፥ ክፉዎችም ሲጠፉ ታያለህ። ክፉን በጭቆና ከፍ ከፍ ብሎ እንደ ሊባኖስ ዝግባም ለምልሞ አየሁት። ብመለስ ግን አጣሁት፥ ፈለግሁት ቦታውንም አላገኘሁም። ቅንነትን ጠብቅ፥ ጽድቅንም እይ፥ ለሰላም ሰው ተተኪ ይወጣለታልና። በደለኞች በአንድነት ይጠፋሉ፥ የክፉዎቸ ዘር ይጠፋል። የጻድቃን መድኃኒታቸው በጌታ ዘንድ ነው፥ በመከራቸውም ጊዜ መጠጊያቸው እርሱ ነው። ጌታ ይረዳቸዋል፥ ያድናቸዋልም፥ ከከፉዎችም እጅ ያወጣቸዋል፥ ያድናቸዋልም፥ በእርሱ ታምነዋልና።

ቪዲዮ ለ {{ዋቢ_ሰዉ}}